6

የ2005ዓ.ም የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

                                  በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

6

በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 የሚከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሪነት ከ13 ታቦታት በላይ በሚያድሩበት በጃን ሜዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡ የዓመቱ ተረኛ የሆነው የገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ ‹‹ ተሰሃልከ እግዚኦ ምደረከ ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ እም ሰማያት ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም››በማለት ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል፡፡ በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ዐበይት በዓላት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ይህም በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ፤ በማእከለ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ከዋዜማው ከጥር 10 ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ፤ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን መሠረት በማረድግ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ታቦታት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ በካህናትና ዲያቆናት፤ እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራንና ምዕመናን በዝማሬ በመታጀብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ታቦት ማደሪያ በማምራት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሔድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ማምራቱን ያበስራሉ፡፡ ‹‹ያን ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ ዮሐንስም በዮርዳኖሰ ወንዝ አጠመቀው›› እንዲል፡፡/ማቴ.3፡1/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስራቿን መድኅነ ዓለም ክርስቶስን ለዓለም የምትሰብክበት፣ ከእርሱም ያገኘችውን፣ ይህም ዓለም እንደሚሰጠው ያልሆነውን፣ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ትሕትና ለዓለሙ ትሰብክበታለች፡፡ እንዲሁም ለሀገራችን በጎ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ተደንቀው የሚያዩትና በመስተንግዶው የሚደመሙበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ በዓሉን በልዩ ትኩረት ታከብራለች፡፡

ለዚህ በዓል አከባበር ቤተክርስቲያን ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ታቦታት በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲመለሱ ጉልህ ሚናዋን ትወጣለች፡፡ በዚህ መሠረት በየአጥቢያው የሚገኙ ወጣቶች ከክብረ በዓሉ ቀደም ብሎ በመሰብሰብ ቅዱሳት ሥዕላትን በታቦታት ማረፊያዎች በማዘጋጀት፣ በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ጨርቆችን /ባነሮችን/፤ የኢትዮጵያ ባንዲራን በየአብያተ ክርስቲያናቱ አደባባዮች በመስቀል፣ የቤተክርስቲያናትን ቅጥርና አስፋልት በማጽዳት ፤ለታቦት ክብርን ለመስጠት ምንጣፎችን በማንጠፍ በዓሉን ያደምቁታል፡፡ ምእመናን ከየቤታቸው ለበዓሉ በሚገባው ልብስ አሸብረቀው ወጥተዋል፡፡ እናቶቻችን ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰሙትን የሊቃውንት አባቶቻችን ወረብ ተከትልው፣ የታቦታቱን መውጣት በመጠባበቅ እልልታቸውን ያሰማሉ፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ዝግጅቶቻቸውን አጠናቅዋል፣ የዝማሬ ልብሳቸውን ለብሰዋል፡፡ምእመናኑም ከየመሥሪያ ቤታቸው በር ላይ ቆሞው የታቦታትን ማለፍ እያዩና በእልልታ እና በጭብጨባ እያጀቡ በእነርሱም መባረክን ዓይናቸው ተስፋ እያደረገች ታቦታቱ የሚመጡበትን አቅጣጫ ያማትራሉ፡፡ ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር በተለይም በጃንሜዳ ከየአድባራቱ አስራ ሦስት ታቦታት በአንድነት የሚገኙበት በመሆኑ ህዝቡን ለመባረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ፤በመዘምራንና ምዕመናን በመታጀብ ጉዞ የተጀመረ ሲሆን አመሻሽ ላይ ጃን ሜዳ ሊደርሱ ችለዋል፡፡

የየሰንበት ት/ቤቶቹ መዘምራን ፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዜማ እየዘመሩ ፤ምዕመናን በዕልልታና በሸብሸባ ታቦታቱን በማጀብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በመቀጠልም እለቱን በማስመልከት በአቃቤ መንበረ ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ቸርነት ሰፊ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዑለ ባሕሪውን ዝቅ አድርጎ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ዮሐንስ ወዳለበት ቦታ ለመጠመቅ መጥቷል፡፡

ዮሐንስን አጥምቀኝ ማለቱ ለእኛ አብነት ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ለመመሥረት ሲል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዶ አጥምቆት ቢሆን ኖሮ ምእመናን ቀሳውስቱን እቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥመቁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሔድም ባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሌላት እንዳትሆን ሥርዓትን ለማስተማር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር፤ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ” ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ጥምቀትን በየዓመቱ የምናከብረው እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፤ በዝናብ አብቅሎ በጸሐይ አብስሎ የሚመግብ እርሱ ስለሆነ፡፡ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነውና ከሦስቱ አካል አንዱ አካል መሆኑን በአደባባይ የገለጠበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን በዓል ነው” በማለት እለቱን በማስመልከት የገለጹ ሲሆን በብፁዕነታቸው ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

5.6

የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ምሽቱን በመቀጠል ትምህርት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የተሰጠ ሲሆን በእለቱ ተረኛ በሆነው በገነተ ኢየሱስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀውንትና ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

የለሊቱ ሥርዓተ ማህሌትና ሥርዓተ ቅዳሴ በባለተረኛው በገነተ ኢየሱስ ካህናትና መዘምራን ተከናውኗል፡፡ ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ክቡር አቶ ታደሰ በንቲ፤በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር፤ጥሪ የተደረገላአቸው እንግዶች፤ አገር ጎብኚዎች፤ የየአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን በማስመለከት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ መርሐ ግብሩ ተጀመረ፡፡ ጸበሉም ተባርኮ ለምእመናን እንዲዳረስ ተደርጓል፡፡ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ባሰተላለፉት ትምህርትም “በዓላችን የሰላማችን ፤የአንድነታችን ምልክት ነው፡፡ መሠረቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ አደባባይ ተገኝቶ የእኛን ችግር ያስወገደበት ፤ ነፃነታችንን ያገኘንበት፤ የኀጢዓት ደብዳቤያችን የተቀደደበት፤ዮርዳኖስን ተሻግረን በአንድነት ድኅነት መንግስተ ሰማያትን ያየንበት እለት ነው፡፡ ዛሬ በአንድነት በዘመነ ፍዳ የተዘጋው ጆሯችን የአብ ድምጽ የሰማበት ቀን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ ታቦታቱ ወደየ ማረፊያ ቦታቻው በክብርና በሰላም ተመልሰዋል፡፡

                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

5.3

ዓመታዊው የዓጋዓዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

                            እንኳን ለአብርሃሙ ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

                                                               በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

5.3

‹‹እመ እግዚአብሔር ኢሐነፀ ቤተ ከንቶ ይፃምው እለ የሃንፁ›› ‹‹እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ግንበኞቹ በከንቱ ይደክማሉ›› መዝ 126፡1 ይህን የታላቁን ነቢይ ቃል ለመነሻነት የተመረጠው ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በዓለ ንግሥን ምክንያት ለመግለፅ ነው፡፡ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዳዊት ምንም እንኳ ይህን ኃይለ ቃል ከጊዜ በኋላ የፃፈው ቢሆንም የዚህን ጽሑፍ ሐሳብ የሚያንፀባርቀው ቀደም ሲል በዘመነ ህገ ልቡና የተፈፀመ ነበረ በዘፍ1ዐ፡32 ላይ ‹‹የኖኀ የልጆቹ ነገዶች እንደየ ትውልዳቸው በየህዝባቸው እነዚህ ናቸው፤ አህዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከነዚህ ተከፋፈሉ››፡፡ ይልና በተለይ በዘፍ 11፡1 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት ደግሞ ‹‹ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋ ንግግር ነበረች›› ብሎ የሰናኦርን ግንብ መገንባትና መፍረስን ያትታል፡፡ በአጭሩ የዚህ ኃይለ ቃል ጭብጥ ሐሳብ፡- የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ለመቃወም ሲሉ ታላቅ ግንብ እንደገነቡና እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ታላቅ ግንብ እንደ አፈራረሰባቸው ነው የሚያብራራው፡፡ ይህን ግንብ ለመገንባት 43 ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡

