ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ መልእክት አስተላለፉ

                            በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤

ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በየጠረፉ የቆማችኹ፤

በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤

እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ2005 ዓ.ም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግብሩ›› ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ እንጂ የሥጋችኹን ምኞት ከቶ አትፈጽሙ እላችኋለኹ››

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

የሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተገኘ ፍጡር እንደመኾኑ በሥጋዊ ፍላጎቱ ሳይሸነፍ ራሱን ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ማስገዛት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ከዚህም አንጻር ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ፤ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና›› ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡

ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን በፊታችን ሰኞ፣ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓቢይ ጾም ወራት ጎጂ ከኾኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የኾነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ከዚህ አንጻር ለሥጋዊ አካላችን ጥንካሬ ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጠነክር መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ወደ እግዚአብሔር ቅርበት የነበራቸው ቅዱሳን በተሞክሯቸው እንዳስተማሩንና ቅዱሳት መጻሕፍትም እንዳስረዱን÷ መንፈሳዊ አካላችን የሚጠነክረው የሥጋዊ አካላችን ፍላጎት በጾም ኃይል እንዲደክም ስናደርገው ነው፡፡ ሰይጣንና ክፉ ተግባሩ በሰው ላይ ኀይል የሚያገኙበት ምክንያት እኛ ወደ ምግበ ሥጋ ስናዘነብል እንደኾነ በአዳምና በሔዋን ላይ የኾነውና በጌታችን ላይ የተቃጣው በምግበ ሥጋ የመፈተን ሙከራ ማስረጃዎቻችን ናቸው፡፡

የጾም መንፈሳዊ ጥቅም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በማያሻማ ኹኔታ ተረጋግጧል፡፡ ጾም ማለት የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም መተው፣ ወይም እግዚአብሔር ከማይወደው ነገር ሁሉ መራቅ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከኾነ ከእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶችን ጨምሮ ከሌሎች ፍላጎቶች ሁሉ በመራቅ ራሳችንን ተቆጣጥረን በፍጹም አእምሯችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ኀይላችን እግዚአብሔር አምላካችንን ልናመልክና ለእርሱ ፍጹም ታዛዦች መኾን ይጠበቅብናል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሁልጊዜ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚጠቅም መልካም ሥራን ከመሥራት በቀር ጉዳት የሚያደርሱ ተግባራትን ማራመድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ በየአቅጣጫው የተዘረጋው የሀገሪቱ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲኾን እየተደረገ ያለውን ጥረት የምንመለከተው በታላቅ አድናቆት ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥረቱ አካል በመኾን ጥሪውን ተቀብላ የሚጠበቅባትን ድርሻ ስታበረክት የቆየች ቢኾንም የልማት ፕሮጀክቱ እውን ኾኖ ውጤታማነቱን እስኪያረጋግጥ ድረስ ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታደርገው የተግባር ተሳትፎ ዘወትር ይቀጥላል፡፡

ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊኾን የሚችለው ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ምጽዋትን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ስምምነትን፣ ትሕትናን፣ መረዳዳትን፣ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደኾን ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡ የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢኾኑም በተለይ መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም፤ ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፣ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው የሚቻለንን በመለገሥ፣ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል፡፡ በመኾኑም የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኀይላችን ለመታዘዝ መዘጋጀት ነውና እግዚአብሔር በቃሉ የነገረንን ሁሉ ከመፈጸም ጋራ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታችንን በመወጣት፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መርሐ ግብራችንን በማፋጠን፣ መልካም የኾኑትን የልማት ሥራዎቻችንን ሁሉ በማከናወን ወርኃ ጾሙን ልናሳልፍ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ወርኃ ጾሙን በሰላም እንዳስጀመረን ሱባዔውን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም.

አዲስ አበባ፤

በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ተጀመረ

                                        በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

መጋቢት 8/005 ዓ.ም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠዋቱ 3.00 ሰዓት ጀምሮ በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሃ ግብር ላይ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን በመርሀ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የክፍል ሃላፊዎቹና ሠራተኞች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ የደብር ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞችና ሰባኪያነ ወንጌል በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡

ስብሰባው በብፁእነታቸው በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የመግቢያ ንግግር በብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካኝነት የተደረገ ሲሆን በመቀጠልም በክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ስለአንድነት ጉባኤው ጠቀሜታ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡

በጉባኤው ላይ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ለሜገኙ ገዳማት እና አድባራት የሚከተለው ይዘት ያለው ሴኩላር ደብዳቤ ተበትኗል፡፡

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙት ገዳማት እና አድባራት እንደየ አቅራቢያቸው ተመድበው የአንድነት ጉባኤው በሚካሄድበት ወቅት ካህናትን እና ምዕመናንን ያቀራረበና ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት መነቃቃትን የፈጠረ ጉባኤ እንደነበረ ይታወቅል፡፡

ይሁን እንጂ በሀገራችን አንዱ የጀመረውን መልካም ሥራ ተተኪው የማስቀጠል ልምድ ባለመኖሩ የአንድነት ጉባኤው ተቋርጦ ቆይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ4 አህጉረ ስብከት ከተከፈለ በኋላ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የአንድት ጉባኤው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ካህናቱን እና ምዕመናንን ለማቀራረብና በሃይማኖታቸው ፀንተው እንዲኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ የካትት 13 ቀን 2ዐዐ5 ዓ/ም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት በተደረገው የሰባክያነ ወንጌል ጥምር ስብሰባ የአንድት ጉባኤው ጠንካራ ጎን እና ደካማ ጎን በስፋት ውይይት ከተደረገበት በኋላ የአንድነት ጉባኤው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ጠቃሚ መሆኑ ስለታመነበት በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ የሚመራ 7 አባላት ያሉት የስብከተ ወንጌል መስፋፋት አጋዥ ኰሚቴ ተመርጦ ሥራ በመጀመር የአንድነት ጉባኤው እንዲጀመር ገዳማት እና አድባራትን እንደየ አቅራቢያቸው መድቦአል፡፡ በመሆኑም የገዳሙ /የካቴድራሉ/ የደብሩ ሰበካከ ጉባኤ ጽ/ቤት የአንድነት ጉባኤው መጀመሩን አውቆ ለሰብከተ ወንጌል መስፋፋት ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አስፈላጊውን ወጪ እንዲመድብ እናስታውቃለን የሚል ነው፡፡

በዚሁም መነሻነት የሰሜን አዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት በ6 ምድብ ተመድበው/ተከፍለው በየተራ የአንድነት ጉባኤውን ሊያካሂዱ እንደሚችሉ ሁሉም በደስታ ተቀብለውታል፡፡

ምድብ 1

1. መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል

2. ታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ገዳም

3. መንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም

4. ቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ

5. ቀበና ቤዛዊት ዓለም ኪዳነ ምህረት ቤ.ክ

6. ደብረ ዕንቁ ልደታ ለማርያም ቤ/ክ

ምድብ 2

1. መንበረ ፓትርያርክ ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም

2. መንበረ ልዑል ቅ/ማርቆስ ቤ/ክ

3. ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም

ምድብ 3

1. ገነት ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ

2. ደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ

3. ደበረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤ/ክ

ምድብ 4

1. ደብረ ሲና ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ

2. መንበረ ክብር ደብረ ታቦር ቅዱስ ሚካኤል ገዳም

3. ደብረ ጎልጎታ ድል በር መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ

ምድብ 5

1. እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ቤ/ክ

2. እንጦጦ መንበረ ስብሐት ቅ/ሥላሴ ቤ/ክ

3. እንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት ገዳም

ምድብ 6

1. ገነተ ኢየሱስ ወገነተ ማርያም ቤ/ክ

2. መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ

3. አንቀጸ ምህረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ

4. ደብረ ፀሐይ ፈረንሳይ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ

5. ምስራቀ ፀሐይ ጉራራ ኪዳነ ምህረት

በቀጣይ የዚህ ዓይነት የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር በሁሉም የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ሊካሄድ እንደሚችል ለማወቅ የተቻለ ሲሆን እኛም በሰዓቱና በወቅቱ እየተገኘን ስለ አንድነት ጉባኤው የትና መቼ እንዲሁም እንዴት ተከበረ የሚለውን በጽሁፍ፤በድምፅና በምስል በሰፊው የምንዘግብ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

