“ችግኝን መትከልና መንከባከብ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ነው” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ “ችግኝን መትከልና መንከባከብ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ነው” ሲሉ መልእክት አስተላለፉ።
ብፁዕነታቸው መልእክቱን ያስተላለፉት በጉለሌ የእፅዋት ማዕከል በመገኘት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ባካሄዱበት ነው።
የችግኝ ተከላ መርሐግብሩን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጋር በመተባበር ነው።
“አብሮነትን በማበልጸግ አዲስ አበባን እናልብሳት” በሚል መሪ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ተካሂዷል።
“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው” (ዘፍ 2:15) በሚል መለኮታዊ ቃል መነሻነት እግዚአብሔር መጀመሪያውኑ ሰውን ሲፈጥር ከልማት ጋር አያይዞ መሆኑን ብፁዕነታቸው አብራርተዋል።
አያይዘውም ችግኝን መትከልና መንከባከብ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እፀዋትን በመትከል የጎላ ሚና ያላት ስለመሆኗ በየገዳማቱና በየአድባራቱ ያሉት ዕድሜ ጠገብ ዛፍች ምስክሮች ናቸው ሲሉም አውስተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም በሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ሕይወት፣በሰላም፣በፍትህ፣ አረንጓዴ አሻራን በማሳረፍ ረገድ የራሱ ኃላፊነት እንዳለውም አብራርዋል።
ሁላችንም የድርሻችንን ከተወጣን ልምላሜን በክረምት ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የማየት ዕድል ይኖረናል ብለዋል።
ዛፎች በየቦታው ካሉ አዛውንቶች ያርፋሉ፣ ወጣቶች ያነባሉ፣ ሕጻናት ይጫወታሉ በማለትም ገልጸዋል።
ቤተእምነትን ወክለው ለተገኙት ሁሉ ችግኝን መትከልና መንከባከብ የቤተእምነቶች መገለጫ እንዲሆን መልእክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የመንግሥት ባለሥልጣናትና የቤተእምነት አባቶችም በመርሐ ግብሩ ላይ “አብሮነትን በማበልጸግ አዲስ አበባን እናልብሳት” በሚለው መሪ ቃል ላይ መነሻነት እፀዋትን በመትክል የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አብራርተዋል።
በመርሐግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ኃላፊዎችና አባላት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ ከሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተክህነት አስር አስር የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።


ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

በጉራጌ ሀገረ ስብከት በእዣ ወረዳ በአገና ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ዑራኤል አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ በመጠናቀቁ በብፁአን አባቶች ተባርኮ ተመረቀ

በጉራጌ ሀገረ ስብከት በእዣ ወረዳ በአገና ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ዑራኤል አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ በመጠናቀቁ በግንቦት 21 ቀን በአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና በሰሜን አሜሪካ የካሊፎርንያ አከባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተባርኮ ተመርቋል፡፡

አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረተ ድንጋዩ ከተጣለ ከ9 ዓመታት በኋላ ተጠናቅቆ በግንቦት 21 ቀን ተባርኮ በማግሥቱ በቀን 22 ብፁአን አበው ሊቀ ጳጳስትና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ የዋለ ሲሆን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቀድሰው ምእመናኑን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን አቀብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕዝብ ግኑኝነት ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በትምህርታቸው በኢሳ 6÷6-7 ያለው ኃይለ ቃል መነሻነት “ሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።“ በማለት መላእክት ለሰው ልጆች ያላቸውን ተራዳኢነትና ባለሟልነት ሰፋ አድረገው ማስተማራቸውን ተገልጿል፡፡

በክብረ በዓሉ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስም ግበሩ ኲሎ ዘይቤለክሙ፣ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ በሚል መነሻነት ሰዎች ሁሉ የእመቤታችን ምክር ሰምተው ፣የእግዚአብሔርን ቃል፣ ትእዛዝ፣ ብሎም የቤተ ክርስቲያንንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ትእዛዝ እንዲከብሩ ለምእመናኑ አባታዊ ምክራቸውን አሰተላልፈዋል፡፡