ይህ ግንብ በአሁኑ ዘመን በነዱባይ ከተገነቡት ታላላቅ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እንደሚበልጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መምህራን ይናገራሉ፡፡ ይህንን ህንፃ ሲገነቡ የነበሩ ሰዎች ቀደም ሲል እንደተገለፀው ለትምክህትና እግዚአብሔርን ለመቃወም ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ ትምክህትንና ራሱ እግዚአብሔርን የሚቃወም ሰው አይወድም ዘዳግ 5÷ 10 አስመ አነ አምላክ ቀናኢ እኔ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነኝ ሲል በሙሴ አፍ እንዳስተማረ የሚቃወሙትን የቃወማቸዋል ፡፡እግዚአብሔር በአምላክነቱ ቀናኢ ነው፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የሚሠሩት ሥራ (ህንፃ) ስኬታማ አይሆንምና ብትንትኑ ወጣ፤ ፈራረሰ፡፡ መ/ቅዱሱ እንደ ነገረን አንድ የነበረ የሰዎች ቋንቋ በሰዎቹ ቁጥር ልክ ሆነ፡፡ ይህም የኃጢአት ውጤት ነው፡፡ አዳም ከመበደሉ በፊት ሰው ከእንስሳትና አራዊት ከጠቅላላ ፍጥረታት ሁሉ በቋንቋ ይግባባ እንደ ነበረ አበው ያስተምራሉ አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ግን ከፍጥረታት ጋር መግባባት ተሳነው፡፡ አሁን ደግሞ በነዚህ ኃጢአት ምክንያት ሰውና ሰው መግባባት አቃታቸው፡፡ ሰው ኃጢአት ሲሰራ ከራሱ ከልቡናው ጋር ይጣላል፤ መግባባት ያቅተዋል፡፡ ሰዎች የሚሠሯአቸው ሥራዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ካስፈለገ እግዚአብሔር እንዲጨመርበት ማድረግ ነው፤ እግዚአብሔር ካልተጨመረበት ግን ነቢዩ እንደነገረን ልፋቱ ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ታሪክ በዘመነ ህገ ልቡና የተፈፀመ ሲሆን ሌላ ተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን ከዚሁ ጋር አብራ የምታከብረው ታላቁ የሐዲሱ ኪዳን የልደት በዓል ነው፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ በ1 ዮሐ 3÷8 ‹‹በእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሥዓር ግብሮ ለጋኔን›› ‹‹ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ›› ብሎ እንደ ነገረን የእግዚአብሔር ልጅ ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን የገነባው የሐጢአትን ግንብ ለማፍረስ ሰው የሆነበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ሠራዊተ ዲያብሎስ ያዘኑበት የተዋረዱበት ሲሆን የሰው ልጆችና መላእክት ደግሞ ያመሰገኑበትና የዘመሩበት ጊዜ (ወቅት) ነው፡፡ ታላቁ ሊቀ ቅዱስ ቄርሎስ ‹‹ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን›› ‹‹እነሆ ዛሬ መላእክትና ሰዎች በእምነት ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመስገን አንድ መንጋ ወይም አንድ ማኀበር ሆኑ›› ሲል ይገልፀዋል ታላቁ የኢትዮጵያውያን መመኪያ የሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በጣዕመ ዜማ ይህን ያብራራዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ሰዎች 55ዐዐ ዘመን በዲያብሎስ ሥር ተገዝተው(በዲያብሎስ ግዛት)ስለነበሩ በዚሁ በጌታ ልደት ከዚህ አስቀያሚ ከሆነው የዲያብሎስ ግዛት ነፃ መውጣታቸውን ያረጋገጡበት ቀን ስለሆነ ለአምላካቸው፣ ለመድኃኒታቸው ታላቅ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡ መላእክትም ደግሞ በሰው ሞት አዝነውና ተክዘው ነበር አሁን ግን ሰው ድህነተ፤ ሥጋ ድህነተ ነፍስን ስላገኘ ደስ ብሏቸው አመስግነዋል ዘምረዋል፡፡ መላእክት ሰዎች በሥጋቸውም ይሁን በነፍሳቸው እንዳይጎዱ ወደ ፈጣሪ የሚለምኑ፣ የሚማፀኑ ናቸው፡፡ በዘካ 1፡12 ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቆጣሃቸው ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው›› አለ ይላል ይህ የመላእክትን ምልጃ የሚያመላክት ነው፡፡

5.5

ስለዚህ መላእክት ለሰው ድህንነት በየጊዜው ይፀልያሉ፤ ይማልዳሉ፡፡ ሰው ሲድን ደግሞ ደስ ብሏቸው ይዘምራሉ ያመሰግናሉ ይህን ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ በሉቃ2÷12 ድንገትም የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋራ ነበሩ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ፤ሰላምም በምድር ለስውም በጎ ፈቃድ ወይም እርቅ ተጀመረ አሉ ሲል የመዘገበልን ፡፡ አሁን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው ‹‹ዮም መላእክት ይየብቡ ወሊቃነ መላእክት ይዜምሩ ኃይላት ይየብቡ እስመ መድኀን መጽአ ውስተ ዓለም ለቢሶ ሥጋነ›› ‹እነሆ መላእክት ሊቃነ መላእክት ለአምላካቸው ለፈጣሪያቸው፣ ምስጋናን ያቀርባሉ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ለመሆን የሰውን ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም መጥቷልና በተጨማሪም ለኛ ስለ ተወለደልን ሥልጣን ያላቸው መላእክት ይቀድሱታል፤ ሱራፌልም እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ኪሩቤልም ውዳሴን ያቀርባሉ፤ ዛሬ ከኛ የጥንቱ መርገም ተወግዷል፤ ዛሬ ኃጢአታችን ተተወልን ወዘተ….. በማለት ያመሰገኑትን ምስጋና ይቀጥላል፡፡ በነዚህ ሁለቱ ታሪኮች ተመሳሳይ የሆኑ ድርጊቶችን እግዚአብሔር አከናውኗል፡፡

1. ሰው የገነባው ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አእምሮን የሰጣቸው መልካም ነገርን እንዲሰሩበትና መልካም ነገርን እንዲያስቡበት እንጂ ለመጥፎ አልነበረም እነሱ ግን ይህንን አእምሮ ለመጥፎ ነገር ያውሉታል ሰዎች በአእምሮአቸው መጥፎ ሥራ ቢሰሩ የሚጎዱ ራሳቸው ፤ጥሩ ሥራ ቢሠሩ የሚጠቀሙ ራሳቸው ነቸው፡፡

2. ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን የገነባውን የኃጢአት ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ ታሪኮች የምንማረው ፡-

1. የሰው ልጅ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም፣ ምንም ነገር መሥራት እንደማይችል ነው ሰው ግንብን ቢገነባ፣ መኪና ቢገዛ፣ ቢነግድ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

2. አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን በብዙ ውጣውረድ የገነባውን የኃጢአት ግንብ በልደቱ (ሰው ሆኖ) ንዶታል፡፡ ነገር ግን ይህ የተናደውን ግንብ እንደገና ኃጢአትን በመስራት እንዳንገነባው ወይም እንዳንጠግነው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ዲያብሎስ ይህንን የፈረሰውን የኃጢአት ግንብ ለማስጠገን እየወጣና እየወረደ ነው ያለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በ1ኛ መልእክቱ 5÷8 በመጠን ነሩ ነቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና ሲል የሚገልፀው፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ እንድንኖር እጅግ አስፈላጊ ነው ይህንንም እንድናደርግ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ዘተሰሃለነ ወገብረ መድኃኒተ ለሕዝበ ዚአሁ፡፡ ስለዚህ በዓለ ቅድስት ሥላሴ ጥር 7 ቀን ምን ተደረገ? ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖኅ ልጆች ወልደው ተዋልደው ብዙዎች ሆኑ ባቢሎን የነበሩት በሰናዖር ምድር ሰፊ ሜዳ አግኝተው ሳንሞት ስም ማስጠሪያ ግንብ እንገንባ ብለው መክረው ታላቅ ግንብ ገነቡ፡፡ አለቃቸውም ናምሩድ ይባላል፡፡ ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸው እነርሱን ወግተን ሞትን እናርቅ አላቸው፡፡ እነርሱም ከግንቡ ላይ ሆነው ጦር እየሰበቁ ይወረውሩ ጀመር፡፡ ሰይጣን በደመና በምትሀት ጦሩን ደም እየቀባ ይልክላቸዋል እነርሱም ደሙን እያዩ አሁን አብን ወጋነው አሁን ወልድን ወጋነው ይሉ ጀመር፡፡ ሥላሴ ምንም እንኳን ምህረታቸው የበዛ ቢሆንም ባቢሎናዊያን ዲያቢሎስ ስለሰለጠነባቸው ቋንቋቸውን ለያዩባቸው ከዚያም ውሃ ሲለው ጭቃ፣ ጭቃ ሲለው ደንጊያ የሚያቀብለው ሆነ፡፡ እንዲህ የማይግባቡ ቢሆኑ ተበታትነዋል፡፡ ባለማስተዋል የሰሩትም ሕንፃ ነፋስ ጠራርጎ አጥፍቶታል፡፡ ዘፍ.11 1-9 በዘመነ አብርሃምም የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ወንድ ለወንድ እስከ መጋባት ድረስ ኃጢአት ሰሩ እግዚአብሔርንም በደሉ፡፡ የአብርሃም የወንድም ልጅ ሎጥ በዚያ ይኖር ነበር፡፡ ሊያድኑት ቢሹ ሁለቱን መላእክት ልከው እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን አጠፋለሁ ብሏልና ሚስትህንና ልጆችህን ይዘህ ወደ ዞዓር ሂድ ስትሄድም ወደ ኋላ ዞረህ አትመልከት አሉት፡፡ ሎጥም ማልዶ ተነስቶ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ከከተማ ወጣ፡፡ ሰዶምና ገሞራም ባህረ እሳት ሆኑ፡፡ የሎጥም ሚስት ወይኔ ሀገሬ ብላ መለስ ብትል የጨው ሀውልት ሆና ቀርታለች፡፡ ዘፍ.19 1-29 ይህ የተደረገው በወርኀ የካቲት እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡ፍሬ ነገሩ ግን ይህን ያደረጉት ቅድስት ሥላሴ እንደመሆናቸው በዚህ ዕለት ይዘከራል ሁል ጊዜ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል ፡፡በመሆኑም በዘንድሮው ዓመትም እንደተለመደው በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በታላቁ ካቴደራል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከብሯል፡፡በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤በፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ፤በፁዕ አቡነ ማቲያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ስምኦን የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ክቡር ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ በላይ፤የካትድራሉ ሰበካጉባኤ አባላትና መላው ማህበረ ካህናት እንዲሁም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝበ ክርስቲያን በበዓሉ ላይ ተገኝተው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡

5.1

የምዕራብ፤የምስራቅና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ስለጥምቀት በዓል አከባበርና አጠቃላይ ስለስራ ሁኔታ ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ጋር የውይይት መርሃ ግብር ተካሄደ