ቸር ያቆየን

m

የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው የሚገኙት የገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ ጋር የትውውቅ መርሃ ግብር ተካሄደ

                               በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

m

የካቲት 29 ቀን 2005 ዓ.ም በጠቅላይ በተ ክህነት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ የትውውቅ መርሃ ግብር ላይ ብፁአን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት፤የ4ቱም አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥራ አስከያጆችና ሠራተኞች፤የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤የሰበካ ጉባኤ ም/ሊቃነ መናብርት፤ፀሐፊዎች፤ቁጥጥሮች፤ሒሳብ ሹሞች፤ሰባኪያነ ወንጌሎችና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በትውውቅ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ስብሰባው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካኝነት በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የዕለቱ ፕሮግራም በመጋቤ ካህናቱ አማካኝነት እንዲገለጽ ተደርጓል የዕለቱ አጀንዳዎችም፡-

 

 

1. በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው የሚገኙት በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች የተዘጋውን  የደስታ መግለጫ ደብዳቤ ማቅረብ

2. የ 2005ዓ.ም አቢይ ፆምን አስመልክቶ መመሪያ መስጠት

3. ስለ አክሱም ሙዝዬም ሕንፃ ግንባታ በተመለከተ እና

4. በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለ ሚገኙ የተጎዱ አብያት ክርስቲያናት በመለከተ ነበር

ወደ ዋና ፕሮግራም ከመገበቱ በፊት በ3 በፁአን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምሥራቅና የሰሜን አ/አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የምዕራብና የበቡብ አዲስ አበባ አህጉር ስብከት ሊቀ ጳጳስ የፋና ቤንጅ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካኘነት ስለ ነበረው የወቅቱ ሁኔታ አስመልክተው ሰፊ የሆነ ንግግር አድርገዋል፡፡በመቀጠልም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው የሚገኙት በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች የተዘጋውን የደስታ መግለጫ ደብዳቤ በተወከሉ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች አማካኝነት እንዲነበብ የተደረገ ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ቅዱስ አባታችን በ3 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መመሪያ ሰጥተዋል፡-

 1.   የ 2005 ዓ.ም አብይ ጾምን በማስመልከት ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን ከፊታችን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓብይ ጾም ወራት ጎጂ ከሆኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የሆነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡ የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኃይል ለመታዘዝ መዘጋጀት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ በጾም ወራት ሊፈጸሙ ይገባቸዋል ያሏቸውንም ሲጠቅሱ “ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊሆን የሚችለው ርኅራኄን፤ ቸርነትን፤ ምጽዋትን፤ ፍቅርን፤ ስምምነትን፤ ትሕትናን፤ መረዳዳትን፤ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደሆነ ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡን የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢሆኑም በተለይ መሠረታዊ የሆነ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፤ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የሚቻለንን በመለገስ፤ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል” በመሆኑም እንደ ከአሁን ከቀደም መንፈሳዊም ሆነ ማህበራዊ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
 2. በአክሱም የተጀመረው ታሪካዊ የሆነው የሙዝዬም ሕንፃ ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲደረግ ሲሉ መመሪያ የሰጡ ሲሆን
 3. እንደዚሁም በገጠሪቱ ኢተዮጵያ ስለ ሚገኙ የተጎዱ አብያት ክርስቲያናት ቀደም ሲል የተጀመረው የእርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም በአግባቡ ተጠናክሮ ስለ ሚቀጥልበት ሁኔታ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከመደበኛ አገልጋይነት ለዚሁ ታላቅ ክብር ከበቁ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች መካከል 4ኛ ፓትርያሪክ ናቸው

በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው በሚገኙት በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች የቀረበ የደስታ መግለጫ የካቲት 29 ቀን 2005 ዓ.ም

“ ንወድሶሙ ለዕደው ክቡራን ለአበዊነ በመዋዕሊሆሙ እስከ ብዙኃ ክብረ ወሀብቦሙ እግዚአብሔር፤ “ የከበሩ አባቶቻችንን በዘመናቸው እናመሰግናቸው እግዚአብሐር ብዙ ክብርን ሰጥቷቸዋልና”

 1. ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 
 2. ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤ/ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሊባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ 
 3. ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምሥራቅና የሰሜን አ/አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 
 4. ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የምዕራብና የበቡብ አዲስ አበባ አህጉር ስብከት ሊቀ ጳጳስ የፋና ቤንጅ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
 5. ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳስት 
 6. የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤ/ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጆች እና የየመምሪያው ኃላፊዎች 
 7. የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች እና የየክፍሉ ኃላፊዎች 
 8. የጉባኤው ታዳሚዎች በሙሉ

j

በቅድሚያ ከሁሉ አስቀደሙን የበጐ ነገር ሁሉ መገኛ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ በጐ ነገርን ለማድረግ ሲፈቅድ ለዚሁ ተግባር የሚበቃ በጐ ሰው አስነስቶ ለቸርነቱ መገለጫ ያደርገዋል፡፡

በዚህም አምላካዊ ፈቃድ መሠረት ኦርቶዶክሳዊት፣ ሐዋርያዊተና ዓለምአቀፋዊት የሆነችውን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን፣ የካህናቶቿና የሕዝቦቿ እረኛና መሪ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ተጠርተውና ተመርጠው ለዚህ ታላቅ ክብር በቅተዋለና ከማንኛውም ነገር ሁሉ በጽኑዕ ክንዱ ጠብቆ ከዚህ ያደረስዎን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡ ቅዱስ አባታችን እንደሚታወቀው ሁሉ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ወራቶች እጅግ አሳዛኝ በሚባል የታሪክ ክስተት በሳል መሪዎቿን በሞት ያጣችበት መሪር ጊዜ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ማንም ባላሰበውና ባልገመተው ወቅት እኒህን ሁለት የልማት፣ የብልጽግና እና የሰላም ፈርጦች ሀገራችን ብቻ ሳትሆን ምድራችን ብታጣም ሀዘንና ምሬቷን በውስጧ ይዛ መሪዎቿ አኑረውላት ያለፉትን የልማት ትልም በመከተል ቤተ ክርስቲያናችንም ሆነች ሀገራችን ከታቀደላቸው የእድገት ሰገነት ላይ ይደርሱ ዘንድ በመንግስት በኩል በበሳል መሪዎቿ የተፈፀመው የሥልጣን ሽግግር ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ በመጠናቅቁ መላውን የዓለም ህብረተሰብ ያስደነቀ ሆኖ አልፏል፡፡

