በጉራጌ ሀገረ ስብከት በእያ ወረዳ ቤተክህነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ

ጥር 23ቀን 2013 ዓ.ም በጉራጌ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኘው በእዣ ወረዳ ቤተ ክህነት የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕንጻ ቤተክርስቲያን የቅዳሴ ቤቱ ክብረ በዓል የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱና የወረዳ ቤተ ክህነቱ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በቀዳማዊው የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጸሎተ ቡራኬ በ2000ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ከ4 ዓመታት በኀላ የሕንጻው ሥራ የተጀመረው የጻድቁ መታሰቢያ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ቀና ትብብርና በበጎ ሥራቸው በሚታወቁት በኩረ ምዕመናን ይቁም መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ አስተዋጽኦ ለመጠናቀቅ እንደበቃ በአሰሪ ኮሚቴው በኩል በቀረበው ሪፖርት ተገልጿል፡፡

የጥንታዊው የምሁር ገዳመ ኢየሱስ አበምኔት አባ ዘኢየሱስ በቦታው ለተገኘው ሕዝበ ክርስቲያን ዕለቱን አስመልክተው ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በጻድቁ ስም የተሠራው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ለምትገኙ ወገኖች ወንጌል እንድትማሩበትና እንድትጸልዩበት እንዲሁም ሥጋና ደሙን እንድትቀበሉበት ነው፡ ይህንን በጎ ተግባር የሠራችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኀል በማለት አመስግነዋል፡ ለደብሩም ምሥራቀ ፀሐይ የሚል የመጠሪያ ስም ሰይመዋል፡፡

አያይዘውም በዚህ ቦታ የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ምሉዕ ለማድረግና ተተኪ ትውልድ ለማፍራት የአብነትና የሰንበት ትምሕርት ቤት አቋቁም፡ ልጆቻችሁንም አስተምሩ ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተያያዘ ዜናም በዚያው ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘውን የገጨ ቅዱስ ሩፋኤል አንድነት ገዳምንና ገዳማውያኑን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

ዘጋቢ፡- መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡- በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

የመልአኩ ቅዱስ ዑራኤል የበዓለ ሲመት መታሰቢያ በዓል በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ

ጥር 22 ቀን 2013 ዓ.ም በካዛንችስ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን በተከበረው የመልአኩ ቅዱስ ዑራኤል የበዓለ ሲመት መታሰቢያ ክብረ በዓል የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ በርካታ የቤተክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎችና ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናን በተገኙበት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምሕርት ቤት ዘማርያን ያሬዳዊ ዝማሬና ትምሕርተ ወንጌል ታጅቦ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡

ለረጅም ጊዜያት የጸበል አገልግሎት ይሰጥበት የነበረው የመልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ጸበል ቤት በአካባቢው ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር አስተባባሪነት በአዲስ መልኩ ተሠርቶና በርካታ የመጠመቂያ ክፍሎች ተዘጋጅተውለት በብፁዕነታቸው ተባርኮ ለድጋሚ አገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል፡፡

የዕለቱ ትምህርተ ወንጌልም በሀገረ ስብከቱ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለ ወልድ ተሰማ ተሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በደብሩ ተገኝተው ባዩት መንፈሳዊ አገልግሎትና የልማት እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልጸው፡ በዚህ መንፈሳዊ ተግባር ላይ የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነዋል ፡ቃለ ምዕዳንና አባታዊ መልእክትም አስተላልፈዋል።

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ለሙዳይ በጎ ኣድራጎትና ለየካ ወረዳ 3 የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ድጋፍ አደረገ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ምግባረ ሰናይ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተሰበሰቡ የትምህርት ቁሳቁሶች፣ የልብስና የቤት ዕቃዎችን ለሙዳይ በጎ ኣድራጎትና ለየካ ወረዳ 3 የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አስረክቧል፡፡
ድጋፉን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳሰና የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደሐና ለማኅበራቱ ተወካዮች አስረክበዋል፡፡
ብፁዕነታቸውና የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ድርጅቶቹን በያዙት መልካም ሥራ እንዲቀጥሉ አበረታትተዋቸዋል፡፡
ማኅበራቱ መንገድ ላይ ወድቀው የተገኙ የአእምሮ ታማሚዎችን፣ ተጥለው የተገኙት ሕጻናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ሴቶችን የሚንከባከቡና የሚረዱ እንዲሁም ሕጻናትን የሚያሳድጉና የሚያስተምሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መሆናቸውን በድርጅቶቹ ተወካዮች ተገልጿል፡፡
ባለፉት ጊዜያት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የምግባረ ሰናይ ዋና ክፍል ኃላፊ መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ ድጋፉ ቀጣይ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው
በዚሁ መሠረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ድጋፍ እያደረገና መልካም ሥራዎቻቸውን እያበረታታ ይገኛል፡፡

በየካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የቃና ዘገሊላ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሮ ዋለ

በዛሬው ዕለት ጥር 12 ቀን 2013 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ አረጋዊ(ዶ/ር) የውጭ ግንኙነትና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ኃላፊና እንዲሁም የድሬደዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጲያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ፣ ንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ በጠቅላይ ቤተክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ኃላፊ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ እሰኪያጅ መጋቤ ትፍስሕት ግርማ አሰፋ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሳህል ቆሞስ አባ ተክለብርሃን፣ የደብሩ ዋና ጸሐፊ መ/መዊእ በቃሉ ያለው፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና የደብሩ ማኅበረ ካህናት፣እንዲሁም በርካታ ምእመናንና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች መዘምራን በተገኙበት ከታቦታቱ ማደሪያ ጀምሮ እስከ የካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ድረስ ባለው ጎዳና በዝማሬ፣በሆታና በእልልታ የቃና ዘገሊላ ክብረ በዓል በድምቀት የታሰበ ሲሆን በደብሩም ሥርዓተ ቅዳሴ ተፈጽሟል።
ብፁዕ አቡነ አረጋዊ(ዶ/ር) በደብሩ የጸበል ቦታ ዕለቱን በተመለከተ “ስለ ቃና ዘገሊላ” የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1 እስከ 11 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሠረት በማድረግ ትምህርት የሰጡ ሲሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም ብላ ለልጇ እንዳሳሰበች፤ ለአገልጋዮቹም የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ እንዳለቻቸው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቃና ዘገሊላ የምልክቶች መጀመሪያ እንዳደረገ፤ ክብሩንም እንደገለጠና ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ እንዳመኑ አብራርተው ስለ በዓሉ ይዘት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ታቦታቱ ደብሩ ጋ ከደረሱ በኋላ ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቦ ብፁዕነታቸው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ፣ መልካም እረኛ፣ የሕይወት እንጀራና የዓለም ብርሃን መሆኑን አብራርተው፤ የተዘጋውን ገነት የከፈተና ለ5,500 ዘመን ጎድሎ የነበረውን ሕይወት የሞላ አምላክ በእያንዳንዳችን ጓዳ የጎደለውን እርሱ ይሙላልን በማለት በዓሉ የሰላም፣ የጤና ፣የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸውና ቃለምዳን ሰጥተው ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል።


ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

መ/ር አካለወልድ ተሰማ የአ/አ/ሀ/ስ/ ዋና ስራ አስኪያጅ የከተራ እና ጥምቀት በዓል በዓለም ምን እንደሚመስል ሃይማኖታዊ እንድምታ እና ሥርዓቱ ምንድን ነው ? በሚል ርዕስ የሰጡትን ማብራሪያ ይከታተሉ

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

ብፁዕነታቸው “በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው” እንደገለጹት የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ስናከብር “እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6፥4-5) የሚለውን መለኮታዊና ሕያው የሆነውን ቃል በውስጣችን በማሰብ ማክበር እንደሚገባን መልእክት አስተላልፈዋል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በ30 ዓመቱ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ የመጠመቁ ዓላማ ምሥጢረ ሥላሴን ለመግለጥ (ማቴ 3፤16-17)፣ ጽድቅን ሁሉ ሊፈጽም (ማቴ 3፡15)፣ ትሕትናን ሊያስተምረን (ማቴ 3፡13-15)፣አርአያ ሊሆነን እንደሆነ ትኩረት በመስጠትና ከልብ በማስታወስ በዓሉን ማክበር እንደሚኖርብን የበዓሉን ጭብጥ መልእክት በመግለጽ አብራርተዋል።
አያይዘውም በዓሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ በመሄድና በእርሱ እጅ በመጠመቅ ትህትናን በተግባር ፈጽሞ ያሳየበትና ያስተማረበት ዕለት እንደመሆኑ መጠን እኛም የክርስቶስን ፈለግ በመከተል የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ወላጅ አልባ ሕጻናትን በመጎብኘትና በመንከባከብ፣በኃዘን ላይ ያሉትን በማጽናናትና ትህትናን አብዝተን በተግባር በመፈጸም በዓሉን ማክበር እንደሚገባንም መክረዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በዓሉ የሰላም፣የጤና፣ የአንድነትና የፍቅር እንዲሆንልን ከምንም በላይ የበዓሉ መንፈሳዊ ይዘት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን ለአባቶችና ለመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካላት ትዕዛዝና መመሪያ በመታዘዝ፣ በስሜት ሳይሆን በማስተዋልና በእምነት፣ እርስ በእርስ በመደማመጥና በመናበብ፣ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን በመጠበቅና የጤና ሚንስተር መመሪያዎችን በመተግበር ማክበር እንደሚኖርብን አጽንዖት ሰጥተው አባታዊ መመሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