                                                           በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

5.1
ክቡር መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ስብሰባውን ሲመሩ

ቀደም ሲል የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በታኅሣሥ 26/05 ዓ.ም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ስብሰባ መካሄዱንና ወሳኝና ወቅታዊ የሆኑ መመሪዎች እንደተላለፉ በወቅቱ በድህረ ገፃችን ላይ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ከሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀጥሎ ጥር 4/05/05 ዓ.ም ሰብሰባ ያካሄደው የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሲሆን በስብሰባው ላይ ክቡር መልአከ ፅዮን አባ ሕሩይ ወንዲፍራው የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የክፍል ሃላፊዎቹና ሠራተኞች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፤የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞች፤ ሰባኪያነ ወንጌልና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፍ ሃላፊዎች ተኝተዋል፡፡የስብሰባው ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ስለ ጥምቅት በዓል አከባባር ዙሪያ የተመለከተ ሲሆን ከበዓሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ነገሮች ማለትም ሕገ ወጥ ልመና እና ንግድ፤መዋቅሩንና ሥርዓቱን ያልጠበቀ አሠራርና የመሳሰሉት ተነስተው ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ክቡር መልአከ ፅዮን አባ ሕሩይ ወንዲፍራው የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ሀገረ ስብከቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ብዙ ሥራ መሠራቱን ገልፀው የደረሱበትን ደረጃ ለተሰብሳቢዎች የገለፁ ሲሆን ለወደፊቱም የቤተ ክርስቲኒቷን ሕግና ሥርዓት ለማሰከበር ግንባር ቀደም ሆነው እንደሚሠሩ ጠቁመው በተቻላቸው መጠን የሀገረ ስብከቱን አሰራር ዘመናዊ ለማድረግ ሌት ተቀን እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡ተሰብሳቢዎቹ በበኩላቸው በስብሰባው እጅግ መደሰታቸውን ገልፀው ከስብሰባው ብዙ ግብአት ማግኘታቸውን ገልፀው የሀገረ ስብከቱና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከሀገረ ስብከቱ ጋር እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩ ቃል ገበተዋል፡፡በመጨረሻም ከተሰብሳቢዎች ለተነሱት ገንቢ ጥቆማዎችና አሰተያየቶች በክቡር መልአከ ፅዮን አባ ሕሩይ ወንዲፍራው አማካኝነት በቂ ማብራሪያና ማጠቃልያ ተሰጥቶ ስብሰባው ተጠናቅቋል፡፡ በተመሳሳይ ዜና የምስራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ6/05/05ዓ.ም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ስብሰባ ሰበሰባ የተካሄደ ሲሆን ክቡር ሊቀ ኅሩያን ሰርፀን ጨምሮ የሚመለከታቸው የምስራቅ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እንዲሁም የምስራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞች፤ ሰባኪያነ ወንጌልና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፍ ሃላፊዎች የስብሰባው ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡በስብሰባው ላይ ለተገኙት ታዳሚዎች በክቡር ሊቀ ኅሩያን ሰርፀን አማካኝነት ስለ ጥምቀት በዓል አከባባር ዙሪያን እና የጥምቀት በዓል ለቤተ ክርስቲያናችን ብሎም ለሃገራችን መልካም ገፅታ ልዩ መሆኑን ገልው ሁሉም በተሰለፉበት መስክ የኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡አያይዘውም ሀገረ ስብከቱ ከመቸውም በላይ የተሻለ ሥራ እንደሚቺል ጠቁመው አድባራቱና ገዳማቱ የሚጠበቅበቸውን ፐርሰንት በወቅቱና በሰዓቱ በክፈል ሀገረ ስብከቱን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡በመቀጠልም ከተሰብሳቢዎቹ መካከል የእÓዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ፤የደ/ስ/ ቅ/እስጢፋስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪና ፣ የመሪ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በእኛ በኩል በተቻለ መጠን የጥምቀት በዓል እየተዘጋጀንበት እንገኛለን፣ ከፖሊስ ሠራዊትም ጋር ጸጥታዉ ምን መሆን እንዳለበት እየተነጋገርንበት ነዉ ፣ ከሰ/ት/ቤት ወጣቶች እና ከአከባቢ ማህበረ ሰብ በዓሉ እንዴት ማክበር እንደሚባን ተነጋግረንበታል፣ እነርሱም ከአሁን በፊት እንዳከበሩት ሁሉ አሁንም በዚሁ ሁኔታ ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል ብለዋል፡፡

5.2
ክቡር ንቡረ ዕድ አባ ዮሐንስ ገ/ሕይወት ስብሰባውን ሲመሩ

በሌላ በኩል ሀገረ ስብከቱ ያሉትን ችግር ለመቅረፍ እንዲችል ያሉትን ስጋቶች እንደሚከተለዉ ገልጸዋል ወጣቶች በተለያየ ቦታ በመገኘት ሕገወጥ የገንዘብ አሰባስብ ሥራ ይሰራሉ፣ ይህን ሀገረ ስብከቱ እንዴት ያየዋል?ሁል ጊዜስ ሀገረ ስብከቱ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቀድሞ ተወያይቶ ለምን ዘለቄታዊ መፍትሔ አይሰጥም? ሁል ጊዜስ ለምን በዓላቶቹ ሲደርሱ ብቻ ስጋታችንን እንገልጻለን ካሳለፍናቸዉ በዓላት በመነሳት ለምን አንማርም? በሰልፍ አለመሄድ፤ ምንጣፍ ሲነጠፍ ቶሎ አለመሄድ፤ አለመታዘዝ፤ በሰዓት መድረስ አለመቻል፤ ሰ/ተማሪዎች እኛ ሕጋዊያን ነን ሌሎቹ ሕጋዊን አይደሉም ብለዉ ሲፈርጁ ሌሎቹ ደግሞ እኛም የቤተክርስቲያን ልጆች እንደመሆናችን መጠን ይመለከተናል የሚሉ እና እንዲሁም የበዓሉን ገጽታ የሚቀይሩ ሕገወጥ ሰባክያን ፣ ባሕታዊያን ሰዎችን በመስብሰብ ከየት እንደመጡ ሳይታወቅ ሕዝቡን ግራ የሚያጋቡ አሉ፡፡ አንዳንዶችም መድረኩን ለንግድ ብቻ ነዉ የሚፈልጉች በሞንታርቦ ሰዎች የበዓሉን ምንነት እንዳይረዱ ግራ ያጋበሉ በማለት ሃሳበቸዉን የገለፁ ሲሆን የምሥራቅ አዲስ ኣበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ለተነሱት አስተያየቶች መልስ ሲመልሱ የበዓሉ ባለቤቶች ካህናት ሰ/ተማሪዎች፣ ወጣቶች እና ሁሉም ማህበረ ምዕመናን መሆናቸውን ገልፀው የካህናት አለባበስ፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች አለባበስ፣ የምዕመናን አለባበስ ምን መሆን እንዳለበት በሰፊው አብራርተው መመሪያ ሰጥተዋል ፡፡ በፀበል አረጫቸት ዙሪያም ከሕዝቡ አንደንድ አስተያየቶች እየመጡ ስለሚገኝ ማጥመቅና መርጨት ያለበት ካህናት እንደመሆናቸዉ መጠን በስርዓቱ መሠረት እርጩ፣ ከአቅማችሁ በላይ ካልሆነ በቀር በደንብ ለማዳረስ ሞክሩ፣ በሰ/ት/ ቤቶች እና በወጣቶቹ መካከል ስላለዉ ሁኔታ እኛ ለወደፊቱ ሁሉንም ለማስተካከል ስለምንጥር ለአሁን ግን በሰላም ለማስተካከል ሞክሩ፣ ንግድንና ሕገወጥ ሰባክያንን በታመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕጋዊ እዉቅና ካለዉ ከማኅበረ ቅዱሳን ዉጪ ለማንም አልተፈቀደም ስለዚህ ማንም አስገብቶ የሚሸጥ እይኖርም ፣ትምህርተ ወንጌልንም በተመለከተ ከመድረክ ዉጪ እንደማይሆን ገልጸናል ስለዚህ ባለተረኞቹ በሚገባ መድረካችሁን መጠበቅ ይገባችኃል ብለዋል፡፡ የፐርሰንት ክፍያን በተመለከተ አሁን አዲስ ነገር የምናመጣዉ ሳይሆን በነበረዉ ሂደት የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ይገባል ሀገረ ስብከቱም የራሱን መንገድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል በደረሰን መረጃ መሰረት በመልካም ሁኔታ እየከፈሉ ያሉ ቢሆኑም የተወሰኑ ግን መዘናጋት የሚታይባቸው አሉ፡፡ ስለዚህ የሀገረ ስብከቱን፡- 1ኛ መልካም አስተዳደር ለማምጣትና ለማስፈን፤ 2ኛ በፋይናንስ ደረጃ ሀገረ ስብከቱን ለማሳደግና አቅም ለመፍጥር፤ 3ኛ የሀገረ ስብቱን መሠረተ ልማት ለማሳደግና ለማስፋፋት እንዲሁም 4ኛ የሀገረ ስብከቱን ንብረቶች በአግባቡ እንዲጠበቁ ለማድረግ፤ በቃለ ዓዋዲው መሠረት ፐርሰንት መከፈል አስፈላጊ ስለሆነ በዚሁ መሰረት የፐርሰንት አሰባሰብን በተመለከተ እስከ ታኀሣሥ ወር በትክክል የከፈሉ፤ እየከፈሉ ያሉ እና ከነጭራሹ ያልጀመሩ መኖራቸዉን ገልፀዋል፡፡ አያይዘዉም በአሁኑ ሰዓት ፐርሰንት ለመክፈል የሚያስቸግር ነገር አለመኖሩን ገልፀው ፡፡ሁሉም በተዘጋጀዉ አዲስ ሕጋዊ ሞዴል መሰረት መሰብሰብና ገቢ መደረግ አለበት ብሏል፡፡ ፐርሰንትን በተመለከተ ከተሳታፊዎች ሞዴሉ ትልቅ ስለሆነ ቢስተካከል ፣ ሌላ ተጨማሪ ወጪዎች በአቋራጭ ባንታዘዝ፣ ሠራተኛ ባይበዛብን መልካም ይሆናል በማለት ሃሳባቸዉን የገለፁ ሲሆን ክቡር ሥራ አስኪያጁ እና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሃላፊና የሰ/ት/ቤቶች መምሪያ ሃላፊ ኣባ አዕምሮ ታከለ ሕጉ ላይ ማሻሻያ እስከሚደረግበት ድረስ ልንገለገልበት የሚገባን ባለዉ ስለሆነ ባለን ልንገለገል ይገባል ሌሎቹን ግንበቀጣይ እንደሚገባ ለማስተካከል ይሞከራል በማለት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ሰዎች ያለምንም ሥራ ሲያጨናንቁት ይታያል ለዚህ ደግሞ ዕልባት ያስፈልገዋል ሀገረ ስብከቱ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል እንደሌለበት በክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ እና አባ አዕምሮ ታከለ የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ እና የሰ/ት ቤት ማደራጃ መምሪያ ሃለፊ በሰፊው የተገለፀ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ሳይበደሉና ሥራ እያላቸውዉ ሌላ ቦታ ልቀየር በማለት ተቀጥሮበት ያለዉን ሥራ በመበደል ይመላለሳሉ፡፡ ለዚሁም ተጠያቂዉ በደብሩ ያሉ አሰሪዎች ናችዉ የሥራ መቆጣጠሪያ የላችሁም ሠራተኞቻችሁ የት እንደሚዉሉ አትጠይቁም፣ ቅጥር ዕድገት በራሳችሁ ጊዜ ትፈጽማለችዉ፤ ታሸጋሽጋላችዉ ይህ ደግሞ ሠራተኛዉ አገሌ ቅጥራችን እኩል ሆኖ ሳለ እርሱን አሳድገዉ እኔን እምቢ በለዉኛል በማለት ለአቤቶታ በር ከፍቷል፣ ስለዚህ አድበራቱም ከቃለ አዋዲዉ ትዕዛዝ ዉጭ መቅጠር፤ ማሸጋሸግ እነደማይቻል እየታወቀ ለሀገረ ስብከቱ ችግር እንዲፈጠርበት ምክንያት ሆኖኗል፡፡በመሆኑም ሁሉም ባለ ጉዳይ ሥርዓቱን ጠብቆ መጓዝ ያስፈልገዋል ችግር ካለ መጀመሪያ ለአጥቢያዉ ማሳወቅ ይገባዋል፤ ከዚያ መፍትሄ ሲያጣ ወደ ሀገረ ስብከቱ መምጣት ይገባዋል አሁን ግነ እየሆነ ያለዉ ከዚያ በተለየ መንገድ ነዉ፡፡በመሆኑም ሁላችንም በተመደብንት ሥራና ኃላፊነት በሕጉና በሥርዓቱ ልናገለግል ይገባናል ብለዋል፡፡ እንደዚሁም በተመሳሳይ ዜና በ8/05/05 ዓ.ም የደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሀገረ ስብከቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን ክቡር ንቡረ ዕድ አባ ዮሐንስን ገ/ሕይወትን ጨምሮ የሚመለከታቸው የደቡብ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እንዲሁም የደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞች፤ ሰባኪያነ ወንጌልና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፍ ሃላፊዎች በስብሰባው የተሳተፉ ሲሆን በስብሰባው ላይ ለተገኙት ለሀገረ ስብከቱ እና የደቡብ አዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎቸ በክቡር ንቡረ ዕድ አባ ዮሐንስን ገ/ሕይወት አማካኝነት ስለ ጥምቀት በዓል አከባባር ዙሪያን እና ስለ ሀገረ ስብከቱ መጠናከር በተመለከተ ሰፋ ያለ መብራሪያ የሰጡ ሲሆን በአጠቃላይ ለሀገረ ስብከቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እታች ድረስ ወርዶ የተሠሩ ሠራዎችን በመገምገም እና ሰርቶ በማሰራት ሀገረ ስብከቱ ለሌሎችም ጥሩ አርአያ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡በመጨረሻም መልካም የጥምቀት በዓል እንዲሆን ሁሉም የአህገረ ሰብከቱ ሥራ አስከያጆች መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