በሃገራችን መንግስት እንደተከናወነው የሥልጥን ሽግግር ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የደረሰባትን ሀዘን በውስጧ አኑራ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሳል አመለካከት እንዲሁም ያለሰለሰ ጥረትና የፀሎት ውጤት አንድነቷ ሳይናጋና መሠረቷ ሳይነዋወጥ የተፈፀመው የስድስተኛ ፖትርያርክ ምርጫ እውነትም ቤተ ክርስቲያን የሰላም አውድማና መሪዎቿ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም የሰላምና የወንጌል ገበሬዎች መሆናቸውን ፈንትው አድርጎ ያሳየና አማኞቿንም ያኮራ ተግባር ሆኗል፡፡ ቅዱስ አባታችን የቤተ ክርስቲያናችን 5ኛ ፖትርያርክ በመሆን ለሃያ ዓመታት ለዕድገትዋ ደፋ ቀና በማለት ሲጥሩላት የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የአለም ሃይማኖቶች ለሰላም የብብር ፕሬዘዳንት እና የሰላም አምባሳደር ይህን ቅዱስነትዎ አሁን የተረከቡትን ታላቅ መንበር ከተረከቡ ቀን አንስቶ በሚያስጨንቃቸው የቤተክርስቲያን ጉዳይ ምክንያት ለዓይን ሽፋሽፍቶቻቸው እንቅልፍን ለወገባቸውም እረፍትን ሳይሹ በጤናቸውም ሆነ በሕመማቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለአማኞቿ ኩራት እንደሠሩ እና ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለም አደባባይ የላቀ ሥፍራ አግኝታ ተከብራና ታፍራ እንድትኖር ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁ በቃል የሚነገር ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሥራቸው ፍሬዎች በዓይን የሚታዩና በእጅ የሚዳሰሱ የተግባር ማሳያዎች በመሆናቸው እየተመለከቱ ዕፁብ ከማለት ባለፈ ሌላ መስካሪና ዘካሪ አያሻቸውም፡፡ ቅዱስነታቸው ሥራቸውን ጨርሰው ያቆሙ ሳይሆን ከዕለት ወደ ዕለት ቤተ ክርስቲያችን ካለችበት የእድገት ደረጃ ወደ ላቀ የዕድገት ጫፍ ትደርስ ዘንድ በርካታ ትልሞችን ሰንቀው እየተጉ የነበረ ቢሆንም እግዚአብሔር አምላክ ከድካመ ሥጋ ያርፉባት ዘንድ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ/ም ቆርጦ ኖሮ እርሱ ባወቀ ከእኛ በእርፍተ ሥጋ ወስዶ ወደ እርሱ እረፍተ ነፋስ አግብቷቸዋል፡፡

ታዲያ በዚህ ጊዜ እጅግ የበዛ የቤተ ክርስቲያን ሀዘን በካህናቶቿና ምዕመናኖቿ ላይ የደረሰ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ መንፈስ ቅዱስን አጋዥ አድርጐ አስቸኳይ ውይይት በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችን ቀጣዩ ፖትርያርክ እስኪመረጥ ድርስ ታላቁን መንበር ይጠብቁ ዘንድ አንጋፋውን አባት ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ዐቃቤ መንበረ ፖትርያርክ በማድረግ ከሰየመ በኋላ በብፀዕነታቸውም ሥር ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ሊቃነ ጳጳሳትን ሰይሞ ቤትክርስቲያን የቀድሞ ፖትርየርኳ ህልመና ራዕይ ለአፍታም ሳይደናቀፍ በነበረበት ፍጥነት እንዲቀጥል እንዲሁም ሰላሟ እንዳይደፈረስና አገልግሎቷም እንዲስፋፋ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የደረገው አኩሪ ተግባር የቤተ ክርስቲያናችን ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ በታች ይህች ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተክረስቲያን በርካታ የሚተጉላትና የሚሳሱላት የምሁራን አባቶች ምንጭ መሆኗን አመላክቷል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዓባላትም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ከብፁዕ ዐቃቤ መንበረ ፖትርየርኩ ጋር በመምከር ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ያሉትን በርካታ ሥራዎችን ከመፈፀማቸውም ባሻገር ቀጣዩ ፖትርያርክ የሚመረጥበትን ሂደት በአትኩሮት መርምረው ብቁ የሆኑ እና በዕውቀትም ሆነ በአመለካከት የበሰሉ የአስመራጭ ኮሚቴዎችን በማቋቋምና የአስመራጭ ኮሚቴውንም የሥራ እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተል የበኩላቸውን ኃላፊነት የተወጡ ሲሆን የአስመራጭ ኮሚቴውም በመንፈስ ቅዱስ እየታገዘ በመሉ አቅሙና በተሟላ ነፃነት ሰፊ ጊዜ በመውሰድ ሥራውን ሲያከናውን ሰንብቶ አምስት ሊቃነ ጳጳሳትን ለእጩነት በማቅረብ ባለፈው የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ/.ም ታሪካዊ፤ ነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ሂደት ስድስተኛው የቤተ ክረሰቲያናችን ፖትርያርክ ማን መሆኑን ፈንትው አድረጐ አሳየቶንና ቅዱስነትዎን አስረክቦን ኮሚቴው የተጠራበትንና የተሰየመበትን ዓላማ በሚገባ ተወጥቷል፡፡

h

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሌላ አፅናኝ ጰራቅሊጦስን እስክልክላችሁ ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ ብሎ ከተለያቸው በኋላ አዝነውና ተክዘው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት አፅናኝ መንፈስ ቅዱስን እንደላከላቸው ሁሉ ብፁዕ ወቅድሪስ አቡነ ጳውሉስም በእረፍተ ነፍስ ሆነው ከሚገኙበት የጌታ እቅፍ በመንፈስ ሆነው እርስዎን ቅዱስነትዎን የላኩልንን ያህል ተስምቶናልና እኛ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በቅዱስነትዎ ሢመተ ኘትርክና መደሰታችንንና መፅናናታችንን ስንገልፅልዎ ከውስጥ በመነጨ ልባዊ ሀሴት ነው፡፡

ቅዱስ አባታችን ከተፈቀደልን ውሱን ጊዜ አንፃር ብዙ ለማለተ እየፈለግን ብንቆጠብም በቅዱስነትዎ ፊት ሳናመሰግን የማናልፋቸውን አካላት በመጥቀስ (በድጋሚ) እንድናመሰግን ይፈቅዱልናል የሚል የፀና እምነት አለን፡፡

ይኸውም አንደኛ በታላቁ አባት በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተመራ በርካታ ሥራዎችን በዚህ አጭር ጊዜ ላከናወነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋቋመው ለሰባቱ ሊቃነ ጳጳሳት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጅግ የላቀ ክብርና ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ሁለተኛውም በቅዱስ ሲኖዶስ ተቋሙሞ ቅዱስነትዎን ያስገኘልንን የአስመራጭ ኮሚቴም ለከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት የምናመሰግን ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መላው የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምዕመናን ፈጣሪያቸውን በምሕላ፣ በጾምና በፀሎት የጠየቁበትን ረዥም የፀሎት ጊዜያት ባሰብን ቁጥር በዚህ የምርጫ ሂደት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት እነርሱ ናቸውና ለእነርሱ ያለንን ክበረና አድናቆት ልናቀርብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም ብርሃኑ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በላከው 2ኛ መልዕክት ም.13 ቁ11 ላይ “ተፈሥሑ እንከሰ አኃዊነ አጥብዑ ወተዓገሡ ወተሰናአው ወአምላክ ሰላም ወፍቅር የሃሉ ምስሌክሙ፤ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ በአንድ ልብ ሁኑ በሰላም ኑሩ የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” ብሎ እንደተናገረው እኛም የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ቅዱስነትዎ ያልዎትን ዓለም አቀፍ እና ጥልቅ እውቀት በጠቀም ቤተክረስቲያን ዛሬ ከምትገኝበት ታላቅ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚተጉበት ማንኛውም ሥራና በየአህጉሩ በመዘዋወር እንደየሰው ቋንቋ (ልሳን) በመናገር ለሚከውኑት ታላቅ የቤተ ክረስቲያን ሥራ ከእግርዎ ሥር በመሆን ልንታዘዝዎትና ልናገለግልዎት በቁርጠኝነት መቆማችን ስንገልፅልዎ እጅግ ጥልቅ በሆነ ደስታና ስሜት ሲሆን ልዑል እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው የላቀ ሥራም እንደሚፈፅሙ እምነታችን የፀና ነው፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቅዳስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን

የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሀገሪቱ የሰላም፣የልማትና የዕድገት ጉዞ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንደምትቀጥል ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ገልፀዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ከኢትዮጵያ ፌድራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ፕሬዚዳንት ከክቡር አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአቶ ኃይለማርያም ጋር ባደረጉት ውውይት ቤተክርስትያኗ በሀገሪቱ የልማት ጉዞ በመሳተፍ ለሰላምና ለዕድገት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ምዕመናኑም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆንና በመከባበር በሀገሪቱ የልማት ተግባራት ላይ ተሳትፎውን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያላትን አስተዋፅኦ እንደምትቀጥል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣቱን በልማት ስራው በማሳተፍ እንዲሁም ከሀገር ወጥተው ወደ ዓረብ ሀገራት የሚሰደዱ ዜጎችን በማስተማር በኩል ትኩረት መሰጠት አለበትም ብለዋል፡፡ መንግስት ከቤተክርስትያኗ ጎን መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓትሪያሪኩ ገልፀውላቸዋል፡፡

d

የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.የ6ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

                                      በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

d

ብፁእ አቡነ ማትያስ በእስራኤል የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ስድስተኛው የኢትዮጵዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትሪያሪክ በመሆን የካቲት 21/2005 ዓ.ም እንደተመረጡ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በዚሁ በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ 806 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ አቡነ ማትያስ 500 ድምፅ በማግኘት ነበር ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት፡፡

በዚሁም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. እጅግ ባማረ/በደመቀ ሁኔታ ስርዓተ ሢመቱ ተከናውኗል፡፡

ከዋዜማው 2.00 ሰዓት ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያደሩ ሲሆን ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሲደርሱ በክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ ፤ በክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ እና ልብሰ ተክህኖና ጥንግ ድርብ በለበሱ የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል ሁለቱም የካቴድራሉ ደወሎችም ለ20 ደቂቃ ያህል ተደውሏል ፡፡

በመቀጠል ኪዳን የደረሰ ሲሆን ከፀሎተ ኪዳን/ከኪዳን ጸሎት በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴ የቀጠለ ሲሆን ፤ ከሥርዓተ ቅዳሴው ጋር በማያያዝ የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ሢመት በአቃቤ መንበሩ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተመራ በማከናወን ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡ ከሥርዓተ ሢመቱ በኋላ ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል የሕንድ፤ የግብጽ እንዲሁም የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በየተራ ጸሎት አድርሰዋል፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴው እንደተጠናቀቀ በአውደ ምሕረት ላይ የተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡ የአኀት አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ አባቶች እንዲሁም አባ ዱላ ገመዳ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤ አፈ ጉበኤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው በመሾማቸው መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለአገር እድገት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት መልእክት “የተሰጠኝ መንፈሳዊ ኃላፊነት አጅግ ከባድ ቢሆንም ወይኩን ፈቃድከ /እንደ ፈቃድህ ይሁን ብሎ ማገልገል ብቻ ነው የሚቻለው ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ስለሆነ ነው በመሆኑም ከእግዚአብሔርና ከሕዝበ ክርስቲያኑ የተሰጠኝን አደራ ለመወጣት ከብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ከምእመናን ጋር አብረን ተባብረን ከሠራን ሥራው የቀለለ ይሁናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡

ብፁእ አቡነ ማትያስ በትግራይ ክልል በቀድሞው አጋሜ አውራጃ በሰቡሀ ወረዳ በ1934 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም ቀሲስ ወልደገሪማ ከሚባሉ አባት ፊደልና ንባብን ተምረዋል ። የኤርትራ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማእርገ ድቁና እንደተቀበሉ በቀድሞው ትግራይ ክፍለ ሀገር ተንቤን አውራጃ ጮኸ በሚባል ገዳም በ1949 ዓ. ም በመግባት ለ10 ዓመት ገዳሙን ያገለገሉ ሲሆን በ1955 ዓ ም ከገዳሙ አበምኔት ማዕርገ ምንኩስናን ተቀብለዋል ። አቡነ ማትያስ 13 ዓመታት በሊቀ ረዳኢነትና ለአንድ ዓመት የገዳሙ ቄስ ገበዝ በመሆን አገልግለዋል ። ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ተመድበውም አገልግለዋል፡፡ በ 1968 ብፁእ አቡነ ተክለሃይማኖት የቤተክርስትያኒቱ ፓትሪያሪክ ሆነው ሲመረጡ አቡነ ማተያስ ምክትል ልዩ ፀሓፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ብፁእነታቸው ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ ፣አረቢኛ፣እብራይስጥኛና ግሪክኛ ቋንቋዎች ይናገራሉ፡፡

b

ሰበር ዜና

b

ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢትየጽያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው ተመረጡ፡፡ ከ806 ድምጽ 500 ውን በማግኘት ፓትርያርክ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በዚሁም መሠረት:-

ብፁዕ አቡነ ማትያስ 500ድምፅ በማግኘት 1ኛ

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ 98

ድምፅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ 98

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በ70 ድምፅ

ድምፅ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ 39

በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሚሾሙ ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ይኾናሉ፡፡በዐለ ሲመቱም እሁድ የካቲት 24/2005 ዓ.ም በመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የፈፀማል፡፡

በመጨረሻም ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት ብፁዕ አቡነ ማትያስ  ባስተላለፉት መልእክት “ከእግዚአብሔርና ከሕዝበ ክርስቲያኑ የተሰጠኝን አደራ ለመወጣት ከብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ከምእመናን ጋር አብረን ስንለምንሠራ ሥራው የቀለለ ይሁናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡

z

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

                                              በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

በስመ አብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን

z

 

ከስድስተኛው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ስድስተኛው ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ ከተቋቋመበት እና ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እየሰራ ያለውን ስራዎች ለሚዲያ ተቋማት መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም ምርጫው በካህናት እና በምዕመናን ዘንድ ግልፅ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ የካቲት 8 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በሰጠነው መግለጫ እንደገለፅነው የምርጫው ሂደት በወጣው መርሃ ግብር መሰረት በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በምርጫ ህገ ደንቡ በተደነገገው መሰረት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ካህናትና ምዕመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክርስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይሆናል የሚሉትን እንዲጠቀሙ በተላለፈው ጥሪ መሰረት ጥቆማቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከየካቲት 8-14 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጡ ጥቆማዎችን ሲያጣራ ቆይቷል፡፡

በተደረገው ማጣራትም 2791 ጥቆማዎች ለኮሚቴው ደርሰዋል፡፡ ለፓትርያርክነት የተጠቆሙ ብፁዓን አባቶች ቁጥር 36 ሲሆኑ 15 የጥቆማ ወረቀቶች በአግባቡ ተሞልተው ባለመገኘታቸው ኮሚቴው ሳይቀበላቸው ቀርቷል፡፡ ጥቆማዎችን ከማጣራት ጎን ለጎን የአስመራጭ ኮሚቴው ከአምስት ያልበለጡ ከሶስት ያላነሱ ዕጩ ፓትርያርኮችን የካቲት 16 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ለሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለማቅረብ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በተደረገው ውይይትም አሁን በአገልግሎት ላይ ካሉ ብፁዓን አባቶች መካከል 19 ሊቃነ ጳጳሳትን በቀጣይነት ለማጣሪት አሳልፏል፡፡ የተከተለው መመዘኛም ዕድሜና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