በCMC ደብረ ጽባሕ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለዘጠኝ ዓመታት ያክል ደብሩን ሲያስተዳደሩት ለነበሩት መልአከ ምሕረት ዘካርያስ ሐዲስ የሽኝት መርሐ ግብር ተደረገ

ጥር 9 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፡ የEOTC መገናኛ ብዙኃን ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተስማ: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፡ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/ምሕረት ዘካርያስ ሐዲስ፡ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፅባሕ ቆሞስ አባ ጥዑመልሳን አድነውና የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና የደብሩ ማኅበረ ካህናት፡እንዲሁም የደብሩ ማኅበረ ምእመናንና የሰ/ት/ቤት መዘምራን ተወካዮች በተገኙበት በደብሩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በዘጠኝ ዓመታት የአስተዳዳሪነት ቆይታቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦና ላሳዩት ቅን አመራር ዕውቅና የሚሰጥ የሽኝትና የሽልማት መርሐ ግብር ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት መ/ም ዘካርያስሐዲስ በዚህ ታላቅ ቦታ የሚያገለግሉ ካህናትና ምእመናን ገና ወደ ደብሩ ተመድቤ ስገባ በሽልማት ተቀብለውኝ፡ ስንብቴንም በዚያው መልኩ አድርገውታል፡ይህም ለእኔ ያላችሁን አክብሮትና ፍቅር ያሳያልና ለመልካም ድርጊታችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ውለታቸሁን ይክፈል፡በአደረጋችሁት በጎ ሥራ ደስታዬ ወደር የለውም እጅግ አመሰግናለሁ፡ ዕለቱን እንደ ዳግም ልደቴ እቆጥረዋለሁ ሲሉ በሽኝቱ መርሐ ግብር የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተስማ:የዛሬ ወር አካባቢ የዚህ ደብር ካህናትና ምእመናን ተወካዮች ቢሮዬ ድረስ በመምጣትመልካሙን አስተዳዳሪያችንን ለምን ታነሱብናላችሁ አሉኝ፡ እኔም የተነሡበት ምክንያት ለዕድገት መሆኑን ገለፅኩላቸውና ሐሳቤን ተቀበሉ፡ዛሬ ደግሞ የምትወዷቸው አባት መሆኑን በእርግጥም በተግባር አሳያችሁን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለሚተጋ አገልጋይ እንደዚህ ዓይነት የሽኝት መርሐ ግብር መደረጉ አግባብ ነው፡ በአሁኑ ስአት ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ ያለምንም ዕረፍት የሚመሩት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፍቅርና በመርህ ከመሞላቱም ባሻገር በዕቅድ የተመራ የሥራ ውጤት ለማስመዝገብ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡ ይህ መልካም ጅምር ወደ አጥጋቢ ውጤት እንዲለወጥና የተፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ ደግሞ የእናንተ የአባቶቻችንና ወንድሞቻችን ያላሰለሰ ጸሎት፡ ሐሳብና ዕውቀት ያስፈልገናልና አብሮነታችሁ አይለየን በማለት አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ወደእግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ እንዳለ፡ እኔም ምንም እንኳን በከፍተኛ የሥራ ውጥረት የሥጋ ድካም ውስጥ ብቆይም የፍቅር አዝመራ ወደ ሚዘመርበት ወደዚህ ቦታ ስመጣ በደስታ ስሜት ነው፡ ምክንያቱም ያደረጋችሁት በጎ ተግባር ድካምን ያሳረሳልና ነው፡የዛሬዋ ዕለት የእሳቸው ሽኝት ብቻ ሳይሆን የሀገረ ስብከቱ የሥራ ፍሬ የታየበትም ቀን ነውና ኮርቻለሁ፡ሌሎች አድባራትም ከዚህ ሊማሩ ይገባል፡ ወደፊትም አዲስ ከተመደቡላችሁ አስተዳዳሪ ጋር በመመካከርና በመተባበር ዓለም አቀፋዊ መሥፈርቱን ጠብቆ በመሠራትና በመገባደድ ላይ የሚገኘውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አጠናቁ፡ከምንም በላይ የሰው ልጅ እየፈረሰ ሕንጻ መገንባት አግባብ አይደለምና ስብከተ ወንጌሉንም አጠናክሩ፡አሁን ባለንበት ዘመን አሠራራችንን ለማዘመን የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የግድ ነው፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ራሳችንን አዘጋጅተን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዕድገት መፋጠን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

