p001

የ2006 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ

p001

የመስቀል ደመራ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤የአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ተወካይ፤ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶችና አንባሳደሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በደማቅ ስነ-ስርአት ተከብርዋል፡፡

በዓሉ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፀሎተ ቡራኬ የተጀመረው የተጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ተቀብሮ የነበረውን እና በንግስት እሌኒ የተገኘውን መስቀል ለማሰብ በዓሉን እንደሚያከብሩት ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ኢትዮጵያውያን የተገኘውን መስቀል በማሰብ የመስቀሉን በረከት ለማግኘት እንደሚያከብሩትም ነው የተናገሩት።

የመስቀል በዓል ለዘመናት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሲያከብሩት የቆዩት በዓል መሆኑን ያወሱት ቅዱስነታቸው ፤ ህዝቦች ተከባብረውና ተቻችለው ለመኖራቸው ተምሳሌት መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ የአቶ ድሪባ ኩማ ተወካይ በመክፈቻ ንግግራቸው የመስቀል ደመራ በአል የሀገራችን ብሄር ብሀሄረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት በድምቀት ሲያከብሩት የኖሩት ሃይማኖታዊ በአል ብቻ ሳይሆን ታሪካችንን፣ የቱሪዝም ሀብቶችንና ሌሎች እሴቶቻችን ለሌላው ዓለም የምናስተዋውቅበት የማንነታችን መገለጫ ጭምር ነው ብለዋል፡፡ በበአሉ ጥንግ ድርብ የለበሱ ካህናቶችና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ዝማሬዎችን አቅርበዋል። የደመራ መለኮስ ስነ ስርአቱ ተካሂዶ የደመራው በአል ፍጻሜ ሆኗል ፡፡

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የብፁዕ ወቅደስ አቡነ ማትያስ ቀዲማዊ ፓትርያርክ መልእክት››)

{flike}{plusone}

0691

የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሥሩ ካሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የትውውቅ መርሀ ግብር አካሄደ

0691

በዚሁ ክፍለ ከተማ በዋና ሥራ አስከያጀነት የተመደቡት ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ ሲሆኑ የትምህርት ዝግጀታቸውም በመንፈሳዊና በዘመናዊ ትምህርት መስክ 2 የመጀመሪያ ድግሪዎች አላቸው፡፡

ከዚህ በፊት ከ1996-2005 ዓ.ም በጂማ ሀገረ ስብከት የጎማና አጋሮ ወረዳ ቤተ ክህነት በዋና ሥራ አስከያጅነት፤እንዲሁም የሁሉም ሃይማኖቶች ፎረም ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮምሽን የሠላም አምባሳደር በመሆን መጠነ ሰፊ የሆኑ ሥራዎች የሠሩ ሲሆን በዚሁ ሥራቸው የላቀ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ ተብለው በዚሁ ክፍለ ከተማ በዋና ሥራ አስከያጀነት ተመድበው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ነሐሴ 20/12/05 ዓ.ም በወረዳው ሥር ላሉ አስተዳዳሪዎች፤ ፀሐፊዎች፤ቁጥጥሮች፤ሒሳብ ሹሞችና ሰባክያነ ወንጌል ጋራ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን በዚሁ ስብሰባ ላይ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተው ስለ ሀገረ ስብከቱ አዲሱ የሥራ አወቃቀር እና አደረጃጀት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠል ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ ስለ ክፍለ ከተማው አስመልክተው ሰፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በልማትና በመልካም አስተዳደር ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደመሰሩ ተናግረዋል፡፡በተለይም ክፍለ ከተማው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሠሯቸው ካቀዷቸው መካከል

1. G+5 የወረዳው ክፍለ ከተማ ህነፃ ሲሆን ይህን ሊያሠሩና ሊያሰተባብሩ የሚችሉ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡እነዚህም 5 ከወረዳው ገዳማትና አድባራት፤2 ከወረዳው ጽ/ቤት በድምሩ 7 ሰዎች የተመረጡ ሲሆን እነዚህ ኮሚቴዎች ህንፃውን ለማሠራት ገዳማትና አድባራት፤በጎ አድራጊ ግለ ሰዎችና ድርጅቶች በማስተባበር ሥራው በመጪው 2006ዓ.ም ተጀምሮ በ2007 እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

ህንፃው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም ለቢሮና ለሁለ ገብ አገልግሎት ሊውል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

2. እንደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል እና የመሳሰሉት የወረዳው ገዳማትና አድባራት የቀድሞ ካርታቸው ታድሶ አዲሱ ካርታ እንዲሰጣቸውና ያልነበራቸውም አዲስ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣቸው ለማድረግ ቅደሚያ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡በመቀጠልም ሁሉም የወረዳው ሠራተኞች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት ሠራተኞች በወረዳው መልካም አስተዳደር ለማስፈንና መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ከጎናቸው እንዲሰለፉ አሳስበዋል፡፡