በዕድሜ በተደረገው ማጣራት በምርጫ ህገ ደንብ በተደነገገው መሰረት ዕድሜያቸው ከ75 የበለጡተን እና ከ5ዐ ዓመት በታች የሆናቸውን አባቶች ወደ ምርጫ እንዳይገቡ አድርጓል፡፡ ለቀጣይ ማጣራት ከቀረቡት 19 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የምርጫ ህገ ደንቡን መሰረት አድርጎ ከሰፊ ውይይት በኋላ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት መርጧል፡፡ ኮሚቴው ሰፊ ጊዜ በመውሰድ ማጣራት ያደረገው በስምንቱ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ነው፡፡ በተደረገው ማጣራትም አምስት ሊቃነ ጳጳሳት ለይቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቧል፡፡

እነርሱም፡-

1. ብፁዕ አቡነ ማትያስ – ዕድሜ 71- በኢየሩሳሌም የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ

2. ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ – ዕድሜ 75 የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

3. ብፁዕ አቡነ ዮሴም – ዕድሜ 61 የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

4. ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል – ዕድሜ 59 – የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ፣ የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ፣ የከፋ ሽካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

5. ብፁዕ አቡነ አቡነ ማቴዎስ – ዕድሜ 5ዐ – የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው የምርጫ ህገ ደንቡን መሰረት አድርጎ ለዕጩ ፓትርያርክ ለቅዱስ ሲኖዶሰ ምልዐተ ጉባኤ ያቀረባቸው ከላይ ስማቸው የተዘረዘሩት ብፁዓን አባቶች የካቲት 16 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቀርበው የምልዐተ ጉባኤውን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም ስድስተኛው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ፓትርያርክ ይሆኑ ዘንድ በነዚህ ብፁዓን አባቶች ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመምሪያና የድጅት ኃላፊዎች፣ ከ53 አህጉረ ስብከት የሚወከሉ የካህናት፣ የምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የአድባሪት እና የገዳማት አስተዳዳሪሪዎች በውጭ ሀገር ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የማፀበረ ቅዱሳን ተወካይ፣ ከግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚወከሉ መራጮች፣ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ከጧቱ 1፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ ምርጫውን ያከናውናሉ፡፡

መራጮችም ከየሚወከሉበት ሀገረ ስብከት እና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ተቋማት በመግባት ላይ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የወደደውን እና የፈቀደውን አባት መንጋውን ይጠብቅና ያሰማራ ዘንደ በመንበሩ እንዲያስቀምጥ ከዛሬ የካቲት 18 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተገኙ ፀሎታቸውን በማድረስ ላይ ናቸው፡፡

መላው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ካህናትና ምዕመናን በዕጩነት ከቀረቡት ብፁዓን አባቶች መካከል ለመንጋው እረኛ እግዚአበሔር አምላክ እነዲሰጠን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ በፆምና በፀሎት ፈጣሪያቸውን እንዲጠይቁ፤ መራጮችም የተወከሉበትን ደብዳቤ እና የመረጡበትን ቃለ ጉባኤ በመያዘ የካቲት 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጧቱ 2፡ዐዐ ሰዓት በመገኘት የመራጮች ምዝገባ እንዲያካሄዱ ምርጫው የወጣውን የምርጫ ህገ ደንብ ተከትሎ መካሄዱን ለመታዘብ የአራቱ እኀት አበያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ የዓለም አበያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ሶስት የመንግስት ተወካዮች እና ሶስት የሀገር ሽማግሌዎች እንዲታዘቡ ደብዳቤ የደረሳቸው በመሆኑ በዕለቱ የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ከጧቱ 12፡ዐዐ ሰዓት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተገኝተው ምርጫውን ይታዘባሉ፡፡

ምርጫው የሚካሄደው በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመሆኑ ሁሉም መራጮች የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ከጧቱ 1፡ዐዐ ሰዓት ጀምሮ በቦታው በመገኘት ምርጫውን እንዲያካሄዱ እየጠየቅን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናን እና ምዕመናት ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በሰላም እንዲፈፀም ከዛሬ የካቲት 18 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ጀምሮ ምርጫው እስከሚፈጸምበት የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ቀናት ፈጣሪያቸውን በፆምና በፀሎት እንዲጠይቁ ደጋግመን እናሳስባለን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአበሔር

ራሱን ቅዱስ ሲኖዶስ ብሎ የሚጠራው አካል ያወጣውን የሐሰት መግለጫ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

‹‹ኢያስሕቱክሙ አኃዊነ ፍቅራን፤ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ›› ያዕ. 1፡16

ስሕተት በባህርዩ ጎጂና በማናቸውም ጊዜ የማይደገፍ ቢሆንም ከሰው ጋር አብሮ የሚኖር በመሆኑ ሰው ከስሕተት ጸድቶ አያውቅም፤ ስሕተትም ከሰው ጠፍቶ አያውቅም፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ለሰው የሚያስተላልፈው ቋሚ ምክር ሰው ስሕተትን እንዳይፈጽም ነው፣ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ስሕተት ከፈጸመ ደግሞ በንሥሐ እንዲመለስ ነው፣ ቅዱስ መጽሐፍ ስሕተት እንዳይፈጸም አጥብቆ ከማስተማሩም በተጨማሪ ስሕተትን በንሥሐ ማሰረዝ የሚያስችል ጸጋ አለው፣ ሰዎች በዚህ ጸጋ እየተጠቀሙ ራሳቸውን ያስተካክላሉ እግዚአብሔርንም ያስደስታሉ፡፡

ሰው በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ፍጹም ተወቃሽ የሚሆነው ስሕተትን በመፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ስሕተቱን አምኖ በመቀበል በንሥሐ ለመታረም ዝግጁ ባለመሆኑ ነው፡፡

በክርስቶስ ደም የተመሠረተችና በመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ የምትጠበቅ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በሃይማኖቷ በትምህርቷና በሥርዓቷ እንከን የለሽ ቤተ ክርስቲያን ለመሆኗ ዓለም የሚመሰክረው ሐቅ ነው፣ ይሁንና በውስጧ የሚገኙ አገልጋዮች ሰው እንደመሆናቸው መጠን አልፎ አልፎ ስሕተት አይፈጽሙም ማለት አይቻልም፡፡

ከዚህ አንጻር ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት በቤተክርስቲያናችን ከፍተኛ ባለሥልጣን የተፈጸመውን ቀኖናዊ ስሕተት የዚህ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን የፈጸሙ አባት፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡198 ላይ ‹‹ወአይደልዎ ለኤጲስ ቆጶስ ከመ ያውድቅ ርእሶ እም ሐራተ ንጉሥ ወይሠየም በምንትኒ እምግብራተ ንጉሥ ወለእመ እጥብዐ ውስተ ዝንቱ ይትፈለጥ እመዓርጊሁ እስመ እግዚእነ ይቤ ኢይክል አሐዱ ገብር ከመ ይትቀነይ ለክልኤ አጋእዝት ወእመ አኮሰ ያምዕዖ ለአሐዱ ወያሠምሮ ለካልኡ›» ፓትርያርክ ራሱን ከክርስቶስ አገልጋይነት ሌላ ለንጉሥ ከሚሠሩ ሥራዎች በማናቸውም ስፍራ መሾም አይገባውም፤ በዚህ ቢገኝ ከሹመቱ ይሻር፣ ጌታችን ‹‹አንድ አገልጋይ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻለውም፣ አለዚያ ግን አንዱን ያሳዝናል፣ ሌላውንም ደስ ያሰኛል ብሎአልና»፡፡ (ማቴ 6፡24) ተብሎ በቅዱስ ወንጌልና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለውን የዚህን ዓለም ሹመት ከመንፈሳዊው ሹመት ጋር በማዳበል እየሠሩ የጣሱት ቀኖና ሳያንስ ‹‹ወለእመ ተራድኦ በመኳንንተ ዝንቱ ዓለም ወተሠይመ ለቤተ ክርስቲያን እመኀቤሆሙ ይትመተር ወይሰደድ ውእቱኒ ወኩሎሙ እለ ተሳተፍዎ፣ ማለትም የቤተ ክርስቲያን መሪ በዚህ ዓለም ገዥዎች ጉልበት ለቤተክርስቲያን ቢሾም ይሻር እርሱና ግብረ አበሮቹ ሁሉ ይለዩ›› ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡175 የሚለውን ሌላ ቀኖና በድጋሚ በመጣስ የገዥዎችን ኃይል ተጠቅመው ሲኖዶሱን ተጭነውና መንፈስ ቅዱስን ተጋፍተው የፓትርያርክነቱን ሥልጣን ጨበጡ፡፡