03

የልደት በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቅት ተከበረ

                                                                                      በመ/ር ዘሩ እና ኃይሉ

                     እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11

እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡

03

የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላቶች መካከል አንዱ ሲሆን ሁሌ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ እንደ ተለመደው የዘንድሮ በዓልም መከበር የጀምረው ከዋዜማው 12.00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ሥራዓተ ማኅሌት፤ሰዓታት እና ሥርዓተ ቅዳሴ ሲከናወን ያድራል ፡፡ በተለይም በአገሪቱ ዋና መዲና በሆነቸው በአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚገኘው በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል በዓሉ እጅግ በጣም በማቅ ሁኔታ ተከብሮ አድሯል፡፡በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ፤ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ፤ካህናት እና በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በበዓሉ ላይ ተኝተው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡በዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ሥርዓተ ቅዳሴውን የመሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሲሆኑ በ3ቱም መንበር በሥላሴ፤በማርያምና በዮሐንስ ቤተ መቅደሶች ቅዳሴው የተቀደሰ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውም በተለመደው ሰዓት ተጠናቅቋል፡፡ በበዓሉ ላይ ለተገኙ መዕመናን በዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አማካኝነት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁሌ በየዓመቱ የሚከበረው የቅዱስ በዓለ ወልድ በዐለ ንግሥ ታኅሣሥ 29/2005 ዓ.ም በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ቅዱስ በዓለ ወልድ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት መካከል አንዱ ሲሆን የተመሠረተውም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን መንግስት በ1883ዓም እንደሆነ ይታወቃል፡፡

003

በዓመት ሁለት ጊዜ መጋቢት 29 እና ታኅሣሥ 29 ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በዓሉ በድምቀት ይከበራል/ይነግሣል፤የዘንድሮ የ2005 ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በበዓሉ ላይም በርካታ መእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከታኅሣሥ 28 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው 12.00 ሰዓት ጀምሮ ለ18 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡የካቴድራሉ ሊቃውንት መዘምራን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ወረብ አቅርበዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ በጣም የሚስደንቅ በዓል ነው፡፡በበዓሉ ላይ የተገኙት ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በበዓሉ ላይ ለተገኙት መዕመናን ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡

 

4.1

ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋል ሉቃ.2÷11

                                          በመ/ር ኃይሉ እና ዘሩ

4.1

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቀን አቆጣጠር ቀመር አሁን በ2ዐዐ5 ዓ.ም የምናከብረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ዘመን 2ዐዐ5 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

እግዚአብሔር አዳምን በ7ኛ ቀን ሔዋንን ደግሞ በ14ኛ ቀን ከፈጠረ በኋላ በገነት እግዚአብሔር አምላካቸውን እያመሰገኑ እንዲኖሩ ቢያስቀምጣቸው እነርሱ ግን ባለመታዘዝና ወደ መመራመር በመግባት ከእግዚአብሔር ተለይተው ከገነት በመውጣት እሾህና አሜኬላ ወደምታፈራው ምድር ወርደው እንዲኖሩና ከእነርሱ የተገኙት ልጆቻቸውም የዚህ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ ተበይኖባቸዋል፡፡ አዳምም ታሪክ እንደሚነግረን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም የሳጥናኤልን ጥበብ ማለፍ አቅቶት ሳይሳካለት በመቅረቱ እግዚአብሔር ጥረቱን ተመልክቶ ወደ ተባረርክበት እና ወዳሰብክበት ገነት መግባት ቢያቅትም አንተ ድል መንሳት ባቃተህ ሥጋ ተዋሕጄ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው በማለት ቃል ገብቶለታል፡፡ ከዚህ ቃል ኪዳንም የተነሳ የአዳም ልጆች እና ልጅ ልጆች አቤቱ እጅህን ከአርያም ልከህ አድነን፣ ጨለማችን ይብራ፣ እስራታችን ይፈታ ይበጠስ እያሉ ያለቅሱ ይጮኹ ነበር፤ በየዓመቱም ሱባኤ በመቁጠር እየፆሙ ይፀልዩ ነበር፡፡ እርሱም የነቢያት የአባቶቻችንን ጩኸት በመስማት ቀኑ በደረሰ ጊዜ የሸክሙን ቀንበር፣ የአስጨናቂውን ዘንግ፣ ለመስበር፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተዘረጋውን የጠብ ግርግዳ ለመቅረፍ፣ በጨለማ ለሚኖረውም ሕዝብ ብርሃን ለመስጠትና ለመሆን፣ ነቢያት የናፈቋትን የማዳኑን ዕለት ለማሳየት በሉቃስ ወንጌል እና በሌሎቹም ወንጌላት ላይ እንደተጠቀሰው በእንግድነት ለቆጠራ በሄዱበት በዳዊት ከተማ

በቤተልሔም ተወለደ፡፡ ወቅቱ ሮማዊያን ግዛታቸውን አስፋፍተው ኢየሩሳሌምንም ይገዙ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ለግብር አከፋፈል እንዲመች እና እንዲሁም ግዛታቸውን እንደገና ለማጠናከር እንዲያስችላቸው በዚያ ወራት ከአውግስጦስ (ከ31 ዓ.ዓ – 14 ዓ.ም) ቄሳር ሁሉም እንዲቆጠር ትዕዛዝ ወጣ፡፡ ቄሬኔዎስም የሶሪያ አገረ ገዥ ሆኖ በተሾመበት ወቅት የመጀመሪያ ጽሕፈቱ አድርጎ ሁሉም እንዲቆጠር በመታዘዙ ሁሉም ወደ ተወለደበት ቦታ ሄዶ መቆጠር ግድ ስለሆነ ዮሴፍም የትውልድ ቦታው ቤተልሔም በመሆኑ በአውግስጦስ ቄሳር ትዕዛዝ መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዞ ወደ ቤተልሔም ሄደ፡፡ ቤተልሔም ግን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በሕዝብ ብዛት የተጨናነቀች እና ሁሉም ቀድመው ሥፍራ የያዙ በመሆኑ የእንግዳ ማረፊያ ቦታዎች ተይዘዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ዮሴፍና እመቤታችን ማረፊያ ሥፍራ ባለማግኘታቸው ለጊዜው የሚጠለሉበት ቦታ ፈልገው ያገኙት ቦታ በከብቶች ማደሪያ ሥፍራ ላይ ስለሆነ በዚያው ቆይታቸውን እያደረጉ ባሉበት የእመቤታችን የመውለጃዋ ጊዜ ደርሶ ስለነበር በዚያው የበኩር ልጇን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው በከብቶች ማደሪያ ግርግምም አስተኛችው፡፡ ጌታም የትህትና መምህር ስለሆነ ዓለም ቦታ ባትሰጠዉም በሌሎች ተይዟል ብላ ሥፍራ ብታሳጣውም እርሱ ግን እኛን ለማስተማር ጌታ ነኝ ይህ አይገባኝም ሳይል በማይገባው በከብቶች በረት ተኛ፡፡ ሰማይንና ምድርን የፈጠረው ጌታ ዙፋኑን ትቶ ለሰዎች ልጆች ፍቅር ብሎ ከውርደታችን ሊያነሳን በተዋረደው በከብቶች ማደሪያ ተወለደ፡፡ ጌታችን የተወለደበት ምክንያት