በአራዳና ጉለሌ ክ/ከተማ ስር የሚገኙ አድባራትና ገዳማት ዝርዝር:-

 1.መ/ፀ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል እና በዓለ ወልድ

2. መ/መ/ቅ/ገብርኤል ገዳም

3. ታ/ነ/በዓታ ለማርያምና ቅ/ኪዳነ ምህረት ቤ/ክርስቲያን

4. መ/ፓ/ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም

5.መ/ገ/ጽ/ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን

6. ደ/ነ/ቅ/ዮሐንስ እና ቅ/ማርያም ቤ/ክርስቲያን

7. መ/ል/ቅ/ማርቆስ ቤ/ክርስቲያን

8. ቀበና ም/ፀ/መድኃኔዓለም ቤ/ክርስቲያን

9. ጉለሌ አምባ ደ/መ/ቅ/ኪዳነ ምህረ

10. ጸ/አርያም ቅ/ፋኑኤል ቤ/ክርስቲያን

11. ሐመረ ኖህ ቅ/ኪዳነ ምህረት ገዳም

12. እንጦጦ መ/ፀ/ቅ/ማርያም ቤ/ክርስቲያን

13. እንጦጦ ደ/ኃ/ቅ/ራጉኤል ቤ/ክርስቲያን

14. እንጦጦ መ/ስ/ቅሥላሴ ቤ/ክርስቲያን

15. ምስካዬ ህዙናን መድኃኔዓለም ገዳም

16. ቀጨኔ ደ/ሰ/መድኃኔዓለም እና ቅ/ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን

17. ደብረ ሲና ቅ/እግዚአብሔርአብ ቤ/ክርስቲያን

18. መ/ክ/ቅ/ሚካኤልና አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤ/ክርስቲያን

19. እንጦጦ መንበረ ንግሥት ቁስቋም ማርያም ቤ/ክርስቲያን

20.ድልበር መ/ሳ/መድኃኔዓለም ቤ/ክርስቲያን ናቸው

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅር ››)

{flike}{plusone}

0908

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2006 ዓ.ም አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዓውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡-

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣

• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

• በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣

• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የዘመናት ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ከሁለት ሺ አምስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማቴዎስ ወደ ሁለት ሺሕ ስድስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ!!!

“ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እግዚአበሔር፣ እርሱን ፈልገው ያገኙት ዘንድ፣ ሰዎች የሚኖሩባቸውን የዕድሜና የዘመናት መጠን ሠራ” (የሐ.ሥራ.17÷26-27)

አምላካችን እግዚአብሔር፣ ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል፣ የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት፣ ፍጥረታትን ውብ አድርጎ ሲፈጥር፣ ዘመናትንና ዕለታትን ለመለየት ያስችሉ ዘንድ፣ ብርሃናትን በሰማይ ጠፈር ፈጥሮአል፤ (ዘፍ.1÷14-19) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ የሰው ልጅ፣ በብርሃን ዑደት እየታገዘ፣ ዘመናትን፣ ወቅቶችን ፣ወራትንና ዕለታትን ለይቶ በማወቁ፣ መርሐ ግብር እያወጣ፣ ለሥራው አፈጻጸም ይጠቀምባቸዋል፤ በመሆኑም፣ ዘመናት፣ ለሥራችን የሚሰጡት ግብአት፣ ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል፤ እግዚአብሔር፣ ዘመናትን በሰዓታት፣ በቀናት፣ በወራት በወቅቶችና በዓመታት፣ ከፋፍሎ የፈጠረበት ዋና ምክንያት፣ በእነርሱ መለኪያነት፣ አቅደን፣ አልመንና ጠንክረን በመሥራት፣ ራሳችንን፣ ቤተ ሰባችንን፣ ሀገራችንንና በአጠቃላይ ዓለማችንን፣ ለኑሮ የተመቸች፣ ውብና ለም አድርገን እንድንከባከብና እንድንጠብቅ ነው፡፡ (ዘፍ.2÷15)

የዘመን ጸጋ፣ በሥጋዊ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ከፍተኛ ትርጉም አለው፤ የእግዚአብሔር ቃል፣ ከፍ ብሎ እንደነገረን፣ ዘመናት፣ እግዚአብሔርን ፈልገን ለማግኘት የሚያስችሉን መሣሪያዎች ናቸው፤ ይህም ማለት፣ እያንዳንዱ ዓመት፣ በሰው አእምሮ ውስጥ ጥሎት የሚያልፍ፣ ተግባራዊ ትምህርትና ዕውቀት አለ፤ ከዚህ አኳያ፣ ሰው፣ በየዓመቱ ከሚቀስመው ሰፊ ግንዛቤ፣ ዕውቀቱን እያሰፋ፣ ወደ ተሻለ ማስተዋል ይሸጋገራል፤ ጤናማ ማስተዋልን ሲያገኝ፣ ፈጣሪውን ወደ መፈለግና ወደ መከተል፣ ፍጹም ሰው ወደ መሆንም ይደርሳል፤ በዚህ ምክንያት፣ ዘመን፣ ሰው፣ ፈጣሪውን እንዲያውቅ የሚያስችል፣ የማብቃት ጸጋ አለው ማለት ነው፤ (የሐ.ሥራ. 17÷26-27)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት!

እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥር ዓላማ አለው፤ ተቀዳሚ ዓላማውም፣ በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን፣ እርሱን እንድናውቅ፣ እርሱን እንድናምን፣ እርሱን እንድናመልክና ለእርሱ እንድንታዘዝ፣ በእርሱም የዘላለም ሕይወትና ክብር እንድናገኝ ነው፤ (ሮሜ.1÷19-21፤ ዮሐ.20÷31)

በምድራዊው ኑሮአችንም እንዳንቸገር፣ ልዩ ልዩ ሀብት ያላትን ምድር ፈጥሮ ሰጥቶናል፤ ይሁንና፣ ምድራችን፣ በማኅፀንዋ የተሸከመችውን ልዩ ልዩ ጥሬ ሀብት፣ መልክና ጣዕም እንዲኖረው አድርጎ ወደ ጥቅም የመለወጡ ኃላፊነት፣ ለእኛ አስረክቦአል፤ ይህም፣ እግዚአብሔር፣ እኛን የሥራው ተሳታፊዎች የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር፣ የሥራ ሁሉ ጀማሪ ከመሆኑም ሌላ፣ ሁሌም ሲሠራ የሚኖር፣ ሥራ ወዳድ አምላክ ነው፤ (ዮሐ. 5÷17) የእኛንም አካል ለሥራ የተመቸ አድርጎ መፍጠሩ፣ የሥራው ተሳታፊዎች እንድንሆን ብሎ እንደሆነ ልናስተውል ይገባል፤ ስለለሆነም፣ እኛ፣ ታታሪ ሠራተኞች በሆን ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ተባባሪዎች እንሆናለን፤ ከሥራ በራቅን ቁጥር ደግሞ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ላለመተባበር እየከጀልን እንደሆነ፣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ አንጸር፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዓቢይ ነገር፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኃላፊነቴ ምን ሠራሁ? ምንስ ቀረኝ? በአዲሱ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋር ተባባሪ ልሁን የሚለውን ነው፤ ሥራ መሥራት ማለት፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር ማለት ነውና፤ እያንዳንዱ ሰው፣ ይህንን አስተሳሰብ አንግቦ፣ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው፣ እውነትም ዘመኑን በሥራ ወደ አዲስነት ይለውጣል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፡-

ዓይነተ ብዙ በሆነ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በተፈጥሮ ጸጋ የጎደላት የሌለ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም የበለጠና የተሻለ ሀብት ያላት ሀገር ናት፤ ነገር ግን፣ በሀገራችን ከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ተከማችቶ የሚገኘውን ሀብት፣ ጠንክረን በመሥራት ወደ ጥቅም መለወጥ እየቻልን፣ የሌላውን ትርፍራፊ ለመለቃቀም በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ፣ መተኪያ የማናገኝላቸውን ልጆቻችን፣ በየአቅጫው እየተጎዱብን ነው፤ ወጣት ልጆቻችን፣ ለአደጋ በተጋለጠ ሁኔታ፣ በሕገ ወጥ መንገድ፣ ከውድ ሀገራቸው እየወጡ በየአካባቢው ወድቀው እየቀሩ ናቸው፤ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ለማስቆም፣ ሕዝቡ በርትቶ በማስተማርና በመሥራት፣ ልጆቹን ከአሰቃቂ ሕልፈተ ሕይወት ማዳን አለበት፡፡

ሃይማኖታችንና ሀገራችንን የምንወድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በሀገራችን ሥር ሰዶ የቆየውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመቅረፍ፣ በማኅበራዊ ኑሮው የተስተካከለና በኢኮኖሚው የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርቦሽ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀር፣ በስምምነትና በመመካከር መሥራት፣ ተቀዳሚ ዓላማችን ማድረግ አለብን፤ ከሁሉም በላይ፣ የተጀመሩም ሆኑ ለወደፊት የሚጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ ፍጻሜ አግኝተው፣ ሀገራችንን በልማት የመለወጥ ሕልማችንን እውን ሊያደርግ የሚችል፣ ሰላማችን በአስተማማኝ ሁኔታ የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ ብቻ መሆኑን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ለአፍታ እንኳ ሊዘነጋው አይገባም፡፡ በመሆኑም፣ ሁላችንም ኢትዮያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ በአካባቢ ሳንለያይ የዕድገታችን ዋስትና የሆነው ሰላማችንን፣ በንቃት መጠበቅ አለብን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት፡-

የሀገር ደኅንነትና ልማት ከሚረጋግጥባቸው አንዱ፣ በአካል፣ በአእምሮና በአስተሳሰብ ጭምር፣ ሙሉ ጤናማ የሆነ ማኅበረ ሰብ ሲኖረን ነው፤ ስለሆነም፣ በሀገራችን፣ በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ጊዜ፣ የጤና ባለሙያ ተገቢ እንክብካቤና እገዛ ባለማግኘት፣ ለሞት አደጋ የሚጋለጡ እናቶችና ሕጻናት፣ በርከት ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህን ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ፣ በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን የእናቶችና የሕጻናት የጤና እንክብካቤ፣ የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሕዝባችን ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል፤ ሕክምና ማለት ጥበብ ማለት ነው፤ ጥበብን ደግሞ አጽንተን እንድንከተላትና እንድንጠቀምባት፣ እግዚአብሔር ያዘዘን በመሆኑ፣ በባለሙያና በሕክምና ጥበብ እየተረዱ፣ በጤና ተቅዋም መውለድ እግዚአብሔር የፈቀደውና የሚወደው ነው፤ በተለይም፣ እናቶቻችን፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው፣ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቅዋማት እየተገኙ፣ በጤና ባለሙያ ድጋፍና ርዳታ በመውለድ፣ ጤንነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በመጨረሻም፣ በአዲሱ ዓመት፣ ሕዝባችን ሁሉ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ኑሮው የበለፀገ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የተካነ፣ ጤንነቱና ሰላሙ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ፣ በተሠማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመሥራት፣ ሀገሩን ያለማ ዘንድ፣ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ይባርክልን ይቀድስልን አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