ዓመታዊው የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ

ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ጢሞቲዎስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ፣ የአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/አሚን አባ ላዕከ ማርያም፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሲራክ እንዲሁም የደብሩ ማኅበረ ካህናትና እጅግ በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን በተገኙበት የእግዚአብሔርን ክብር በሚገዳደር መልኩ በሰናዖር ሜዳ ላይ የተሠራውን ሕንጻ ሰናዖር እግዚአብሔር ያፈረሰበትንና መግባቢያ ቋንቋቸውንም የደባለቀበትን ዕለት በሚዘከርበት ሁኔታ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የዕለቱን ታሪክ የተመለከተ ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በእኛም ዘመን የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋፋ የትኛውም ዓይነት ክፉ ተግባር እንዳናከናውን ደግሞም በሕይወታችን ያለውን የኃጢአት ክምር በንስሐ እናፈርሰ ዘንድ መልእክት ተላልፏል፡፡

በመቀጠልም ካቴድራሉ በ1924 ዓ.ም ተመስርቶ በ1936 ዓ.ም መንፈሳዊ አገልግሎት መጀመሩና ለረጅም ጊዜያት ማለትም ለሰባ ሰባት ዓመታት ያክል አገልግሎት በመስጠቱ የተነሣ በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ተገልፆ በአሁኑ ስዓት ግን ይህንን ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርስ ለመታደግና የዕድሳት ሥራ ለመሥራት ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገርና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች እንደ ተዋቀረና በእንቅስቃሴ ላይም እንደሚገኝ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተደምጧል፡፡

በመጨረሻም የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የዕለቱ ትምህርት በሰፊው ተሰጥቷልና ይበቃናል፣ የሰማነውን በሕይወት እናኑረው፣
ይህ ትልቅ ካቴድራል ከመንፈሳዊ ቦታነቱም ባሻገር የቤተ ክርስቲያናችንን ብሎም የሀገራችንን ታሪክ ጠገብነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፣ ስለሆነም የተጀመረው የዕድሳት እንቅስቃሴ የሕንጻውን ታሪካዊ ማንነት በጠበቀ መልኩ መታደስ ይኖርበታል፣ ለዚህም መልካም ተግባር ሀገረ ስብከታችን በአስፈላጊው ነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ነው በማለት አረጋግጠዋል።
የጥምቀት በዓልም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ እንዲከበር ለሕዝበ ክርስቲያኑ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

4.1

በዓለ አስተርእዮ

አስተርእዮ፡- ቃሉ ግእዝ ነው፡፡ አስተርእዮ ማለትም መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው፡፡
በግሪክ ቋንቋ ኤጲፋንያ ይባላል ኤጲፋንያ ማለት መገለጥ፤ መታየት ማለት ነው፡፡ አሁን ያለንበት ዘመን ዘመነ አስተርእዮ ይባላል የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ማለት ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ የተገለጠበት ዘመን ስለሆነ እና እንዲሁም በጥምቀቱ አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠበት ዘመን በመሆኑ ዘመነ አስተርእዮ፡- የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ተብሏል፡፡
የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡
❖ አንድነቱን ሦስትነቱን ለመግለጽ ነው፡- /በማቴዎስ ወንጌል ም. 3፡13-17/ እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ እግዚአብሔር አብ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር” /የምወደው ልጄ እርሱ ነው/ ሲል ከሰማይ ተናግሯል፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚህም አንድነቱን ሦስትነቱን ገልጧል፡፡
❖ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡ ከትንቢቶቹ አንዱን ለአብነት ያህል እንጠቅሳለን “ባሕርኒ ርዕየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬኁ አድባር አንፈርአጹ ከመ ሐራጊት” /ባሕርም አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ ተራሮችም እንደ ጊደሮች ዘለሉ/፡፡ /መዝ. 113፡3/
❖ የዕዳ ደብዳቤአችንን ለመቅደድ ነው፡፡ የክፋት እና የተንኮል ምንጭ የሆነው ጠላታችን ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን መከራውን እንዳቀልላችሁ ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ አላቸው፡፡ ይህም ማለት የእኔ አገልጋይ መሆናችሁን የሚገልጽ ጽሑፍ ስጡኝ ማለት ነው እነርሱም እውነት መከራውን የሚያቀልላቸው መስሏቸው ጽፈው ሰጡት፡፡ ጽሑፉም “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት አዳም የዲያብሎስ አገልጋይ ነው ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት ማለት ነው፡፡ ይህንንም በሁለት የድንጋይ ሠሌዳ ላይ ጽፈው ሰጡት አንዱን በዮርዳኖስ፣ አንዱን በሲኦል ጣለው፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን የዕዳ ደብዳቤአችንን ጥር 11 ቀን የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ደምስሶልናል አጥፍቶልናል፡፡