 

1. በአዳም የገባውን ቃልኪዳን ለመፈፀም

2. በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል የለውን የጠብ ግርግዳ ለማፍረስ

3. የሰው ልጆችን የጨለማ ሕይወት ለመገርሰስ ነው

ጌታ የወለደበት ሥፍራ ቤተልሔም ሲሆን ቤተልሔም የሚለው ሥያሜ ካሌብ መጀመሪያ አዙባ የምትባል ሚስት አገባ ነገር ግን ከጠላቶቹ ወገን ስለነበረች በእርስዋ አልሰየማትም ቀጥሎ ከብታ የምትባል ሚስት አገባ በእርሷም ከብታ ተብላለች ቀጥሎ ኤፍራታ ወንድ ልጁን ወለደ ስሙንም ልሔም አለዉ ልሔም ማለት ኀብስት ማለት ነዉ፡፡ ቤተልሔም ማለት ቤተ ኀብስት ማለት ሲሆን ቤተ የእመቤታችን ኀብስት የጌታችን ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ሲወለድ ሰብዓ ሰገል በቤተልሔም ተገኝተው ስጦታ በመስጠት ሰግደውለታል ሰብዓ ሰገል ማለት የዕውቀት ሰዎች ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የእሩቅ ምሥራቅ ስዎች ሲሆኑ አባታቸው ዥረደሽት ይባላል ፈላስፋም ነው፡፡ አንድ ቀን ውሃ አጠገብ ሆኖ ወደ ሰማይ ሲመለከት ድንግል በሰሌዳ ኮከብ ተስላ ሕፃን ታቅፋ ሲያይ ፈጥኖ በብረት ሰሌዳ ቀርፆ ሲኖር በመሞቻው ወቅት እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ወስዳችሁ ስጡ ብሎ ነግሮአቸው ስለነበር ኮበቡ ጊዜው ሲደርስ በመውጣቱ እነዚያ ጠቢባን ሰዎች ተመልክተው በኮከቡም በመመራት ወደ ቤተልሔም በመምጣት ወርቅ ከርቤ ዕጣን አበርክተውለታል፡፡

ወርቅ የተበረከተለት ምክንያት

1. ወርቅ የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላ ሃላፊያን ናቸው፡፡ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ

2. ወርቅ ንፁሕ ነው አንተም ንፁሕ ባሕርይ ነህ ሲሉ ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው፡፡ ወርቅ ንፁህነቱ የሚታወቀው በእሳት ሲፈተን ነው የሃይማኖትም ንፁህነቱ የሚታወቀው መከራ ሲቀበሉበት ነው፡፡

ዕጣን የተበረከተለት ምክንያት

1. ዕጣን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ

2. ዕጣን ምዑዝ ነው መዐዛው ያማረ ነው ያንተ ማዕዛም የባህርይ ነው ሲሉ ባንተ ያመኑም ምዕመናን ሃይማኖት እና ምግባራቸው ማዓዛ ነው፡፡

ከርቤ

1. አንተ የማታልፍ ነህ በሰውነትህ ግን መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፡፡

2. ከርቤ የተሰበረውን ልብ ይጠግናል የተለየውን አንድ የደርጋል አንተም በመሞትህ ከማኀበረ መላዕክት የተለየውን አዳምን እና ልጆቹን አንድ ታደርጋለሁ፡፡

3. ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው ምዕመናኑም በፍቅር አንድ ይሆናሉ በማለት ከርቤ አበርክተውለታል፡፡ ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ወርቅ ዕጣን ከርቤ አበርክተውለታል፡፡ በቤተልሔም በጌታ መወለድ ተለያይተው የነበሩት ማኀበረ መላዕክትና ሰዎች ከ5ሺ ዘመናት በኋላ አብረው ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ በማለት ምስጋና አቅርቧል፡፡የጌታችን የልደት ቀን ለሰዎች ልጆች መዳን መሰረት የተጣለበት ቀን በመሆኑ የደስታ ቀን ነዉ፡፡ በመሆኑም መላእክት እና እረኞች በአንድነት እንዳመሰገኑ እኛም የምስጋና ቀን በማድረግ እግዚአብሔርን ሰብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ በማለት የጌታ መወለዱን በማሰብ ተሕትናን በመላበስ በጎ ነገር በማድረግ እናክብር መድኃኒት ለሰላማችን ተወልዶልናልና ይህን የምሥራች እንድንናገር ስለታዘዝን ይህን ታላቅ ዜና አየተናገርን ልናከብረዉ ይገባል፡፡መልካም በዓል፡፡

abune_nathnael

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የገና 2005ዓ.ም በዓለ ልደት ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

                                                                                                      በመ/ር ዘሩ እና ኃይሉ

abune_nathnael

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ ፣ በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንኳን ለ2005 ዓ.ም የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዐለ ልደት በሰላም አደረሳችኹ፡፡ ‹‹ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው ቦቱ፤ በእርሱ ቤዛነት እንድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና፣ እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ፍቅር በዚህ ዐውቀናል፡፡›› /1ዮሐ.4÷9/

እግዚአብሔር ከፍጡራን ሁሉ የተለየና ከአእምሮ በላይ የኾነ መለኰታዊ ኀይል ያለው አምላክ በመኾኑ የባሕርዩን ጥልቅነት በምልአተ ማወቅ ፈጽሞ የማይቻል ቢኾንም እርሱ ራሱ በገለጸልን መጠን የተወሰኑ ነገሮችን እናውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ለፍጡራን ያለው የፍቅር ባሕርይ እጅግ ጥልቅና የማይናወጥ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ በቤተ ልሔም የተወለደበት ቀን ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው›› ብሎ ምልአተ ፍቅሩን ካስረዳ በኋላ በማስረጃ ሲያብራራ ‹‹ቤዛ ኾኖ የሰውን ልጅ ያድን ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮአልና ፍቅሩን በዚህ ዐውቀናል›› ይላል፡፡እግዚአብሔር በልጁ መሥዋዕትነት ዓለምን ለማዳን ያደረገው ፍቅር ከሌላው ሁሉ የበለጠ በመኾኑ ልቆ ተነገረ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር ከፍጡራን የተለየበት ጊዜ እንደሌለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በስፋትም ልንገነዘብ ይገባል፡፡የእግዚአብሔር ፍቅር በዓለም ላይ በምልአተ ባይኖር ኖሮ ሰማይና ምድር እንደዚሁም በውስጣቸው የሚገኙ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት በሙሉ ሕገ ተፈጥሯቸውንና ሥርዐተ ምሕዋራቸውን ጠብቀው መኖር ባልቻሉም ነበር፡፡ ሰዎችም ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ውሳጣዊና አፍዓዊ ምግብና ማግኘት ባልቻሉም ነበር፡፡ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ በመኾኑ ጥፋተኛውንና እውነተኛውን ሳይለይ ፍጡራንን ሁሉ በፍቅር ይመግባል፤ ይመራል፤ ይቆጣጠራል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል ሰፊና ምሉዕ እንደኾነ እንገነዘባለን፡፡ እግዚአብሔር አንዳችም ሳያጎድልበት ሰው በራሱ የተሳሳተ ምኞት ከእግዚአብሔር ፍቅር ቢለይም የሰው በደል በእግዚአብሔር ፍቅር ይሸነፋል እንጂ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በሰው በደል ሊሸነፍ ከቶ የማይቻል ነውና የእግዚአብሔር ፍቅር የሰውን በደል ሲያሸንፍ በፍቅረ እግዚአብሔር ተሰባስበው የተገናኙ ሰማያውያንና ምድራውያን ፍጥረታት በአንድነት ‹‹ለእግዚአብሔር በሰማያት ክብር ተደረገ፣ በምድርም ሰላም ኾነ፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ ተሰጠ›› እያሉ በቤተ ልሔም ከተማ ዘመሩ፡፡ (ሉቃ.2÷14)

እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በፍቅር ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ በዛሬው ቀን በቤተ ልሔም ለዓለም የሰጠው ስጦታ እጅግ በጣም የላቀ ነው፤ ምክንያቱም ሌሎች ስጦታዎች ከፍጥረቶቹ የሚገኙ የፍጥረት ውጤት ስጦታዎች ሲኾኑ የቤተ ልሔም ስጦታ ግን አንድ ልጁን ነውና፡፡ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ያገኙትን ሀብት ማካፈል ይችሉ ይኾናል፡፡ ልጃቸውን አሳልፈው ለሌላ መስጠት ግን እጅግ የሚከብድ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ለሰው ድኅነት ሲባል አንድ ልጅን አሳልፎ መስጠት ከባድ ኾኖ አልተገኘም፡፡ በመኾኑም በዛሬዋ ዕለት በኾነው ነገር እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍጹም ፍቅር ምን ያህል እንደኾነ በሚገባ ለማወቅ ችለናል፤ ልብ እንበል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጸው፡-