መስከረም 1 ቀን 2006 ዓ.ም

ባሕረ ሐሳቡን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ(ባሕረ ሐሳብ የዘመን መቁጠሪያ)

{flike}{plusone}

00718

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች የቁጥጥርና የሥራ አመራር ሥልጠና ተሰጠ

                                                                                     በሀገረ ስብከቱ አይቲና ዶክሜንቴሽን ክፍል

                                                       

00718

ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በሥሩ ላሉ 7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና አጠቃላይ ሠራተኞች ከነሐሴ 22 -23 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ የአቅም ግንባታና ማሻሻያ ሥልጠና መርሐ ግብር ተሰጥቷል፡፡

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ማለትም 1. አራዳ ጉለሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት 2. የካ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት 3. ቦሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት 4. ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት 5. ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት 6. ልደታ ቂርቆስ አዲስ ከ/ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት 7. አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሚል በአዲስ መልክ መደራጀቱንና መዋቀሩን ተከትሉ ቀደም ሲል በሐምሌ /2005 ዓ.ም መልካም አስተዳደር ለዘላቂና ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት በሚል ርዕስ ለ5 ቀናት ያህል ለሀገረ ሰብከት ሠራተኞች፣ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች፣ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የክፍል ኃላፊች፣ ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ሙሉ ሥልጠና መስጠቱ ይታወቃል፡፡

እንደዚሁም ሀገረ ስብከቱ ከሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት ያህል የሚገለግል ጊዚያዊ የሥራ አደረጃት በባለሞያዎች አዘጋጅቶና በቅዱስ ሲኖዶስ አፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን 2ኛው ሙሉ መዋቅርና አደረጃጀት ደግሞ ሥራውን ሙሉ ቡሙሉ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከጥቅምት 30/2006 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ለሀገረ ስብከቱ በታሪከ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም ለ2ኛ ጊዜ ከነሐሴ 22-23/05 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል በዚሁ በሥልጠና ላይ የተገኙ ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች 1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2. ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ዳውሮና ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 3. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 5. የሀገረ ሰብከቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ፣ የየክፍላተ ከተሞቹ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አሥኪያጆች፣ ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፍ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የሥልጠናው መርሐ ግብር በቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናውን አስመልክቶ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” በሚል ርዕስ የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በመግቢያ ንግግራቸው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ይበጃል ይሆናል ያለውን ሲወስን ቆይቶ በግንቦት 2005 ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባዔ በወሰነው መሠረት፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት እና በሰባት ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ተደራጅቶ ላለፉት ሦስት ወራት የአድባራት እና የገዳማት ጥያቄዎችን በፍጥነትና በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት እንዲያገኝ ብርቱ ጥረት ማድረጉን በማውሳት፤ ይህን የበለጠ ለማጠናከር በሥልጠና መታገዝ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በሀገረ ስብከቱና በሥሩ ለሚገኙ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ይህ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሥልጠናውን መጀመር በይፋ አብሥረው ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና የሥራ መመሪያ በቤተ ክርስቲያን ከላይ እስከ ታች ባለው የሥራ ኃላፊነት ላይም ሆነ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የምንገኝ አጠቃላይ ሠራተኞች /አገልጋዮች/ ሁሉ እስከ አሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ያስጠፋውንና መልካም ስማችንን እያጎደፈ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ዘረኝነትና የጎጠኝነት መንፈስ ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማስወገድ ሁላችንም ታማኞች ሆነን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ዘመኑን የዋጀ አሠራርን መከተል እንደሚገባን ከገለጹ በኋላ የተቀመጥንበት ወንበር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሥራችን ቸልተኛ መሆን የለብንም ብለዋል፡፡ ቅዱስነታቸው አያይዘውም ለአዲሱ አደረጃጀት የለውጥ ሐዋርያነት ግንባር ቀደም ሆነን የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊነት፣ ጥንታዊነትና ሉዐላዊነት አስከብረን የቀደመ ስሟን አስመልሰን ሀብቷንና ንብረቷን በሕጋዊ አሠራር ተቆጣጥረን በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ በየደረጃው ያለን ሁላችንም አገልጋዮች የለውጥ ሰው ለመሆን፣ ለውጡን አምኖ ለመቀበል ሥልጠና በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዋናነት ይህን ዓላማ ከማስተግበር አንጻርም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለለውጡ አመራር ራሳቸውን በማስቀደም ከዚህ በፊትም ለመላው የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ሥልጠና እንዲሰጥ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ የዛሬውም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ለተመደቡት አገልጋዮች በየደረጃቸው የተዘጋጀ ሥልጠና በመሆኑ ተሳታፊዎችም በሥልጠናው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው አስምረውበታል፡፡