በሲኦል የጣለውን ደግሞ በዕለተ አርብ በስቅለቱ በሞቱ ደምስሶልናል አጥፍቶልናል “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ አስወግዶታል” /ቆላስ 2፡14/
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም ይህንን መሠረት በማድረግ በደረሰው የእመቤታችን ምስጋና ላይ “ወሠጠጠ መጽሐፈ ዕዳሆሙ ለአዳም ወለሔዋን” /የአዳም እና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ቀደደ፤ ደመሰሰ፣ አጠፋ/ ሲል ተናግሯል፡፡
❖ ጥምቀትን ለእኛ ለመባረክ ነው፡፡ ለእኛ አብነት ለመሆንና ከአምስቱ አእማደ ምሥጢር በአንዱ በምሥጢረ ጥምቀት ልጅነትን እንድናገኝ ለማድረግ ነው፡፡
“በዮርዳኖስ ውኃ በተጠመቀ ጊዜ ይህ ምሥጢር ዳግመኛ ተገለጠ፤ ጥምቀትን ሽቶ አይደለም፤ ሽቶ አልተጠመቀም፤ አምላክ በሥጋ ተገልጦ ጥንተ ልደትን ዳግመኛ ይሰጠን ዘንድ ነው እንጂ” (ሃይ.አበው ምዕ. 87፥15)
❖ ትሕትናን ለእኛ ለማስተማር ነው፡፡ ይህም በአገልጋዩ በቅ/ዮሐንስ እጅ መጠመቁ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀባቸው አምስት ምክንያቶች ከላይ ከ1-5 ተራ ቁጥር የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በ30 ዘመኑ ተጠመቀ? ቢሉ አዳም በተፈጠረ በ30 ዘመኑ ልጅነቱን አስወስዷል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ልጅነት ለመመለስ በተመሳሳይ ዘመን በ30 ዘመኑ ተጠምቋል፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በውኃ ተጠመቀ? እኛም በውኃ እንድንጠመቅ ለምን አዘዘ?
የሰላም ንጉሥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ የተጠመቀበት፣ እኛም በውኃ እንድንጠመቅ ያዘዘበት ምክንያት ብዙ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ውኃን ድሃውም ሀብታሙም በቀላሉ ያገኘዋል ለድሃውም ለሃብታሙም እኩል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ስለሚፈልግ በውኃ እንድንጠመቅ አዘዘ፡፡ እርሱም በውኃ ተጠመቀ፡፡
ያለ ጥምቀት መዳን የለም “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፡፡ /ማር. 16፡16/ “አማን አማን እብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል በዊአ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር” /እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይችልም/ /ዮሐ. 3፡5/ ሲል የእውነት አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በነገረው መሠረት ያለ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ አይቻልም፡፡
ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀን ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀን የሚጠመቁበት ምክንያት፡- እንደሚከተለው ተገልጻል፡፡