 1.   የሰው ዘር በአጠቃላይ በአዳም በደል ምክንያት ለሞትና ለኃሣር እንደተዳረገ ሁሉ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት ምክንያት የሰውን ዘር ሁሉ ለማዳን፤
 2.   እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ታላቅ ነገር ቢኖር የእርስ በርስ መፋቀር እንደኾነ ለማስረዳት፤
 3.  በኃጢአት ምክንያት ያጣነውን በእግዚአብሔር መንግሥት በክብርና በዘላለማዊ ሕይወት የመኖር ዕድል ለማስመለስ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በቤተ ልሔም የተወለደው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለፍጹም ምሕረት ለማብቃት በመኾኑና ምሕረቱንም በብዛት ስላፈሰሰልን ከጌታ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ምሕረት፣ ማለትም የምሕረት ዘመን ተብሎ ይታወቃል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን እኛም እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል፤ ከልደተ ክርስቶስ የምንማረው ትምህርት ወገንን ሁሉ ማለትም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን የሰው ዘር ሁሉ መውደድና መርዳት ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መሥዋዕትነትን ያይደለ ምሕረትን እወዳለኹ፤ እነኾ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለኹ፤ እርሱም እርስ በርሳችኹ ትዋደዱ ዘንድ ነው›› ብሎ እንዳስተማረን በፍቅር እየኖርን ችግረኞችን መርዳት ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር መኾናችንን ሰውን በመውደድና በመርዳት መግለጽ ይኖርብናል፡፡ ባለንበት ዘመን በተለያየ ምክንያት እናትና አባትን ያጡ፣ የወገንን ፍቅርና ክብካቤ የሚሹ ብዙ የእግዚአብሔር ልጆች በየሰፈሩ አሉ፡፡ ለበዓል መዋያ ያዘጋጀነውን ኅብስተ በረከት ከተቸገሩት ሕፃናትና፣ የሚላስ የሚቀመስ ካጡ ወገኖች ጋራ በመኾን በኅብረት መመገብ ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ በፍጹም ፍቅሩ የወደደንን እግዚአብሔርን በቤታችን ውስጥ እየጋበዝን እንደኾነ ርግጠኞች መኾን አለብን፡፡ ‹‹ተርቤ አብልታችኹኛልና ኑ ወደኔ›› የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም እናስታውስ፡፡

በሌላ በኩል በልዩ ልዩ በሽታ ተይዘው መዳንን በመሻት በየሆስፒታሉና በየሰፈሩ የሚገኙ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ በእነዚህ ወገኖች አድልዎንና ማግለልን ሳናደርግ ማስታመምና አቅማችን በፈቀደ መጠን እነርሱን ለማገዝ መረባረብ ምሕረትን የሚያስገኝልን እንደኾነ መገንዘብ አለብን፡፡ ‹‹ብታመም ጠይቃችኹኛልና መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ኑ ወደ እኔ›› የሚል ቃል ኪዳን እንዳለበትም አንዘንጋ፡፡ መማር የሚያስፈልጋቸው ነገር ግን አቅመቢስ በመኾናቸው በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን የሚያባክኑ ወገኖችን ተገቢውን ርዳታ በማሟላት ብቁ ዜጋ ማድረግ ግዴታችን ነው፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! የኑሮ መጓደል በየትኛውም ክፍለ ዓለም ያለ ቢኾንም ሌት ተቀን ጠንክረው በመሥራታቸው በተሻለ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ የሚኖሩ ሀገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያንም አሁን በተጀመረው የልማት ጎዳና በመሮጥ ሁላችን ለሥራ ብቻ ከተሰለፍን ያሉብን ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተወገዱ፣ ሀገራችን እንደበለጸጉት አገሮች በልማት አድጋ፣ ሕፃናት በክብካቤና በዕውቀት የሚያድጉበት፣ አረጋውያንና አረጋውያት የተቸገሩ ወገኖች በማኅበራዊ ተቋማት የሚረዱባትና የሚከበሩባት፣ በሁሉም መስክ ዜጎች በደስታ የሚኖሩባት አገር ማድረግ እንደምንችል ጥርጥር የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድና ፍላጎትም ይህ ነው፡፡ስለኾነም የተጀመሩና ሊጀመሩ ተቃርበው ያሉ ግዙፋን ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች የአገራችንን የድኅነት ገጽታ በመቀየር፣ ከበለጸጉ የዓለም አገሮች ጎን በእኵልነትና በክብር እንድንሰለፍ የሚያደርጉ፣ የኅብረተሰባችንን የዘመናት ችግር በአስተማማኝ ኹኔታ የሚቀንሱ መኾናቸው የታመነ ስለኾነና በሥራም የተረጋገጠ ስለኾነ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የልማት ሥራውን በየዘርፉ እንዲያፋጥን በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን፤ ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን!!

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

                 ታኅሣሥ 29 ቀን 2005 ዓ.ም

img_0011

በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ጋር የትውውቅ መርሃ ግብር ተካሄደ

በመ/ር ዘሩ እና ኃይሉ

 

img_0011
ክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ስብሰባውን ሲመሩ

ታኅሣሥ 26/005 ዓ.ም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠዋቱ 3.00 ሰዓት ጀምሮ መርሃ ግብሩ የተካሄደ ሲሆን በትውውቅ መርሀ ግብሩ ላይ ክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የክፍል ሃላፊዎቹና ሠራተኞች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፤የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የደብር ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞች ሰባኪያነ ወንጌልና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፍ ሃላፊዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ስብሰባው በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የመግቢያ ንግግር በኩቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የተደረገ ሲሆን በንግግራቸው ላይ ሁሉም ነገር የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ነው፡፡ አንድም ነገር ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ነገር የለም፤ ለዚሁም ነው ዛሬ የእግዚብሔር ፈቃድ ሆኖ እናንተን አባቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼን ለማገልገልና እንደወጣትነቴ ላይ ታች ብዬ ለመታዘዝ እዚሁ ቦታ ላይ ለመታዘዝና ለማገልገል የመጣሁት ብለዋል፡፡ ስለሆነም እናንተ የምታዙኝን በአግባቡ፣ በሰዓቱና በወቅቱ ህጉን ተከትዬ ከሠራሁና ከፈፀምኩ እናንተም ሀገረ ስብከቱን የሚያዛችሁና በስሥራችሁ የምታስተዳድሯቸው ሰራተኞች ሥራውን በህጉና በመመሪያው ከሰራችሁና ካሰራችሁ ከአሁን በፊት የነበረውን የሀገረ ስብከቱ የአሠራር ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡

በመቀጠልም በ5ት ዋና ዋና ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መመሪያ ሰጥዋል፡፡