0761

ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው ብጹዕ ረዳት ሊቀ ጳጳሱም ሆኑ ከክቡር ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ በአጠቃላይ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች እስከ አሁን ላደረጉት የሥራ እንቅስቃሴ እና ላዘጋጁት የሥልጠና መርሐ ግብር ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበው፤ ወደ ፊትም እንዲህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጭምር ለሥልጠናው ተሳታፊ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ የዕለቱ መርሐ ግብር መሪ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሀዲስ ይልማ ቸርነት የሁለቱን ቀን መርሐ ግብር አስተዋውቀው ወደ ሥልጠና ተገብቷል፡፡ የሥልጠና ርዕሶችም “የለውጥ ሥራ አመራር ሥልጠና፣ የኦዲትና ኢንስቴክሽን /ክትትልና ቁጥጥር/ ሥርዓትና ሥልጠና እንዲሁም የሒሳብ አያያዝ ሥልጠና” በሚሉ አርዕስት ሲሆን፤ ሥልጠናውም የጉባዔውን በውይይት ባሳተፈ መልኩ የሚከተሉት ነጥቦችን ዳስሷል፡-

• ለውጥ በማንኛውም ተቋም ሊኖር የሚችል ክስተት መሆኑን

• በለውጥ ሂደት እንቅፋቶች ለኖሩ እንደሚችሉ

• ለውጥ ጠንካራ መሪን እንደሚፈልግ

• ለውጥ ለአንድ ተቋም ስኬት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚታይ መሆኑን እና ሌሎችም ነጥቦች በአቶ ታደሰ አሰፋ እና በአቶ ካሳ አወቀ

• አንድ ኦዲተር ሊኖረው ስለሚገባ ሙያዊ ክህሎት

• መሠረታዊ የኦዲትና ኢንስቴክሽን መርሆች

• ስለ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ዓይነቶች እና የኦዲት ባለሙያ ስለሚያቀርበው የሪፖርት ቅርጽ በዲ/ን ንጋቱ ባልቻ እና ዲ/ን ተመስገን ወርቁ

• ስለ መሠረታዊ የሂሳብ አሠራር መቅላላ ሂሳብ ሥራ መነሻ እና መድረሻ አስመልክቶ በአቶ ሞሐባ በስፋትና በጥልቀት በታዘዘላቸው ሰዓት ጊዜ ሰጥ በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት እንዲሁም በጥያቄና መልስ ንቁ ተሳትፎ በማድግ ሥልጠናው እንዲሰርጽ አድርገዋል፡፡ ከሥልጠናው የሚገኝ ግብዓት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከዋና ጽ/ቤቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አድባራትና ገዳማት ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የገንዘብ እና የንብረት ብክነት፣ ያለማቋረጥ የሚታየውን የሰዎች አቤቱታ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለው የመዋቅር ማስተካከያና ተከታታይ ሥልጠና ይበል የሚያሰኝ መልካም ጅምር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም በቅድሚያ በሀገረ ስብከቱና በየክፍላተ ከተሞች የምንገኝ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቁርጠኝነት በመነሣት፤ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት በፍጥነት ለመቅረፍ በእጅጉ ይረዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለተግባራዊነቱም የሥልጠናው ተሳታፊዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በተደረገው ውይይት አረጋግጠዋል፡፡

ተሳታፊውም ይህን ዓይነቱ ሥልጠና በሥራው ላይ ያለው አዎንታዊ ተጽእኖ መልካም ስለሆነ ወደ ፊትም እንዲቀጥል እየገለጸ የሚከተለውን የጋራ አቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ 

                                   የአቋም መግለጫ

1. እኛ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ሠራተኞች ሀገረ ስብከቱ የጀመረውን የለውጥ ሥራ አመራር ሂደት ሙሉ በሙሉ በመደገፍ አዲሱን አደረጃጀት ለመተግበር ቃል እንገባለን፡፡

2. እኛ የዚህ ሥልጠና ተሳታፊዎች ለዚህ የለውጥ እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውም አካላትን በጽኑ በመቃወም እና በመታገል ለመልካም አሠራር ሂደት አፈጻጸም እንተጋለን፡፡

3. የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ለአንድ ተቋም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተረድተን ሕግን የተከተለ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንዲተገበር እንተጋለን፡፡

4. በቤተ ክርስቲያናችን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲተገበር የበኩላችንን ሥራ እሰራለን፡፡

5. በቤተ ክርስቲያናችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲሰፍን ባለንበት የሥራ ኃላፊነት ላይ ጠንክረን በመሥራት የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር እናስጠብቃለን፡፡

6. በሀገረ ስብከቱና በክፍላተ ከተማ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ያለመሰልቸት እንሠራለን፡፡

7. የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ስም የሚያጎድፍ ብልሹ አሠራር አስወግደን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያላትን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነትና ሐዋርያዊነት ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በታማኝነት ለማገልገል ቃል እንገባለን፡፡ 8. ጊዜው በሚጠይቀው መሠረት የሥራ አመራር ለውጥ ለቤተ ክርስቲያችን ተልዕኮ መሳካት የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት ጠንክረን እንሠራለን፡፡

9. የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ከማንኛውም አስተዳደራዊ ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ሙያዊ ተግባሩን እንዲያከናውን እንደግፋለን፡፡

10. በሂሳብ አያያዝ ሥራ በኩል ያለውን ክፍተት በማረም በተሰጠን ሥልጠና መሠረት ዘመኑ በሚጠይቀው የፋይናንስ ሥርዓት ለማስተካከል እና ለመሥራት ጥረት እንናደርጋለን፡፡ ማጠቃለያ በተለይ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናው ከተጀመረበት ደቂቃና ሰዓት ጀምሮ በቦታው ከተሳታፊዎች ቀድመው በመገኘት ለሁሉም ሠራተኞች የአባትነት አርአያነታቸውን ያሳዩን በመሆናቸው እጅግ ምሥጋናችን የላቀ ነው፡፡ እኛም የሀገረ ስብከትና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሠራተኞች የብፁዕነታቸውን ፈለግ በመከተል በየተመደብንበት የሥራና የአገልግሎት ክፍል በርትተን ለመሥራት ከብፁዕነታቸው በተግባር የተተረጎመ ትልቅ የሥራ መመሪያ አግኝተናል፡፡

ብፁዕ አባታችን! እኛ ልጆችዎት ሌሊት ከቀን እየደከሙበት ያለውን የሥራ አመራር ለውጥ እና መዋቅር ተግባራዊ እንዲሆን ከልብ እንሠራለን፡፡

“አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ከማሁኬ ይብራህ ብርሃንክሙ በቅድመ ሰብእ ከመ ይርአዩ ምግባሪክሙ ሰናየ ወይሰብህዎ ለአቡክሙ ዘበሰማያት፤ የዓለም ብርሃን እናንተ ናችሁ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ በጎ ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ” ማቴ. 5፡12

እኵት እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ዘዘልፈ የአቅበነ ዘአውትሮ የሚጠብቀን የአባቶቻችን አምላክ ይመስገን አሜን!!

ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ 

1. ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ  ሰብሳቢ

2. ሊቀ ኅሩያን ሰርፀ አበበ – አባል

3. ቀሲስ አሉላ ለማ – ጸሐፊ

በመጨረሻም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በሥሩ ለሉ 7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ሥልጠና ተሰጠ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሥልጠናው ወደ ቀደመው ታሪካችን የሚወስድ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለውታል የመጀመሪያ መሪ አባት በመሆንዎ ደስ ሊሎት ይገባል በማለት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን አመስግነዋቸዋል፡፡የሐዋሪያት ቁልፍ የተረከብነው እኛ በመሆናችን ታሪካችን በአግባቡ ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡

በመቀጠል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የመጨረሻ የመዝጊያ ንግግር እንዲያደረጉ፤ቃለ ምዕዳንና መመሪያ እንዲሰጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የጋበዙ ሲሆን ቅዱስነታቸውም ቅዱስ ዮሐንስ አባጣ ጎርባጣውን አቅኑ እንዳለው ሁሉ እናንተም ይህን ልታቀኑ ይገባችኋል ብለዋል፡፡

ችግር ወጥቶ ካልተነገረ መፍትሔ አይመጣም እኛ ለመደበቅ ብንሞክርም ሊሆን አይችልም እናንተም በዚሁ ቆይታችሁ ብዙ እንደተወያያችሁ ይገባኛል፡፡አባቶቻችን በየዘመናቱ በሚችሉት ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል ዘመኑም የኮምፒውተር እና የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ እኛም ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፤ከዘመኑ ጋር ልንራመድ እና አሠራራችን ኮምፒውተራይዝድ ሊሆን ይገባል በማለት ሰፋ ያለ ንግግር እና ቃለ ምዕዳን የሰጡ ሲሆን በመጨረሻም ለ2 ቀን ሲካሄ የቆየውን ጉባኤው በፀሎት ዘግተዋል፡፡

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የለውጥ ሥራ አመራር ሥልጠና››)

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አገልግሎት››)

{flike}{plusone}

በሀገረ ስብከቱ አይቲና ዶክሜንቴሽን ክፍል

0021

የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ የ1ኛ ዓመት መታሰቢያ የፀሎት ስነ ሥርዓት ተካሄደ

0021

ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለዩት የ5ኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ኅልፈት የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዐት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በማሕሌት፣ በጸሎተ ፍትሐትና በቅዳሴ ታስቦ ውሏል፡፡

በመታሰቢያ ክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፤ ካህናትና ምእመናን የተገኙ ሲሆን በቅዱስነታቸው መሪነት ሙሉ ፀሎተ ፍትሐት ከደረሰ በኋላ ከሰዓት ፀሎተ ቅዳሴው ተከናውኗል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በ20 ዓመት የፕትርክና ዘመናቸው ለሀገራቸውና ለዓለም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደነበር በዚሁ የመታሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የአንደኛ ዓመት መታሰቢያ የፀሎት ስነ ሥርዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ባለው መካነ መቃብራቸው ላይ ተካሂዷል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐምሌ 1984 ዓ.ም ፓትሪያሪከ ሆነው ከተሾሙበት ጊዜ አንስቶ ለሀገር እድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ለ20 ዓመታት ሐወርያዊ ተልእኳቸውን በመፈፀምና ከፍተኛ አገልግሎት በማበርከት ለቅድስት ቤተክርስትያንና ለሀገሪቱ ታላላቅ ሥራዎችን ሰርተው ማለፋቸው ተገልጿል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ በስነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ በህይወት ዘመናቸው ለትምህርት መስፋፋት፣ ለሀገርና ለዓለም ሰላም እንዲሁም የኃይማኖት መቻቻልንም በሰፊው በማስተማርና በቤተክርስትያኗ ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እንድታበረክት በማስቻል ከፍተኛውን ሚና ያበረከቱ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ››)