ለካህናቱና ምእመናኑ አባታዊ መልእክትና መመሪያ ያስተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፡ ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናት እየተገነቡ ናቸው፣ እኛም በዛው ልክ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተገኝተን ተምረን በሃይማኖትና በምግባር ታንጸን በክርስቲያናዊ ሕይወት በመልካም ልናድግ ይገባል ብለዋል፡፡

ከሕንጻዉ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሪፖርት እንደተደመጠው ሕንጻው ለማስጀመር የነበረውን 70ሺህ ብር ብቻ ይዘው ብረት ለመግዛት ወደ ገበያ ሲሄዱ የብረቱ ዋጋ ከዛ በላይ በመሆኑና ባለሀብቱ/ነጋዴው የተፈለገው ብረት ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ መሆኑን በማወቁ 70ሺህ ብሩና የሚያስፈልጋችሁን ብረት ይዛችሁ ሂዱ ብሎ መተባበሩን ተነግሯል፡፡

ከዚህ በተያያዘም የቤተ ክርስቲያኑ የሕንጻው ዲዛይንና ሙሉ ሞያዊ አቅም በኢንጅነር ቸሩ መሸፈኑን ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ምንጭ ከሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት የተገኘ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከተጋባዥ እግዶቻቸው ጋር በጉራጌ ሀገረ ስብከት እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በሰሜን አሜሪካ የካሊፎርንያ አከባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ከሌሎች እግዶች ጋር በጉራጌ ሀገረ ስብከት እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዊችን ጎብኝተዋል

ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳስቱና እንግዶቹ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኝ ብዙ መናንያንና መናንያት ያሉበትን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ልዩ ድጋፍና ክትትል የሚደረግለት የገጨ ገዳም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በመጎብኘት ለገዳማውያኑ የማበረታቻ ቃለ ምዕዳንና አባታዊ መመሪያን ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም ወደ መንበረ ጵጵስናቸው በማቅናት በሀገረ ስብከቱ እየተሠሩ ያሉ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች ጎብኝተዋል፡፡

በተለይም በዝዋይና በሙሁር ገዳም መንፈሳዊ የትምህርት መርሕ መሠረት ባስጀመሩት በወልቂጤ መንበረ ጵጵስና ቅጥር ግቢ ውስጥ እየተሰጠ ያለውን የአብነት ትምህርት ለእንግዶች አሰጎብኝተዋል፡፡

በተጨማሪም በመንበረ ጵጵስናቸው ተሠርተው የተጠናቀቁና እየተሠሩ ያሉ ግዙፍ ልዩ ልዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ተዘዋውረው መመልከታቸውን ተገልጿል፡፡ ከነዚህ መካከልም፡
የመንበረ ጵጵስና ባለ ሁለት ወለል፣ ቤተ ክርስቲያን፣ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የካህናት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ኮሌጅና በርካታ የልማት ሥራዎችን መጎብኝታቸው ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ምንጭ ከሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት የተገኘ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያካሄድ በቆየው ጉባኤ ላይ መግለጫ ሰጠ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 17ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም ድረስ ሲያካሄድ የቆየውን ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል።

ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተክርስቲያንና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል።

መግለጫው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ተሰጥቷል።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከግንቦት 17 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 20 ቀን 2013ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማህበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

 1. የ2013ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት የጉባኤ መክፈቻ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ማለትም፡-
  ❖ ስለ አገር ደህንነትና ስለ ሕዝቦች አንድነት፣
  ❖ ከቄያቸው ስለተፈናቀሉና ለስደት ስለተዳረጉ ወገኖች፣
  ❖ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ስለአሉ አለመግባባቶች የሚያመላክት እና ይህንንም በመግባባት በውይይት በይቅርታ መፍታት እንደሚገባ ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ምሕረት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ በመሆኑ ጉባኤው ተቀብሎ በተግባር ላይ እንዲውል ተስማምቷል፡፡
 2. አገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የጠፋው የሰው ሕይወት የታረዱና ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግሩ ምክንያት የወደመ ንብረት በዓይነትና በቁጥር ተለይቶ በየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
 3. የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥፍራ ስምና እስከዛሬ ተጠብቆ የቆየ ክብሯ እንዲሁም በካህናትና በምዕመናን ላይ እየደረሰ ያለ ሞት፣ ስደት የመሳሰለው ከየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ ሪፖሪት እንዲቀርብ መንግሥትም አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
 4. ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን የነበረውንና የቆየውን ታሪካዊ ሂደት ለመቀየር በዚህም አጋጣሚ የኖረውንና ዓለም የሚያውቀውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል አደባባይና የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች እንዲሁም የአምልኮ ሥፍራዎችን ምክንያት በመፍጠር አንዳንድ ወገኖች የግጭትና የትንኮሳ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡

በመሆኑም ይህ በቤተ ክርስቲያናችን ስም የቆየው የዘመናት ታሪክ አገራዊ ታሪክ ተደርጐ ልዩ ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት ስለሚገባ አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የኖረው የቤተ ክርስቲያኒቱና የአገሪቱ ታሪክ ክብሩ ከነማንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር የበኩሉን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት አሳስቧል፡፡

 1. አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ እንደሚታወቀው ዳር ድንበሯን ጠብቃና አስጠብቃ ያለ ቅኝ ግዛት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በአገር ወዳድ መሪዎቿ አንድነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗ አለም የሚያውቀው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የውጭ አገራት ከሩቅና ከቅርብ ግንባር በመፍጠር በአገራችን ሕልውና ላይ እያደረጉት ያለው ጣልቃ ገብነት፣

❖ አገራዊ የመልማት ፍላጐታችንን ለመግታት
❖ ዳር ድንበራችንን ለመድፈር እያደረጉ ያለውን ሙከራ ጐረቤት አገራት ጭምር በጠላትነት እንዲነሳሱብን እያደረጉ ያለው ቅስቀሳ ተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃውሞአል ሕዝባችንም ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ አገራዊ አንድነቱን በመጠበቅ አገሪቱን ከውጭ ወራሪ በመከላከል አገራዊ ልማትን በማፋጠን የበኩሉን እንዲወጣ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡

 1. አገራችን ኢትዮጵያ በልማት እንድታድግ ሌሎች አገራት ከደረሱበት ደረጃ ለማድረስ በዚህም ዜጐችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማውጣት ታስቦ እየተገነባ ያለው ህዳሴ ግድባችን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተቃረበ እና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነታችን ማሳያ እየሆነ በመምጣቱ አሁንም ለግንባታው ፍጻሜ መላው ኢትዮጵያ እንዲረባረብ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
 2. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ታሪኳ የአብያተ ክርስቲያናትን አፀድ በመትከል አረንጓዴ ልምላሜን በማስፋፋት ጠብቃ የቆየች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መንግሥታችን በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱ ለአየር ጥበቃና በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው አገራዊ ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ በዘንድሮውም የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር መላው ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
 3. ከአንድ ዓመት በፊት በመላው ዓለም ተከስቶ ብዙዎችን ለሕልፈተ ሕይወት የዳረገው ኮቪድ 19 ተላላፊ በሽታ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በመስፋፋቱ ብዙዎች ወገኖቻችን ለሞት እየዳረገ የሚገኝ በመሆኑ መላው ሕዝባችን ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ጊዜ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ በመቀበል ራሱን ከወረርሽኑ እንዲጠብቅ ጉባኤው አሳስቧል፣
 4. በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ያለመጠለያ የሚገኙ እና በዚሁ ተላላፊ በሽታ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖቻችንን በተለመደውና በኖረው የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባሕላችን ከምንግዜው በላይ አሁን ለችግራቸው እንድንደርስላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
 5. አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሽግግር ላይ የምትገኝ በቀጣይም ሕዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎች ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመውን ሰላማዊ መንገድ እንዲከተሉ መላው ሕዝባችንም ለአገርና ለወገን ይጠቅማሉ የሚባሉትን በመምረጥ ሁሉም አካል ውጤቱን በፀጋ በመቀበል ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የምናስመሰክርበት ምርጫ እንዲሆን ጉባኤው የሰላም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
 6. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጐንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነምሕረት በሕገ-ወጥ መንገድ ዶግማና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጣሰ መልኩ ራሳቸውን በራሳቸው ጳጳስና ፓትርያርክ አድርገው የሾሙ፡-
 7. መምህር ሄኖክ ፈንታ
 8. መምህር አባ ኪዳነማርያም
 9. መሪጌታ ሙሉ
  ከግንቦት 19 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወግዘዋል፡፡ የገዳሙንም ሀብትና ንብረት አስረክበው ከገዳሙ እንዲወጡ ተወስኗል፡፡ የዚህ ተባባሪ የነበሩ መነኮሳት ካህናትና ዲያቆናትም የተወገዙ ሲሆን በዚህ የዶግማና የቀኖና ጥሰት ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተሳስተው ድጋፍ ሲሰጡና ሲከተሏቸው የነበሩ ምእመናን ንስሐ እየገቡ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡
 10. በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው፡-