 • በመስተንግዶ ዙሪያ ጉዳይ
 • በሥራ እቅድ ዙሪያ ላይ
 • በመልካም አስተዳደር ዙሪያ
 • በስብከተ ወንጌል ዙሪያ
 • በደሞወዝና የጥምቅት በዓል አከበባር ዙሪያ
 1.  በመስተንግዶ ዙሪያ በተመለከተ፡- በሀገረ ስብከቱ እንደ ከአሁን ቀድም በር ላይ ተሰልፎ መዋል አይኖርም፤ ማንኛውም የገዳማትና አድባራት ሥራም ይሁን የሠራተኞች የግል ጉዳይ የሚፈልጉትን ነገር ግልጽ በሆነ ደብዳቤ ገልጸው ካመጡ አንዳችም የሚዘገኝበት ጉዳይ አይኖርም ሊያስኬድ በሚችለው ሁሉ በህጉና በሥራዓቱ ሁሉም ሰራተኞች በእኩል ጥያቄዎቻቸው እንዲስተናገዱ ይደረጋል፡፡ ይሁንና ግን የተመደቡበትን መደበኛ ሥራ እየተው ያለ አግባብ እና በቂ ምክንያት ሀገረ ስብከቱን እየመጡ ማጨናነቅ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡ ይልቁንም የገዳማትና አድባራት ሠራተኞችና ምዕመናን የተሟላ አገልግሎት ልትሰጡዋቸው ይገባል ምክንያቱም ጽ/ቤቱን ዘግታችሁ ስትመጡ ብዙ ባለ ጉዳይ ይጉላል አሁን ያለንበት ዘመን ደግሞ አይደለም ብዙ ሰው አንድም ሰው በምንም ተአምር ሊጉላላ አይገባም በመሆኑም ሀገረ ስብከቱ እናንተን አያጉላላም እናንተም ሰራተኞችና ምዕመናን ማጉላላት የለባችሁም በማለት መመሪያ ሰጥተዋል፡
 2. በሥራ እቅድ ዙሪያ ላይ በተመለተ፡-ሀገረ ስብከቱም ሆነ ገዳማቱና አድባራቱ በእቅድ እና በእቅድ ብቻ መመራት እና መሥራት አለባቸው ምክንያቱም በእቅድ የማይመራ መስሪያ ቤት ኮንፖስ እንደሌለው አውሮፕላን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከየት ተነስተን የት መድረስ እንዳለብን የምንሰራቸው ማናቸውም ሥራዎች ልማታዊም ሆኑ ማህበራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ በበጀት ዓመቱ አቅደን በሚመለከታቸው የበላይ አካላት ተተችቶና ተገምግሞ ከጸደቀ በኋላ በእቅዱ መሠረት መጓዝ በጣም ቀላል ነው ምክንያቱን ሲገልፁ በእያንዳንዱ ወር ምን መስራት እንዳለብን ዝርዝር እቅዱን እያየን በቀላሉ መስራት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ከእቅዳችን ተነስተን መስራት ከነበረብን ምን መስራት እንዳልቻል እና መስራት ከነበረብን ምን የተሻለ ስራ እንደሰራን መገምገም ይቻላል፡፡ በዚሁም በቀላሉ ጠንካራና ደካማ ጐናችንን ማወቅ እንችላለን ስለሆነም በእቅድ ስንመራ ጠንካራ ጐናችንን አጠንክረን ደካማ ጐናችን ደግሞ አርመንና አስተካክለን በቀጣይ ወር የተሻለ ስራ ለመስራት ያስችለናል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በእቅድ፤ በሰዓትና በጊዜ ልንመራ ይገባል ብለዋል፡፡
 3. ስለመልካም አስተዳደር በተመለከተ፡- ቤተ ክርስቲያኒቷ የመልካም አስተዳደር ፣ የህግ ፣ የቋንቋና፣ የካላንደር ባለቤት መሆኗን ገልጸው ነገር ግን ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በተለይም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሥራው ታሪክ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም ፍትህ በእኩል ያለ አድሎ ለሁሉም መስጠት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሃይማኖታዊ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን የሀገረ ስብከቱና ገዳሙቱ መልካም አስተዳዳር ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ሲነጻጸር ለመናገር የሚከብድ ነገር መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ስለዚህ መልካም አስተዳደር ከስም የዘለለ በሀገረ ስብከቱም ሆነ ሀገረ ስብከቱ በሚመራቸው ገዳማትና አድባራት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም መድረክ ላይ የምንሰብከውና በተግባር የምንሰራው ስራ ሁሉ አንድ መሆን አለበት ሃይማኖታዊ ግዴታችንም ጭምር ነው፤ በተግባር ያልተፈተነ ሃይማኖት ደግሞ ሃይማኖት ሊሆን እንደማይችል ለሁላችሁም ግልጽ ነው ከዚህም የተነሳ ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ አድባራቱ በየሶስት ወር በሀገረ ስብከቱ እየተገኙ ሀገረ ስብከቱን እንዲገመግሙ ይደረጋል፤ እንዲሁም ሀገረ ስብከቱ አድባራቱ ድረስ ወርዶ የስራ ሀላፊዎችን በሰራተኞች ያስገመግማል ይህም አሰራሩ ጥሩ ያደርገዋል ሁላችንም ተጠባብቀን እንድንሰራ ያደርገናል ብለዋል፡፡ከዙሁ ጋር በተያያዘ ቴክኖሎጀው ባመጣው መሳሪያ በመጠቀም አሠራራችን የተሻለ ዘመናዊ መድረግና ለተገልጋዬ ማህበረ ሰብ የተሟላ አግልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርን መስፈን እንችላለን ለዚሁም 4ቱም አህጉረ ስብከት ለአሥራር ያመች ዘንድ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ዌብ ሳይት በሥራ ላይ የዋሉ ሲሆን ይህ ደግሞ በቀላሉ ከሁም ጋር ለመገናኘትና አስፈላጊና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን በዚሁ ዌብ ሳይት በመልቀቅና ምልክቶቻችሁም በኢ-ሜል፤በፋክስና በስልክ በመቀበል ፈጣን እና ዘመኑ የሚፈቅደውን ሥራ መሥራት እንችላለን ብዬ አምናለሁ ብለዋል፡፡የአቅም ግንባታ ሥልጠናም አስፈላጊ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋር ለሁሉም የስራ መስኮች በተዋረድ ወቅታዊ ስልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑንም ገልፀዋል፡
 4.  ስለ ስብከተ ወንጌል አስመልክቶም የቤተክርስቲያኒቷ ትልቁ አገልግሎት ስብከተ ወንጌል ማስፋፋት መሆኑን ገልጸው ትክክለኛ ሰው በትክክለኛ ቦታ ላይ ሊቀመጥ ይገባል ምክንያቱም በዚህ ቦታ ላይ ተመድበመው የሚሰሩ ሰዎች ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅቸዋል፡፡ በተለይም የስብከተ ወንጌል ሀላፊዎችና አስተዳዳሪዎች የስብከተ ወንጌሉን መድረክ ሊያስከብሩት ይገባል ለዚህ የሚመደበው በጀትም ከሁሉም የተሻለ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ይህ የስራ ዘርፍ ሥራው የሚያተኩረው ሰው በማዳን ሥራ ስለሆነ ነው በለዋል፤ ሰው ለማዳን ደግሞ ከሁሉም የተሻለ በጀት መመደብ አግባብ ነው፡፡ በመሆኑም ደብሩ ጥሩ በጀት ሊመድብ ይገባል፤ ሁሉም ሰባኪያነ ወንጌል ደግሞ ለህዝቡ ጥሩ አርያ መሆን ይገባቸዋል በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡
 5. የደሞወዝ ጭማሪን በተመለከተ፡-ምንም እንኳን የደሞወዝ ጭማሪው ከተየቀ የቆየ ቢሆንም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ4 በመከፈሉ ምክንያት ቢዘገይም በአገልግሎት ተሰማርተው ምዕመናን የሚያገለግሉ አገልጋዮች አቅም በፈቀደና ህጉ በሚፈቅደው መልኩ ወቅቱን ጠብቆ ደሞወዝ ጭማሪ ማግኘት መብታቸው ስለሆነ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ተነጋግረው ውሳኔ ስላስተላለፉ በቅረብ ጊዜ እንደሚለቀቅ አስታውቀዋል፡፡ በመቀጠል ከተሰብሳቢዎች መካከል መልአከ ብርሃን ክብሩ ገ/ጻዲቅ የዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ አስተዳዳሪ፣ ወ/ሮ አሰፋች ተስፋዬ የገነተ ኢየሱስ ም/ሰበካ ጉባኤ፣ መጋቤ ሥርዓት ልዑል ሰገድ ተ/ብርሃ የመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዋና ፀሀፊ፣ መጋቢ ሀዲስ ገብረማርያ እሸቴ የመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የስብከተ ወንጌል ኃላፊ እና ብዙ የስብሰባው ታዳሚዎች ክቡር መላአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመመደባቸው እጅግ መደሰታቸውን ገለጽው በወጣው መርሃ ግብር መሠረት መስተናገዱ ለእኛ እጅግ ትልቅ ክብር በመሆኑ እጅግ በጣም ደስ ብሎና ብለዋል፡፡ አያይዘውም የሰሜኑ ክፍል ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ገለጽው የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በመዲናይቱ ዋና ከተማ በቤተ መንግስቱ፣ በመንበረ ፓትሪያሪኩ፣ በፖርላማውና በዩንቨርስቲው መሃል የሚገኝና አገራዊና አሁጉራዊ ፤መንፈሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚከናወኑት በዚሁ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመሆኑ በጣም ደስ ብሎል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመሆን በልማቱና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ እጅና ጓንት ሆነው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል በመጨረሻም የተደረገውን ነገር ሁሉ በማመስገን በቀጣይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስብሰባ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆም ለሁሉም የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞች፤ለገዳማትና አድባራት መኅበረ ካህናትና ልዬ ልዬ ሠራተኞች መልካም የገና እና የጥምቀት በዓል እንዲሆንላቸው በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስም መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ የዕለቱን መርሃ ግብር በፀሎት ተዘግቷል፡፡
img_0002

በአ.አ.አ.ስ .ግ. ፈንድ 7ኛ ዙር ፕሮጀክት የ4ኛ፤ሁ2ኛ ፤ 3ኛና እሩብ ዓመት የድጋፍ እርዳታና በጥቃቅንና አነስተኛ ለሚደራጁ ስልጠና ተካሄደ

                                                                                                  በመ/ር ዘሩ እና ኃይሉ

img_0002
መ/ር ዮናስ ፍቅሩ ፕሮግራሙን ሲመራ

 

በአዲስ አበባ አህጉረ ሰብከት የግሎባል ፈንድ 7ኛ ፕሮጀክት ቅ/ጽ/ቤት ላለፉት አራት ዓመታት ለወላጅ አጥና በችግር የተጋለጡ ህፃናት ድጋፍ እና እንክብካቤ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚሁም በርካታ ተጠቃሚዎችን መርዳት ተችሏል፡፡ እ.አ.አ 2012 የበጀት ዓመት የሁለተኛ እና የሶስተኛ እሩብ አመት ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ለ465 ዜጎች የምግብ የልብስ የጤና እና የመሳሰሉት ወጪዎችን መሸፈኛ የሚሆን ገንዘብ በእርዳታ የሰጠ ሲሆን ለ1345 ዜጎች ደግሞ በትምህርት መሳሪያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ የተደረገላቸው እየተደረገላቸው ከጠባቂነትና ተረጂነት መንፈስ ወጥተው ራሳቸው በንግድ ስራዎች እንዲሠማሩ የሚያስቸል እቅድ ተዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በአህጉረ ስብከቱ የብከተ ወንጌል አዳራሽ ከታህሳስ 24 – 28 2005 ዓ.ም በተደረገ የአምስት ቀናት ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ለመነሻ የሚሆን ገንዘብም ለ66 ዜጎች የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት ክቡር ንብረ ዕድ አባ ዮሐንስ ገ/ህይወት የደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደተናገሩት ቤተክርሰቲያን ገንዘብ ከምዕመናን መሠብሰብ ብቻ ሳይሆን ምዕመናን ተጠቃሚ በሚያደርግ ስራዎች ማሳተፍ ያለባት መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም ለበርካታ ዓመታት ስታደርግ የቆየች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመቀጠልም ይህንን ዕድል ብዙዎች ቢፈልጉትም በእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እድሉን ስላገኛችሁ በአግባቡ መጠቀም ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያን እናንተ አድጋችሁ ተለውጣችሁ ከእርዳታ ወጥታችሀ ማየት የዘወትር ምኞቷ ስለሆነ ሃላፊነታችሁን በአግባቡ ተወጡ በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡ በመቀጠልም የፕሮጀክቱ ዋና አስተዳባሪ መ/ር ዮናስ ፍቅሩ ይህ ለአራተኛ ዙር የሚደረግ ስልጠና መሆኑን ገልፀው ተሳታፊዎች ከአስረ አምስት አድባራትና ገዳም የተውጣጡ ከቀሌ/ከወረዳ/ እና ከአብያተ ክርስቲያናቱ በተቋቋመው የፕሮጀክት አማካሪ ኮሚቴ ተጣርተው ለዚህ ስልጠና የተመለመሉ መሆናቸውን ተናግረዋልል፡፡ በቀጣይም የግሎባል ፈንድ 7ኛ ዙር ቅ/ጽ/ቤቱ ብዙ ሥራዎች ለመስራት ዕቅድ የያዘ መሆኑን ገልፀው ይህንን ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ውጤታማና የተሻለ የስራ አፈፃፀም ለማሳየት ጠንክረው እንዲሚሩ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም የግሎባል ፈንድ 7ኛ ዙር ፕሮጀክት በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድዎ ኮሚሽን እየተተገበሩ ካሉት በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ሲሆን በ27 አህጉረ ስብከት በስፋት የተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

2

በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. በየዓመቱ የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በድምቀት ተከበረ