በተያያዘ ዜና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ስነ ሥርዓት ነሐሴ 14/2005 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ባለው መካነ መቃብሩ ተካሂዷል፡፡

በመታሰቢያ ክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ሚኒስትሮች፤ ክብርት ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ፤ ካህናትና ምእመናን በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መካነ መቃብር በፀሎቱ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመታሰቢያ የፀሎት መርሐ ግብሩ ላይ ለተገኙ ምዕመናን ሠፊ የሆነ ትምህርተ ወንጌል ሠጥተዋል ፡፡

00020{flike}{plusone}

017

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ጾመ ፍልሰታን አስመልክተው ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳን

017

          

 

 

 

 

 

 

 

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

 1.  በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ
 2.   ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ
 3.  የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ
 4.   በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ
 5.  የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የተወደዳችኹ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ምእመናንና ምእመናት ልጆቻችን÷ እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለ፳፻፭ ዓ.ም. የቅድስት ድንግል ማርያም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኹ!!

‹‹ወኵሉ ዘሰአልክሙ በስምየ እገብር ለክሙ››፤ ‹‹በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለኹ›› ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ /ዮሐ.፲፬÷፲፫/

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለተከታዮቹ ከሰጠን ስጦታዎች አንዱ የምንሻውን ኹሉ በስሙ እየለመን ጥያቄአችንን የማስፈጸሙ ጸጋ ነው፡፡ እርሱን በስሙ እየለመን የምንሻውን ሁሉ ማግኘት እንደምንችል ቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ ደጋግሞ ያስረዳል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል በተረዱትና በተማሩት ትምህርት መሠረት ይህን ጸጋ ወዲያውኑ በሥራ አውለውታል፤ የለመኑትንም አግኝተውበታል፡፡

እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍቅር ስለኾነ፣ እኛ ሰዎች ፍቅር ኾነን፣ ፍቅርን መርሕ በማድረግ ስንለምነው መልሱ ይኹንታ እንደኾነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ኾኖ ቅድስት ድንግል ማርያምን በእናትነት ለቅዱሳን ሐዋርያት መስጠቱ የእናት ፍቅርና ክብር ከምንም በላይ መኾኑን ለማስረዳት እንደኾነ እንገነዘባለን፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ጌታችን ባዘዘውና ባስተማረው ትምህርት መሠረት የድንግል ማርያምና የሐዋርያት ፍቅር በልጅነትና በእናትነት ደረጃ ዘልቆአል፡፡ ሐዋርያዊት የኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከጌታችን ከሐዋርያት የተቀበለችውን የቅድስት ድንግል ማርያም እናትነትና ክብር ጠብቃ በተግባር እየፈጸመች ትገኛለች፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ በመጀመሪያ ቅዱስ ሥጋዋ ያለበትን ኹናቴ ለማወቅ፣ በሁለተኛ ትንሣኤዋንና ዕርገትዋን ለማየት ባደረባቸው የፍቅርና የአክብሮት ጉጉት ፈጣሪያቸውን በጾምና በሱባኤ ለምነው የልመናቸው መልስ በጥያቄአቸው መሠረት ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ማየት ኾኖአል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ትልቁ ቁም ነገር እንደ ጌታ ቃል በፍቅርና በሰላም ኾነን የምንለምነውን ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አዎንታዊ መልስ የምናገኝበት መኾኑን ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አምስት ቀን ለሁለት ሱባዔ በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት የምትፈጽመው አምልኮተ እግዚአብሔር ይህን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼና ወገኖቼ ምእመናንና ምእመናት

ጾማችንና ጸሎታችን ከእግዚአብሔር ፊት ደርሶ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ፍጹም ይቅርታና በረከት ሊያስገኝ የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የጾምን እንደኾነ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው ጾም በሕገ ቤተ ክርስቲያን ከተከለከሉ መባልዕትና መጠጦች መከልከል ብቻ ሳይኾን÷ ለተበደለና ለተገፋ ፍትሕን መስጠት፣ ለተራበ ቆርሶ ማጉረስ፣ ለታረዘ ቀዶ ማልበስ፣ የተጣላውን ማስታረቅ፣ የተሳሳተውን መክሮና አስተምሮ መመለስ፣ በአጠቃላይ በማኅበረ ሰቡ መካከል ፍጹም ሰላምና ፍቅር፣ እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲሰፍን ማድረግና የመሳሰሉት ሁሉ የጾም ወቅት ተግባራት ናቸው፡፡ በተለይም ስለ ሰላምና ፍቅር ስናስብ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ከዚያም እስከ ዓለም አቀፍ ያለውን ሰላም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ፣ ቀደም ብለው ካለፉት ዘመናት አሁን ያለንበት ዘመን የተሻለና ብሩህ ተስፋ የሚታይበት ቢኾንም፣ አሁንም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ቁልፍና ሀገራዊ ተግባር እንዳለ ሳናስገነዝብ አናልፍም፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ የኾነ ሁሉ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይከፋፍለው ለዘመናት የቆየውን ተፈቃቅሮ፣ ተከባብሮ በሰላምና በአንድነት የመኖር ጸጋችንንና ባህላችንን እንደ ዐይን ብሌን በመጠበቅ ወደ ጀመርነው የልማትና የዕድገት አጀንዳችን ብቻ እንድንመለከት ነው፡፡