በይቀጥላልም ለእግዚአብሔርና ለእውነት ከመታዘዝ ይልቅ ላስመረጣቸውና ለቆሙለት ምድራዊ ባለሥልጣን በማድላት፣ የተዛባ አሠራርን በመከተል፣ እውነትነት የሌለው መልእክትን በማስተላለፍ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለነቀፋ ዳረጉ፣ ሕዝቡንም ቅር አሰኙ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸሙ እነኚህ ስሕተቶች በቀኖናው ላይ በግልጽ እንደተደነገገው ከሥልጣን የሚያሽሩ ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ድርጊታቸው ቅሬታ ያደረበት ሕዝብ እግዚአብሔር ብሶቱን እንዲገልጽ የፈቀደለት ቀን ሲደርስ ቅሬታውን እየገለጸ በሁሉም አቅጣጫ ተቃውሞውን አስተጋባ፡፡

ዐራተኛው ፓትርያርክ የነበሩት አባት ከሕዝቡ ይቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎች በርግጥ የተፈጸሙ ስለመሆናቸው ኅሊናቸው የሚያምንባቸው ነበሩና ሊያስተባብሉአቸው አልቻሉም፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ነሐሴ 18 ቀን 1983 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስን ሰብስበው ሕመም ካደረብኝ ብዙ ጊዜ ቆይቶአል ስለሆነም የቤተ ክርስቲያን ሥራ እንዳይበደል ቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነቱን ተረክቦ እንዲሠራ በማለት በራሳቸው ጥያቄ ሥልጣናቸውን አስረከቡ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን ደረጃ በደረጃ ካጠና በኋላ ቀኖናው የሚጠይቀውን ሁሉ ጠብቆ እርሳቸውን ከሥልጣን አስነሣ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዐራተኛው የቀድሞ ፓትርያርክ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ፓትርያርክ አይደሉም፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ አሠራሩ በእርሳቸው ምክንያት የተፈጸመውን ቀኖናዊ ስሕተት በማስተካከል እርሳቸውን በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ ሲወስን፣ ቀኖናው ያዘዘውን ድንጋጌ ፈጸመ እንጂ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አላፈረሰም፣ ቤተ ክርስቲያናችንም ሁለት ፓትርያርኮች እንዲኖሩአት አላደረገም፣ ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ዐራተኛውን የቀድሞ ፓትርያርክ በሕጋዊ መንገድና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መርህ መሠረት ከሥልጣን ካስነሣበት ቀን ጀምሮ በሕግ ፊት ፓትርያርክ አይደሉምና ነው፡፡

አንድ ፓትርያርክ ለመሻር የሚያበቃ ቀኖናዊ ጥፋት ከተገኘበት መሻር እንዳለበት የሚከተለው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያስገድዳል፡፡ ‹‹ወለእመኒ ኢረከቡ ላዕለ ቀዳማዊ ኤጲስ ቆጶስ ዘይደሉ ለመቲሮቱ ለይንበር በመካኑ ወእመሰ ረከቡ በላዕሌሁ ለይሢሙ በመካነ ዘአሁ ዘአልቦ ነውር ውስቴቱ ወለዝንቱስ ያውግዝዎ፤ በፊተኛው ፓትርያርክ ላይ የሚያሽር ጥፋት ካላገኙበት በቦታው ይቀመጥ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለውን ጥፋት ፈጽሞ ቢያገኙት ግን እርሱን ሽረው ጥፋት የሌለበትን ሌላ ይሹሙ›› ይላል ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡17ዐ

ቅዱስ ሲኖዶስ ዐራተኛው የቀድሞ ፓትርያርክ ባቀረቡት ጥያቄና በዚህ ቀኖና መሠረት እርሳቸውን አንስቶ ሌላ ፓትርያርክን ሾመ እንጂ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ አልሾመም፣ሁለት ፓትርያርክ እየተባለ የሚነገረው አነጋገርም ሕጋዊነት የሌለው ፍጹም የስሕተት አባባል ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ውሳኔ ባስተላለፈበት ጊዜ ዛሬ በአሜሪካ ያሉት አባቶችም ባሉበት በተስማሙበትና በፈረሙበት ሁኔታ የተፈጸመ ሆኖ ሳለ ዛሬ ያ የፈረሙበት ሰነድ በቤተ ክርስቲያን ውሰጥ ተቀምጦ እያለ እውነትነት የሌለው ሌላ ታሪክን ለመተረክ ሲሞክሩ መሰማታቸው እጅግ ከፍተኛ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እምቀዳሚታ ተዓኪ ደኃሪታ፣ ከፊተኛይቱ ይልቅ የኋለኛይቱ ትከፋለች›› (ማቴ 12፡45) ብሎ እንዳስተማረን ፊት በተፈጸመው ስሕተት ተፀፅተው ቤተ ክርስቲያን ለመካስ በመዘጋጀት ፈንታ አሁንም ሌላ የባሰ ስሕተት ለመፈጸም ያለሀገሩና ያለመንበሩ ሲኖዶስን አቋቁሚአለሁ በማለት

1. የሰሜን አሜሪካ አባቶች ራሳቸው ስሕተት ፈጽመው ሌላውን ለማሳሳት እያደረጉት ያለውን ቀኖናዊ ስሕተት አቁመው የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ፣

2. መላው ሕዝበ ክርስቲያን በተለይም በውጭ የሚገኘው የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ከሚገልጽበት የአንድነት መንፈስ ዝንፍ ሳይል ከቤተ ክርስቲያኑ የሚተላለፍለትን መመሪያ እየተቀበለ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንዲቆም

3. ስሕተቱ ማን ጋር እንዳለ አውቆ ለመምከርም ሆነ የኅሊና ዳኝነትን ለመስጠት እንዲሁም በእነርሱ አፍራሽ የሐሰት ቅስቀሳ ግራ እንዳይጋባና እንዳይሳሳት እውነተኛ መረጃ ይደርሰው ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ በቀድሞ ዐራተኛው ፓትርያርክና ከርሳቸው ጋር ባሉት አባቶች የተፈጸመው ስሕተት ሁሉ በጽሑፍ በሚድያና በልዩ ልዩ ጉባኤያት ለሕዝቡ እንዲደርስ የሚደረግ ስለሆነ ሁሉም እየተከታተለ ለቤተ ክርስቲያኑ ሉዓላዊ አንድነት ዘብ እንዲቆም፤ በእነርሱ ላይም ሰላሙን እንዲቀበሉ የማያቋርጥ ተፅዕኖ እንዲያደርግ

4. ሕጉና ቀኖናውን ተከትሎ እየተከናወነ የሚገኘው የስድሰተኛው ፓትርያርክ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ይፈጸም ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ እስከአሁን ድረስ እያሳየ ያለውን የላቀ ተሳትፎና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል

5. የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮ በሀገር ውስጥና በዓለም ዙርያ ለማስፋፋት ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ከግቡ ለማድረሰ የሁሉም ሕዝበ ከርስቲያን ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ ስለሆነ ሕዝቡ እንደ ካሁኑ በፊት የተለመደው ድጋፋን አጠናክሮ እንዲቀጥል

6. በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባቶች እየተከተሉት ያለው ሃይማኖትን የማይወክል ፖለቲካዊ አስተሳሰብን አውልቀው በመጣል በሃይማኖት አጀንዳ ብቻ ለመሥራት ፈቃደኞች ከሆኑ አሁንም ቤተ ክርስቲያናችን እጅዋን ዘርግታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን ሁሉም እንዲገነዘብ

7. ስሕተት የሚስተካከለው ስሕተተኛውን በመከተል ሳይሆን ስሕተተኛውን በማረምና ወደሚበጀው ነገር ለመመለሰ ጠንክሮ በመሥራት መሆኑን ግንዛቤ ተወስዶ የባህር ማዶ አባቶች የሀገርንና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከግምት ሳያስገቡ የበለጠ ስሕተት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተሳስተው እንዳያስቷችሁ በስሕተታቸውም እንዳትተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን በአጽንኦት ያስተላልፋል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊው ቀኖናን መሠረት አድርጎ ጊዜውን የዋጀ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመቅረጽና በማጽደቅ፣ መዋቅሩን በማጠናከርና አገልግቱን ዓለም አቀፋዊ ቅርፅ በማስያዝ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾምና ሕዝበ ክርስቲያንን በመከፋፈል ቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ይቅር የማይሉትን ታላቅ ስሕተት ፈጸሙ፡፡

‹‹የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ›› እንደሚባለው የፈጸሙት ቀኖናዊ ስሕተት ከባድና ተደጋጋሚ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ ነገሩን በሰላም መፍታት ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ በማመንና ቀኖናውን በቀኖና በማሻሻል ለእርሳቸው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አሟልቶ በክብር እንደሚይዛቸው ከእርሳቸው ጋር ያሉት ሿሚዎችና ተሿሚዎች አባቶችም ተቀብሎ በሥራ እንደሚመድብ 6ኛውን ፓትርያርክ በመምረጥና በመመረጥ ሂደትም አብረው እንዲሠሩ በሙሉ ልብ ቢጋብዝም መልሱ አይሆንም ሆኖአል፡፡

ይህም ድርጊታቸው አንድነትን የሚፈልጉ ሳይሆኑ ባይሳካላቸውም በውስጣዊ ኅሊናቸውና ከበስተጀርባቸው ባለ ሌላ አካል በስመ ሃይማኖትና በስመ ቀኖና ለመፈጸም የሚመኙት ሌላ ሕልም እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ተገንዝቦአል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ አንድነቱን በእጅጉ ቢናፍቀውም በአሁኑ ጊዜ ሰሚ አለማግኘቱን ሲረዳ ስድስተኛውን ፓትርያርክ አስመርጦ ሥራውን ለመቀጠል በመወሰን መደበኛ ሥራውን ቀጥሎአል፡፡

የተወደዳችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ምእመናንና ምእመናት

የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድነት ማየት እንደምትናፍቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ይገነዘባል፣ ይሁን እንጂ የምንመኘው መልካም ነገር ሁሉ ስለተመኘነው ብቻ የሚገኝ ሳይሆን እውነቱንና ሊሆን የሚችለውን ተከትለን በምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት ብቻ መልካም ምኞታችንን ማሳካት እንደምንችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የሚፈለገውን የአባቶች አንድነት ማረጋገጥ የሚቻለውን ሌላ የጥፋት ጎጆ ለመቀለስ የሰሜን አሜሪካ አባቶች የሚያስተላልፋትን አፍራሽ ቅስቀሳ በማሰላሰል ሳይሆን በሀገሩና በመንበሩ ያለውን፣ ዓለም ከእርሱ ጋር እየሠራ ያለውን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ተከትሎ በጥበብ በማስረዳትና በመውቀስም ጭምር የሚሳሳቱትን በመመለስ ነው፣ ስለሆነም ይህንን እውን ለማድረግ በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ምእመናን ሁሉ የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት በመፈጸም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ክብርና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና መጠበቅና መስፋፋት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንክሮ እንደሚሠራ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ላላችሁ ምእመናን ሁሉ መግለጽ ይወዳል፡፡

እግዚአብሔር ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ

የካቲት 13 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

7

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን 6ኛውን የፓትሪያርክ ምርጫ የካቲት 21/2005 ዓ.ም እንደምታካሂድ አስታወቀች፡፡

                                              በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

7

ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለማስመረጥ የተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ከምርጫው ሂደት ጋርና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተመለከተ ዛሬ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ለጋዜጠኞች ወቅታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በዚሁም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን 6ኛ የፓትሪያሪክ ምርጫ ለማካሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ከሊቃነ ዻዻሳት ፣ከጠቅላይ ቤተክህነት ሰራተኞች ከአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ከሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ከማህበረ ቅዱሳን የተውጣጣ 13 አባላት ያለው አሰመራጭ ኮሚቴ አቋቋማ ዝግጅት ሰታደረግ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ በዚሁም መሠረት ኮሚቴው ምርጫው የሚካሄድበት ቀንና የምርጫውን ፕሮገራም በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል ፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብፁዕ አቡነ እሰጢፋኖስ በመግለጫው እንዳሉት የመጨረሻውን ምርጫ የሚያከናውኑት ከሊቃነዻዻሳት፣ ከገዳማትና አድባራት፣ ከካህናት፣ ከምዕመናን፣ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና ከማሀበረ ቅዱሳን የተውጣጡ በአጠቃላይ 800 ሰዎቸ ናቸው ብለዋል፡፡ የምርጫውን ሂደት ለማስፈጸም የወጣው መግለጫ ምእመናን ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመያዝ ለእጩነት የሚያስቡትን አባት አስመራጭ ኮሚቴው ጽ/ቤት ድረስ በአካል በመቅረብ እንዲሁም ከሀገር ውጪ የሚገኙ በፋክስ ቁጥር 0111567711 እና 0111580540 ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲጠቁሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ የካቲት18/2005 ዓ.ም አምስት እጩዎችን ይፋ ያደርጋል ፡፡ ምርጫውን ለማካሄድ ከ53 አህጉር ስብከት፣ ከካህናት፣ ከምዕመናን፣ ከሰንበት ተማሪዎች የተውጣጡ 13 አባላት ተመርጠው የካቲት 19 አዲስ አበባ እንደሚገቡም አስታውቀዋል፡፡ምርጫው የሚካሄድበት ቀንም የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ምርጫው ተከናውኖ፣ በዚሁ ዕለት ምሽት 12 ሰዓት ላይ ውጤቱ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

ምርጫው የዓለም አብያተክርስቲያናት ማህበር፣ የአፍሪካ አብያተክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮች እና ምዕመናን እንደሚታዘቡትም ገልፀዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የወደደውንና የፈቀደውን ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ አባት በመንበሩ ያስቀምጥ ዘንድ ካህናትና ምእመናን ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ ለአንድ ሱባኤ የሚቆይ የጸሎት ጊዜ መታወጁን አስታውቋል፡ የፓትርያርኩ በዐለ ሲመቱም እሁድ የካቲት 24/2005 ዓ.ም በመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚካሄድም አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአጉስታ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደረሰ

                            በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

ማክሰኞ ጥር 14/05/05 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7.30 ሰዓት ሲሆን መንስኤው ባልታወቀ ምክንያት የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሊደርስ እንደቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡በዚሁ የእሳት ቃጠሎ እጅግ በጣም የሚያስደንቅ እና የሚያስገርም ተአምር ታይቷል፤4ቱም ፅላቶች ከነመጎናፀፊያቸው አንድም የእሳት አደጋ ሳይነካቸው ሊትርፉ እንደቻሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፅላቶቹም ስም ፡-