ታኅሣሥ 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

                    በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

በመጀመሪያ እንኳን ለኃያሉ መልአክ ለሊቀ መላእክት ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን፡፡

እኛ የምናመልከው አምላክ ኪሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፡፡ ት.ዳን.3፥17

በየዓመቱ ታህሳስ 19 ቀን የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በዚህ ዓመትም እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ውልዋል፡፡በዓሉ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባለበት ሁሉ ተከብሮ የሚውል ሲሆን ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናትና መዘምራን እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ሥነ ስርዓት በየአመቱ ሁል ጊዚ ተከብሮ ይውላል፡፡በዘንደሮ ዓመትም እንደተለመደው በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡

በተለይም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ባሉ የቅዱስ ገብርኤል አጢቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉ በድምቀት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ምእመናንም ተኝተዋል፡፡በተለይም በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እጅግ በደመቀ ሁኔታ በአሉ ተከብሮ ውሏል፡፡በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ፤ካህናት፤መዘምራንና ብዛት ያለቸው ምዕመናን በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

 

2

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከታህሳስ 19 ቀን ጀምሮ ሲሆን የገዳሙ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምረው ለ32 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ ለእምነቱ ተከታዮች ምእመናን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እጀግ በጣም የሚያስደንቅ በዓል ነው፡፡

ዛሬ የምናከብረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከባቢሎን እሳት ያዳነበት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው በብሉይ ኪዳን ዘመን ከ605-562 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነገሠው በናቡከደነጾር ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከጣዖት አምላኪና አስመላኪ ኀያላን ነገሥታት መካከል አንዱ ናቡከደነጾር ነበር፡፡ ምስሉ የቆመው በ587 ቅ/ል/ክ እንደሆነ መተርጎማን ያስረዳሉ፡፡ ዳን.3፥1 ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን በማረከበት ዘመን ዳንኤልንና ሦስቱን ሕፃናት በልዩ ሁኔታ አክብሯቸው ነበር፡፡ 

 • ዳንኤልን ብርጣሶር አለው አሰበ በል አምኃ ቤል ሲል ነው
 • አናንያንም ሲድራቅ አለው ወልደ ሰቃየ አትክልት /አትክልተኛ/ ማለት ነው
 • ሚሳኤልንም ሚሳቅ አለው ፀሐቂ ተጋሂ ፍንው ለግብር መልእክት /ትጉህ ፈጣን መልእክተኛ/ ማለት ነው፡፡ 
 • አዛርያንም አብደናጎም አለው ገብረ ዳጎን /የጣዖት አገልጋይ/ ማለት ነው

1

የቀድሞ ስማቸው ትርጉም ግን 1)ዳንኤል ማለት ፍትሕ እግዚአብሔር ዳኛ እግዚአብሔር

2)አናንያ ማለት ደመና 3)ሚሳኤል ማለት ሰምዓኒ እግዚአብሔር /እግዚአብሔር ስማኝ/ 4)አዛርያ ማለት ረድኤት ማለት ነበር፡፡ ት.ዳን.1፥7 ንጉሡ እነዚህን ሕፃናት ለሦስት ዓመት በቤተ መንግሠት ጥሩ ምግብ እየተመገቡ የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያጠኑ ዘንድ አዝዞ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ትምህርቱን እየተማሩ በንጉሡ ቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ሳይመገቡ ጥራጥሬና ውኃ እየተመገቡ በፈተና ያለፉ ነበሩ፡፡ ዳን.1፥8-21 ጠቢባንና አስተዋዮች በመሆናቸው በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ተሾሙ፡፡ ዳን.2፥46-49 የሠለስቱ ደቂቅ በንጉሡ ዘንድ መወደድና መሾም ያስቀናቸው ባቢሎናውያን ለናቡከደነጾር “በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሸምካቸው ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ አምላክህን ያላመለኩ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ” ብለው ከሰሷቸው ያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጣና እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ እነርሱም አንሰግድም አሉ፡፡ ዳን.3፥13-19”

ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ለምስሉ ለማሰገድ ጥረት አድርጓል 1. በመጀመሪያ ዐዋጅ በማወጅ ነው ይህ ዐወጅ ከተራው እስከ ባለሥልጣናቱ ያሉትን የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም ባለሥልጣናቱ ቀድመው በመስገድ አርአያ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡ 2. ሁለተኛው የሕዝቡን ልብ በሙዚቃ እንዲደሰቱ በደስታው ተውጠው ሳያስቡት እንዲሰግዱ ማድረግ 3. የመጨረሻው በማስፈራራት /ወደ እሳት ትጣላላችሁ እያለ/ እንዲሰግዱ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢያባብልና ቢጥር ሠለስቱን ደቂቅ ለማሰገድ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡

ከሠለስቱ ደቂቅ ሦስት ነገሮችን እንማራለን ማመን፣ መቁረጥ እና ማድረግን፡፡ ሃይማኖት እነዚህን 3 ነገሮች ይፈልጋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት በእግዚአብሔር ፍጹም አመኑ፣ ይህንንም እምነታቸውን ሲገልጡ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” በማለት ተናግረዋል፡፡ የመጣባቸውን ሁሉ ለመቀበል ወሰኑ ቆረጡ “አምላካችን እኛን ማዳን ይችላል ነገር ግን ፈቃዱ ከዚህ እሳት ገብተን ሠማዕትነትን እንድንቀበል ቢሆን ከእሳት እንገባለን” በማለት አንድ ልብ፣ አንድ ቃል ሆነው አቋማቸውን ገለጡ፡፡ የቆረጡትን ነገር አደረጉት፤ ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ሦስቱም ነገሮች ስለተፈጸሙ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እሳቱን አብርዶ አዳናቸው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” በማለት የተናገረው ቃልም ተፈጽሞላቸዋል፡፡ /መዝ.33፥7/ ጠባቂ መልአካቸው ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ውስጥ ገብቶ ከመከራ ሥጋ አድኖአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና መልአኩል ልኮ የፈጸመውን ትድግና ያየው ናቡከደነጾር “ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡” ዳን.3፥28-30

  የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል  ተራዳኢነትና አማላጂነት አይለየን አሜን ፡፡

 

 

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጋራ ልምድ ልውውጥ ጉባኤ ተካሄደ

                         በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በግብፅ ኮብፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጋራ ትብብር በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሰፊ የልምድ ልውውጥ መርሀ ግብር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ይህ ጉባኤ ከታኅሣሥ 11-15 ቀን 2005 ዓ.ም. ለአምስት ተከታታይ ቀናት ልምድ ልውውጡ የተከናወነ ሲሆን በአምስቱ ዕለታት በየቀኑ እስከ አንድ ሺሕ የሚሆኑ የተለያዩ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ሰባኪያነ ወንጌልና እንዲሁም ከሁሉም የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የተውጣቱ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች የዚሁ ትልቅ ጉባኤ ተሳታፊ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል ፡፡

በዚሁ የጉባኤው መክፈቻ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እና የኢሊባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ጸሐፊና የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሊቀ ጳጳስ ፤ብፁዕ አቡነ ቢመን የላዕላይ ግብፅ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ቄስ ዳውድ ለሜይ የግብፅ መንበረ ማርቆስ ካቴድራል ካህን፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአድባራት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና የቅዱስ ጳውሎስ ሰዋሰወ ብርሃን ከፈተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ተገኝተዋል፡፡

በመቀጠልም ዐቃቤ ርእሰ መንበሩ ግብፅና ኢትዮጵያ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን አስታውሰው የቆየ ቤተሰባዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የመጡ ግብፃውያንንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አመስግነዋል፡፡በመቀጠል ቄስ ሶምሶን በቀለ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች አይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ መምሪያ ሓላፊ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት አምስት ቀናት የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮረው የልምድ ልውውጡ በከፍተኛ መነቃቃትና ፍላጎት እንደተካሄደ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እነዚህን ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ያላቸው ብቃት እንደተጠበቀ መሆኑን የገለጡት ቄስ ዳውድ ለሜይ በሥርዓት አፈጻጸሙ ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል በተጨማሪም ምእመናን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት፣ የሚታይና የማይታይ ጸጋ ለማግኘት እነዚህ ምሥጢራት ከሕይወታቸው ጋር አስተሳስረው ሁል ጊዜ በማንኛውም ቦታ በየትኛውም ጊዜ የምስጢራት ተካፋይ መሆን እንደሚያስፈልግ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ልዑኩ በአጽንኦት ገልጠዋል፡፡ በመሆኑም ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በዝርዝር ማወቅ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን በማብራራት ይልቁንስ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመጠንከር፣ ከዲያብሎስ ቀስት ለማምለጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ ለመቃኘት፣ ምስጢራቱን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በተግባር መትግበር እንደሚገባም አክለው ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ከደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን በጋር በመሆን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ሦስት ወጣቶችም በገና እየደረደሩ ዝማሬያቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ስንሰማ ንጉሥ ዳዊት በዓይነ ኅሊናዬ ይመጣል በመጽሐፍ ቅዱስ የተዘረዘሩት የዜማ መሣሪያዎች መልካቸቹውን ሳይቀይሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ መዝለቃቸውን አድንቀው ለወደፊት ይህ ትውፊት ሳይቋረጥ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በእነሱ በኩል ከሁለት የዘለለ የዜማ ዕቃ እንደሌላቸው ያስታወሱት ቄስ ዳውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጣዕመ ዜማ እጅግ የሚመስጥና ደስ የሚል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በዝማሬያችን የተመሰጡት ግብፃውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም በፍጹም ተመስጦ ለመዘመር ሲሞክሩ እንደነበር ከቦታው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በአረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተለያዩ መዝሙራትን በማቅረብ የዝማሬውን መልእክት ቄስ ዳውድ አብራርተዋል፡፡ የልምድ ልውውጡ በጎ ገጽታ እንዳለው እና ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዕለቱ ከተገኙ ተሰብሳቢዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡እኛም እንዲህ ዓይነቱ በጎ ጂምር ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው እንላለን፡፡