❖ የርስ በርስ አለመግባባት እንዲቆም ፣
❖ ሞትና ስደት እንዲያበቃ ፣
❖ ተላላፊ በሽታ ከምድራችን ጠፍቶ ሰዎች በጤንነት እንዲኖሩ ፣
❖ መጪው አገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ጨዋነት በአንድነትና በሰላም እንዲጠናቀቅ ፣
ለዚሁ ሁሉን ቻይና ሁሉን አድራጊ የሰላም አምላክ እግዚአብሔር አገራችንና ሕዝባችንን በሰላምና በምሕረቱ እንዲጐበኝ ሁላችንንም ይቅር እንዲለን ከአሁን ጀምሮ በግልም ሆነ በማህበር ጸሎት በማድረግና ችግረኞችን በመርዳት እንድንተባበር ሆኖ ከምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2013ዓ.ም. ድረስ በመላው አገራችንና በውጭም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 23 ለስድስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቆ በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይጠብቅ፡፡
ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ዋለ

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የግንቦት 21 ክብረ በዓል በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል

ብፁዕነታቸው እመቤታችን “ናሁ እምይእዜሰ ያስተበጽኡኒ ኲሉ ትውልድ ፤” እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤”(ሉቃ 1:48)” እንዳለች ቃሉን እየተተገበረ ነው፤ የቅ/ድንግል ማርያም ማንነትና የማን እናት መሆኗን ባወቁ ሁሉም እስከ መጨረሻ ስትከበር ትኖራለች ብለዋል።

በዕለቱ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በሰሜን አመሪካ የካልፎርንያ አከባቢ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ትምህርት ተሰጥተዋል።

ብፁዕነታቸው አይ ይእቲ ዛቲ እንተ ታስተርኢ፤ ይህች ከሩቅ የምትታይ ማናት በሚል መነሻነት ያስተማሩ ሲሆን ይህች ከሩቅ የምትታይ ማናት ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሆን” በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ።”( ዘፍ 3:15) ተብሎ የተነገረ ቃል የምትፈጽም የጠላታችን ራስ ቀጥቅጦ ሞትን አሸንፎ ሕይወትን የሰጠን ጌታችን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን አብራርተዋል።

በመርሐ ግብሩ በካቴድራሉ ሊቃውንት “አይ ይእቲ ዛቲ እንተ ታስተርኢ እምርሑቅ ከመ ማኅቶት ብርህት ከመ ፀሐይ፣ ሙሴኒ ርእያ ሃገር ቅድስት ደብረ ምጥማቅ፣ እዝራኒ ተናገራ ዘመራ ዳዊት” የሚል፣ በሰንበት ት/ት ቤት ወጣቶች ደግሞ “ክበበ ገጻ ከመ ወርሕ፣ ወአዕይንቲሃ ከመ ኮከበ ጽባሕ፣ ወቆማ ከመ በቀልት ለማርያም ድንግል” በሚል ዕለቱን በተመለከተ ያሬዳዊ ዜማ የቀረበ ሲሆን በመርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፣የካቴድራሉ የአስተዳደር ሠራተኞችና በርከት ያሉ ምእመናን ተገኝቷል።

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

“በዛሬው ዕለት ያሳያችሁን ተግባር ያላችሁን መንፈሳዊ ጥንካሬና ክርስቲያናዊ አንድነት የሚያሳይ ነው“….ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

ብፁዕነታቸው ይህንን መልእክት ያስተላለፉት በ2000 ዓ.ም የግንባታ ሥራው ተጀምሮ ከ13 ዓመታት የግንባታ ቆይታ በኃላ ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም የቦሌ ገርጂ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንን በጸሎተ ቡራኬ በመረቁ ወቅት ነው፡፡

የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ይህ ድንቅ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ዛሬ በቦታው ተገኝተን ስንባርክና ስንመርቅ ከእናንተ ያልተናነሰ ደስታ ተሰምቶናል፡ምክንያቱም ከበርካታ ዓመታት ከፍተኛ ውጣ ውረድ በኀላ ለስኬት የደረሰ ነው ብለዋል፡፡

በደብሩ አስተዳዳሪ በኩል ለተነሡት ጥያቄዎችም አሠራሩን ጠብቀንና በሚገባ ተነጋግረን መፍትሔ እንሰጣለን በማለት አረጋግጠዋል፡፡

አያይዘውም በዛሬው ዕለት ያሳያችሁን ተግባር ያላችሁን መንፈሳዊ ጥንካሬና ክርስቲያናዊ አንድነት የሚያሳይ ነው፡ወደፊትም የቀሩ የልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ፡ ስብከተ ወንጌልን በማስፋት፡ የአብነት ት/ቤትና የሰ/ት/ቤትን በማጠናከርና የሰበካ ጉባኤን በማደራጀት እንዲደግሙትም አሳሰበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ላለፉት 13 ዓመታት የምእመናንን አደራ ተሸክማችሁ በብዙ ድካም የወጣችሁና የወረዳችሁ በገንዘባችሁ፡በዕውቀታችሁ፡በጸሎትና በሙያችሁ የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ፡ ብለው የደከሙትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

የዛሬው የቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ምርቃት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ከተሠሩ ትላልቅ ሥራዎች መካከል አንዱ ትልቅ ስኬታችን ነው፡ምክንያቱም የብፁዕ አባታችን መመሪያና ጸሎት ፍሬ አፍርቶ ታይቷልና ነው ብለዋል፡፡

የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ ይህ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ባለፉት ጊዜያት ተጠናቆ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከፍ ባለ ሰገነት ላይ ብትመሰገን ደስ ባለን ነበር፡ ነገር ግን ሰይጣን በብዙ ትግል ሲያዘገየን ቆይቶ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲፈጸም ለዛሬው ክብር በቅተናልና እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

በዚህ ታላቅ ሥራ ላይ የተሳተፉትን ባለድርሻ አካላት፡ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን የባረኩትን ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት አመስግነዋል፡፡

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግዙፍ ከመሆኑም ባሻገር ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚፈጸምበት ደብር ስለሆነ የካቴድራ ስያሜ እንዲሰጥላቸውና ወደ ቅጥረ ቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ ዋና በር ስለሌለው እንዲፈቀድልን ሲሉ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አቅርበዋል፡፡

በምረቃ መርሐግብሩ ላይ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤ/ክ ሥራ አስኪያጅ መ/ብ ሩፋኤል የማነ ብርሃን፡የጠቅላይ ቤተክህነት፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የክፍላተ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ ገዳማትናአድባራት አስተዳዳሪዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በርካታ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

በማኅደረ መለኮት ወይብላ ቅ/ ድንግል ማርያም እና ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ የተጠናቀቀ አዲሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጸሎትና ቡራኬ ተባረከ

በማኅደረ መለኮት ወይብላ ቅ/ ድንግል ማርያም እና ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በ2005 ዓ/ም የመሠረተ ድንጋዩ ተጥሎ ለ8 ዓመታት በግንባታ ላይ የቆየ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በዛሬ ዕለት በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተባርኳል።

በክቡር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪጅ መ/ር ኣካለ ወልድ ተሰማ ጋባዥነት ለምእመናኑ ቃለ ቡራኬና ትምህርት የሰጡት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ” ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።”(መዝ 118:20) በሚል መነሻነት ሰፋ ያለ ዕለቱን በተመለከተ ትምህርት ሰጥተዋል።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በትምህርታቸው ቤተ ክርስቲያን ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙበት ቅዱስ ቦታ መሆኑን በማስረዳት ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ቤት ሆኖ በእምነት፥ በሃይማኖት በቀኖና እንዲሁም በሥርዓት አንድ የሆኑት ምእመናን በአንድነት የሚያመልኩበት ቅዱስ ስፍራ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ቤተ ክርስቲያን ሰዎች በዘር፣ በፆታና በአከባቢ ሳንለያይ በአንድነትና በእኩልነት የምንገለገልበት ቅዱስ ስፍራ መሆኑን አብራርተዋል።

ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን ፍቅርና ሰላም የሚሰበክባት የጽድቅ መግቢያ ናት ካሉ በኋላ ከዛሬ ጀምሮ ይህ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ማኅደረ መለኮት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተብሎ እደሚጠራም ለምእመናኑ አስረድተዋል።

በመጨረሻም በዛሬ ዕለት ምእመና ፈጣሪያቸውን የሚያመልኩበትና ትምህርተ ሃይማኖት የሚማሩበት አንድ ትልቅ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለሀገረ ስብከታችን ስለ ብሎኛል ሲሉ በምእመናኑ ፊት ደስታቸውን በመግለጽ ምእመናን ቤተ ክርስቲያኒቱ የጽድቅ ደጅ መሆኗን ተረድተው ወደ እሷ እንዲገሰግሱ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በምርቃቱ ስነ ሥርዓት በሊቃውንትና በሰንበት ት/ት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዜማና ቅኔ የቀረበ ሲሆን በመርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ፣ የሀገረ ስብከቱ የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅና ክፍል ኃላፊዎች፣ የቤተ ክርስቲያኑ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና በርከት ያሉ ምእመናን ተገኝቷል።

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ

“ምእመናን ልጆቻችን በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጡ በጣም መጠንቀቅ አለብን” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ምእመናን ልጆቻችን በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጡ በጣም መጠንቀቅ አለብን ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ገለጹ።

ቅዱስነታቸው ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት በዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን፣ በሕዝባችንና በደመ ክርስቶስ በተቀደሱ ክርስቲያን ልጆቻችን ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሰተ ስለሆነ ከምንም ጊዜ በላይ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀን ልንጸልይ፣ ልናለቅስና ልናዝን ይገባናል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህንን የፈተና ጊዜ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታ የምናልፈው ከሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠባሳ ታሪክ መሆኑ አይቀርም፤ በእግዚአብሔርም ተጠያቂነትን ማስከተሉ አይቀርም ብለዋል።

ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች፣ ምእመናንና ምእመናት ፈተና ላይ ሲወድቁና መከራ ሲጸናባቸው ቅዱስ ሲኖዶስን በቀጥታ የሚመለከተው ስለሆነ የመፍትሔው አካል ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል በማለት ገልጸዋል።

ይህ ጉባኤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጎዱ ለሚገኙት ምእመናንና ምእመናት እንደዚሁም በአጠቃላይ ያለ ፍትሕ እየተጎዱ ለሚገኙ ሰዎች መፍትሔ አምጪ አካል ሆኖ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ብለዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ በመግለጫቸው የአሁኑ ጊዜ ከሌላው ጊዜ ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የችግሩ ክብደትና ውስብስብነት ማየሉ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

አያይዘውም የችግሩ ክብደቱን አይተን የምንሸሸው ሳይሆን የቤተክርስቲያናችን የውስጥ አቅምን በማየት የምእመናንን ትብብርና አገዛ በመጠየቅ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትንና በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከራውንና ፈተናውን መቋቋም ይኖርብናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለመንግስት፣ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት የአደራ መልእክት “የሁሉም ነገር መሠረትና የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ሲባል አስፈላጊ የሆነ ዋጋ መክፈል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን” አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም ዋስትና ያለው ሰላም በሀገራችን ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙርያ ተሰባስበው መወያየት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነትን መፈጸም ሲችሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

የአዲስ አበባ ከተማ ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት በቦሌ ደ/ ሳሌም ካቴድራል መድኃኔዓለም ቤ/ክርስቲያን በጥምቀተ ባሕር ለታቦት ማደሪያ የሚሆን 41ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የቦታ ካርታ ለአዲስ አበባ ሀ/ሰብከት ጽ/ቤት ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አስረከበ