1. በእመቤታችን ስም የተሰየሙ ሁለት ጽላቶች ፤

2. የቅዱስ ዑራኤል ፅላት እና

3. የመጥምቁ የቅዱስ ዮሐንስ ፅላት ናቸዉ

የእሳት ቃጠሎ በደረሰበት ዕለት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ እና መ/ር ባህሩ ተፈራ የሀገረ ስብከቱ የህግ መምሪያ ኃላፊ በአካል ተገኝተው ማህበረ ካህናቱንና ህዝበ ክርስቲያኑን ያፅናኑ ሲሆን ታቦታቱም ከተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን በካህናቱና በህዝበ ክርስቲያኑ በክብር ታጅበው ወደ ቤተልሄም ገብቷል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት ሀገረ ስብከቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቃጠሎውን መንስኤ በማጣራት ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑም በተለይ ወጣቶቹ ቤተ ክርስቲያኑን በድጋሚ ለመገንባት ከፍተኛ የሆነ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ዝርዝር ሁኔታውን በቀጣይ እየተከታተልን እናቀርባለን፡፡

6

የ2005ዓ.ም የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

                                  በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

6

በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 የሚከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሪነት ከ13 ታቦታት በላይ በሚያድሩበት በጃን ሜዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡ የዓመቱ ተረኛ የሆነው የገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ ‹‹ ተሰሃልከ እግዚኦ ምደረከ ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ እም ሰማያት ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም››በማለት ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል፡፡ በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ዐበይት በዓላት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ይህም በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ፤ በማእከለ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ከዋዜማው ከጥር 10 ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ፤ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን መሠረት በማረድግ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ታቦታት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ በካህናትና ዲያቆናት፤ እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራንና ምዕመናን በዝማሬ በመታጀብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ታቦት ማደሪያ በማምራት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሔድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ማምራቱን ያበስራሉ፡፡ ‹‹ያን ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ ዮሐንስም በዮርዳኖሰ ወንዝ አጠመቀው›› እንዲል፡፡/ማቴ.3፡1/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስራቿን መድኅነ ዓለም ክርስቶስን ለዓለም የምትሰብክበት፣ ከእርሱም ያገኘችውን፣ ይህም ዓለም እንደሚሰጠው ያልሆነውን፣ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ትሕትና ለዓለሙ ትሰብክበታለች፡፡ እንዲሁም ለሀገራችን በጎ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ተደንቀው የሚያዩትና በመስተንግዶው የሚደመሙበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ በዓሉን በልዩ ትኩረት ታከብራለች፡፡

ለዚህ በዓል አከባበር ቤተክርስቲያን ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ታቦታት በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲመለሱ ጉልህ ሚናዋን ትወጣለች፡፡ በዚህ መሠረት በየአጥቢያው የሚገኙ ወጣቶች ከክብረ በዓሉ ቀደም ብሎ በመሰብሰብ ቅዱሳት ሥዕላትን በታቦታት ማረፊያዎች በማዘጋጀት፣ በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ጨርቆችን /ባነሮችን/፤ የኢትዮጵያ ባንዲራን በየአብያተ ክርስቲያናቱ አደባባዮች በመስቀል፣ የቤተክርስቲያናትን ቅጥርና አስፋልት በማጽዳት ፤ለታቦት ክብርን ለመስጠት ምንጣፎችን በማንጠፍ በዓሉን ያደምቁታል፡፡ ምእመናን ከየቤታቸው ለበዓሉ በሚገባው ልብስ አሸብረቀው ወጥተዋል፡፡ እናቶቻችን ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰሙትን የሊቃውንት አባቶቻችን ወረብ ተከትልው፣ የታቦታቱን መውጣት በመጠባበቅ እልልታቸውን ያሰማሉ፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ዝግጅቶቻቸውን አጠናቅዋል፣ የዝማሬ ልብሳቸውን ለብሰዋል፡፡ምእመናኑም ከየመሥሪያ ቤታቸው በር ላይ ቆሞው የታቦታትን ማለፍ እያዩና በእልልታ እና በጭብጨባ እያጀቡ በእነርሱም መባረክን ዓይናቸው ተስፋ እያደረገች ታቦታቱ የሚመጡበትን አቅጣጫ ያማትራሉ፡፡ ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር በተለይም በጃንሜዳ ከየአድባራቱ አስራ ሦስት ታቦታት በአንድነት የሚገኙበት በመሆኑ ህዝቡን ለመባረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ፤በመዘምራንና ምዕመናን በመታጀብ ጉዞ የተጀመረ ሲሆን አመሻሽ ላይ ጃን ሜዳ ሊደርሱ ችለዋል፡፡

የየሰንበት ት/ቤቶቹ መዘምራን ፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዜማ እየዘመሩ ፤ምዕመናን በዕልልታና በሸብሸባ ታቦታቱን በማጀብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በመቀጠልም እለቱን በማስመልከት በአቃቤ መንበረ ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ቸርነት ሰፊ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዑለ ባሕሪውን ዝቅ አድርጎ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ዮሐንስ ወዳለበት ቦታ ለመጠመቅ መጥቷል፡፡

ዮሐንስን አጥምቀኝ ማለቱ ለእኛ አብነት ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ለመመሥረት ሲል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዶ አጥምቆት ቢሆን ኖሮ ምእመናን ቀሳውስቱን እቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥመቁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሔድም ባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሌላት እንዳትሆን ሥርዓትን ለማስተማር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር፤ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ” ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ጥምቀትን በየዓመቱ የምናከብረው እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፤ በዝናብ አብቅሎ በጸሐይ አብስሎ የሚመግብ እርሱ ስለሆነ፡፡ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነውና ከሦስቱ አካል አንዱ አካል መሆኑን በአደባባይ የገለጠበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን በዓል ነው” በማለት እለቱን በማስመልከት የገለጹ ሲሆን በብፁዕነታቸው ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

5.6

የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ምሽቱን በመቀጠል ትምህርት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የተሰጠ ሲሆን በእለቱ ተረኛ በሆነው በገነተ ኢየሱስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀውንትና ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

የለሊቱ ሥርዓተ ማህሌትና ሥርዓተ ቅዳሴ በባለተረኛው በገነተ ኢየሱስ ካህናትና መዘምራን ተከናውኗል፡፡ ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ክቡር አቶ ታደሰ በንቲ፤በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር፤ጥሪ የተደረገላአቸው እንግዶች፤ አገር ጎብኚዎች፤ የየአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን በማስመለከት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ መርሐ ግብሩ ተጀመረ፡፡ ጸበሉም ተባርኮ ለምእመናን እንዲዳረስ ተደርጓል፡፡ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ባሰተላለፉት ትምህርትም “በዓላችን የሰላማችን ፤የአንድነታችን ምልክት ነው፡፡ መሠረቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ አደባባይ ተገኝቶ የእኛን ችግር ያስወገደበት ፤ ነፃነታችንን ያገኘንበት፤ የኀጢዓት ደብዳቤያችን የተቀደደበት፤ዮርዳኖስን ተሻግረን በአንድነት ድኅነት መንግስተ ሰማያትን ያየንበት እለት ነው፡፡ ዛሬ በአንድነት በዘመነ ፍዳ የተዘጋው ጆሯችን የአብ ድምጽ የሰማበት ቀን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ ታቦታቱ ወደየ ማረፊያ ቦታቻው በክብርና በሰላም ተመልሰዋል፡፡

                                    ወስብሐት ለእግዚአብሔር