1ኛ. አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ ቅድስት ሥላሴ ብርሃን አልብሰው ብርሃን አጎናጽፈው ገነት አስገብተዋቸዋል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ዛሬ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ /መጽ. ኩፋ 4፥9-13/
2ኛ. በብሉይ ኪዳን ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀኗ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይገቡ ነበር /ዘሌዋ. 12፡ 1-5/ ይህንም መሠረት በማድረግ ዛሬ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ፡፡
መንታ ወንድና ሴት ልጆች ከተወለዱ ወንዱ ልጅ አርባ ቀን ሲሞላው በሞግዚት ሄዶ ይጠመቃል፡፡ ሴቷ ልጅ ደግሞ ሰማንያ ቀን ሲሞላት በእናቷ ሄዳ ትጠመቃለች፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 3) በ40፣ በ80 ቀን የምንጠመቅበት ውኃ፡- በግእዝ ማየ ገቦ ይባላል፡፡ ማይ ውኃ፤ ገቦ ጎን ነው ማየ ገቦ፡- አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ሲሰቀል ከጎኑ የፈሰሰው ውኃ ነው፡፡ በቄሱ ጸሎት ውኃው ወደ ማየ ገቦነት ይለወጣል፡፡ በዚህ ተጠምቀን ከሥላሴ ተወልደናል፤ ልጅነትን አግኝተናል፤ ክርስቲያንም ተብለናል፤ ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኘነው በጥምቀት ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት ትርጉሙ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቀ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለናል፡፡ በዚህ መሠረት የክርስቲያኖችን ሥራ ሠርተን መገኘት አለብን የክርስቲያኖች ሥራ፤ ሕገ እግዚአብሔርን፣ ትእዛዘ እግዚአብሔርን መጠበቅ ነው “ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” /ዮሐ. 14፡15/ ብሎ አምላካችን በቅዱስ ወንጌል በተናገረው መሠረት ትእዛዙን መጠበቅ አለብን የክርስቲያኖች ሥራ ይህ ነው፡፡ ትእዛዙን ካልጠበቅን ወዳጆቹ አይደለንም ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ ብሏልና በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ ትእዛዙን እንጠብቅ፡፡

ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን በማየ ንስሓ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከላእከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በመካኒሳ ምዕራፈ ጻድቃን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ካቴድራል በመገኘት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴንና የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

በዛሬው ዕለት ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥር በሚገኘው በመካኒሳ ምዕራፈ ጻድቃን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ካቴድራል በመገኘት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴንና የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝት መርሃግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰው ኃይል አስተዳደር መ/ር አይናለም ተጫኔ፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ፣ የካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ መ/ር እዝራ ንዋይ፣የካቴድራሉ ሰባክያነ ወንጌል፣ የካቴድራሉ ካህናትና ዲያቆናት፣ዘማሪ ዳግማዊ ደርቤ እንዲሁም በርካታ ምእመናን የተገኙ ሲሆን በመምህራን ስብከተ ወንጌል በሰፊው ተላልፏል።
ካቴድራሉ በስብከተ ወንጌል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን፣ ዘወትር አርብ በካቴድራሉ አዳራሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለምእመናን እንደሚሰጥ፣እሁድና ረቡእ ሳምንታዊ ታላቅ ጉባኤ እንደሚካሄድ፣በየወሩ ብሮሸር(በራሪ ወረቀት) እየታተመ ለምእመናን እንደሚሰራጭ፣በሶስት ወር አንድ ጊዜ መጽሔት እየታተመ ወደ ምእመናን እንደሚደርስ የካቴድራሉ ጸሐፊ መ/ር እዝራ ንዋይ ገልጸውልናል።
አያይዘውም የካቴድራሉ ቢሮዎች ኮምፒውተር ያላቸውና ዋይፋይ የተገጠመላቸው መሆናቸውን፣ ዩቲዩብ ተከፍቶ የካቴድራሉን የወንጌል እንቅስቃሴ በውጪና በሀገር ውስጥ ያሉ ምእመናን በቀላሉ እንደሚከታተሉ፣ ካቴድራሉ የአብነት ትምህርት መዋቅራዊ መመሪያ ፕሮጀክት መንደፉንና ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑን፣ ካቴድራሉ በአሠራሩ የዘመነና ዘመኑን የዋጀ ሥራ እየሠራ ከመሆኑም ባሻገር ለሌሎች አድባራትና ገዳማት አርአያ መሆኑን አብራርተውልናል።
የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ስለ ምእመናኑ ወንጌል ወዳድነት፣ምእመናኑ በልማት ሥራ ላይ ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦና በካቴድራሉ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን አብራርተው ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ” በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ” (የማቴዎስ ወንጌል 16:18) በሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ተነስተው ትምህርተ ወንጌልን ለምእመናን አብራርተው አስተላልፈዋል፤ አያይዘውም የቤተክርስቲያን መሠረትና ክብር ኢየሱስ ክርስቶስን አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ማመንና ማስተማር እንደሆነ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በካቴድራሉ አስተዳዳሪ መልአከ ምህረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ ጸሎት ተደርጎ መርሃግብሩ ተፈጽሟል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