የአዲስ አበባ ከተማ ልማት አስተዳደር ተወካዮች በቦሌ ክ/ከተማ ሥር የሚገኘው የቦሌ ደብረ ሳሌም ካቴድራል መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ጥምቀተ ባሕር ለታቦት ማደሪያ የሚሆን 41 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የቦታ ካርታ በሀገረ ስብከታቸው ጽ/ቤት ተገኝተው ለቡፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አስረክበዋል።

ብፁዕነታቸው የከተማ ልማት አስተዳደር ተወካዮችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩአቸው ሲሆን ቦታውን ከታቦት ማደሪያነቱ በተጨማሪ ለልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።

የከተማ ልማት አስተዳደሩ የቦታው ፕላን አሰርቶ ለማስረክብ ቃል መግባቱን ለማዎቅ ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የመንገድ ሥራ የውኃ ፍሳሽና ተዛማጅ ሥራዎችን የከተማ ልማቱ ሰርቶ እንደሚያስረክብ ተወካዮቹ ለብፁነታቸው ገልጸውላቸዋል ፡፡

ለዚህ ውጤታማ ሥራ ከፍተኛውን ሚና የተወጡት ብፁዕነታቸው በሰጡት በሳል አመራርና መመሪያ ሰጭነት የቦሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን የተሰጠውን መመሪያ በመቀበል በተግባር ላይ በማዋል የተገኘው ውጤት እንዲሳካ አድርገዋል ተብሏል ፡፡

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪጅ መ/ር ኣካለ ወልድ ተሰማም በጉዳዩ ላይ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል ፡፡

በመጨረሻም በውይይቱ የተደረሰበትን የካርታ ውል ስምምነት በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅና በቦሌ ክ/ ከተማ ቤ/ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ከከተማ ልማቱ አስተዳደር ጋር የፊርማ ሥነ ስርዓት ተፈጽሟል፡፡

ዘጋቢ መ/ኪደ ዜናዊ
መረጃው ከሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት የተገኘነው

በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም በልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፍ ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎች ተመረቁ

በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም በብሉይ ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳን፣ በሊቃውንት፣ በቅኔ፣ በድጓ፣ በቅዳሴ፣ በአቋቋምና በኆኅተ ስብከት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች በዛሬ ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ፣ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት በጽረሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተመርቀዋል::

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸው “ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” እንዳለው ቅዱስ ወንጌሉ ለሕዝብ ሁሉ ብርሃን ልትሆኑ ይገባል፤እናንተ እንደ ገበሬ ናችሁ፤ ገበሬ እርሻ አርሶ አለስልሶ፣ ዘር ተሸክሞ በክረምትና በዝናም እንደሚዘራ ሁሉ እናንተም ያገኛችሁትን የእግዚአብሔር ቃል ዘር ተሸክማችሁ በሕዝቡ ልብ እርሻ ላይ እንድትዘሩ ያስፈልጋል ብለዋል።

አያይዘውም ብፁዕነታቸው ሑሩ ወመሀሩ ውስተ ኲሉ ዓለም ወስብኩ ወንገለ ለኲሉ ፍጥረት ብሎ ሐዋርያትን ወንጌል እንዲሰብኩ እስከ ዓለም ዳርቻ እንደላካቸው ሁሉ እናንተም ከዛሬዋ ቀን ጀምሮ ወደ ሕዝብ ሁሉ ለመሄድ እንደ ሐዋርያት ተልካቹኋል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት አስተላልፈዋል።

የደቀ መዛሙርቱ የሽልማት ሥነ-ስርዓት ካለቀ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ” መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” እንዳለው ጌታችን በአሁን ጊዜም ቤተ ክርስቲያናችን የአገልጋዮች እጥረት ስላለባት እናንተ ይህን ክፍተት በመዝጋት አገልግሎቱን ታፋጥኑት ዘንድ ወደ መከሩ ተልካቹኋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በአሁኑ ጊዜ የሠለጠነ ዘመን በመሆኑ እየሠራን የምንማርበት ትምህርት ቤት ተከፍቶልን እየተማርን ነው፤ እናንተም የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች ስለ ሆናችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

በመጨረሻም ዕውቀቱን በሚገባ በማስፋፋት ሃይማኖታችን በአግባቡ መጠበቅ አለብን ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውንና ቡራኬአቸውን ለተመራቂ ደቀ መዛሙርት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