ይህም እውን እንዲኾን የክርስቶስ ተከታይና የድንግል ማርያም ወዳጅ የኾነ ሁሉ አሁን በምንጀምረው ሱባዔ ፈጣሪውን ከልብ መለመን አለበት፡፡ በዚህ ዐይነት የምናቀርበው ጾምና ጸሎት የመጨረሻው ግቡ ፍቅርና ሰላም ስለኾነ ከእግዚአብሔር የምናገኘው መልስ ይኹንታ እንደኾነ በመገንዘብ ሁላችንም በሃይማኖት በመጽናትና ፍቅርን ገንዘብ በማድረግ መጾምና መጸለይ ይገባናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ጾሙን የሰላምና የፍቅር ጾም ያድርግልን፡፡ አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.

{flike}{plusone}

0011

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች የ3 ቀን የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥልጠና ተሰጠ


               በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

“ክፉውን ነገር ተጸየፉት ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ”ሮሜ 12÷9

0011

መልካም አስተዳደር ለዘላቂና ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሥልጠና የተጀመረው ሐምሌ 9/2005 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ሥልጠናው እየተካሄደው ያለውም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንገል አዳራሽ ነው፡፡

በዚሁ በዓይነቱ ልዩ የሆነው ሥልጠና ተካፋይ የሆኑ ሥራ ኃላፊዎች፡-

1. የሀገረ ሰብከት ሠራተኞች፣

2. የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች፣

3. የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣

4. የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የክፍል ኃላፊች፣

5. የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ናቸው፡፡

ሥልጠናውን በፀሎት የከፈቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ/ሀ/ስ/የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሓፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣንት በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የሥልጠናውን መርሃ ግብር የሚመሩት መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ ሲሆኑ ከፀሎቱ መርሃ ግብር በኃላ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ/ሀ/ስ/የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስ አማካኝት ስለ ሥልጠናው አስፈላጊነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠልም ከመንግስት ተወካይ አጠር ያለ ፀሑፍ ተነቧል፡፡ከዚህ በኋላ ወደ ሥልጠናው የተገባ ሲሆን ሥልጠናው ከፍተኛ ሞያ ባካበቱ በመንግስትና በግል የሚሠሩ ባለሞያዎች ሙሉ ሥልጠናው ተካሂዷል፡፡ተሰብሳቢዎችም ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ አድርገዋል ፡፡

ሥልጠናው በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት እና በአድባራትና ገዳማት የሚገኙ መሪዎችንና አገልጋዮችን የመሪነትና የሥራ ብቃት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ለታሰበው የአሠራር ለውጥ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የታቀደ ሥልጠና ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ስለ  ሥልጠናው  ዓላማ አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ሀ/ስብከቱ በአስተዳደር፣ በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በማኅበራዊ አገልግሎትና በምጣኔ ሀብት በኩል በሕግና ሥርዐት በመመላለስና በመደራጀት ውጤታማ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በርካታ ዕቅዶቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሀ/ስብከቱ የሚገኙ የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች በለውጡ አጀንዳዎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በዘርፉ የላቀ ክህሎትና ዕውቀት ባላቸው ባለሞያዎች የሥልጠናና ምክክር መርሐ ግብሩን ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ ከሀ/ስብከቱ የሥራ ግዝፈትና ካለው ሰፊ የፋይናንስ ፍሰት አንጻር ሲመዘን ችግሩ የተጋነነና የገዘፈ እንዳልኾነ የሚያምኑት ብፁዕነታቸው፣ ተጠቃሽ ጉድለቶችን ሲዘረዝሩ፡-

 1.  የመልካም አስተዳደር ግድፈትና ማሽቆልቆል፣
 2.  ዘመኑን የዋጀ የምጣኔ ሀብት አስተዳደርና ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር ክፍተት፣
 3.  የእርስ በርስ አለመናበብና የጎጠኝነት ስሜት፣
 4.  ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዐት አለመዘርጋት
 5.  የተአምኖ ግብርና እና የሥነ ምግባር ደረጃ ዝቅ ብሎ መገኘትና የመሳሰሉትን እንደኾኑ ጠቁመዋል፡፡

0003

ብፁዕነታቸው እንዳብራሩት፣ መልካም አስተዳደር÷ ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሥልጣንና ሓላፊነት የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት በሁሉም መስክ በጎ አርኣያነት ያለው መልካም እረኛ መኾን ማለት ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር መርሕ መሠረት ‹‹ሓላፊ ነኝ፤ አዛዥ ነኝ›› ከሚል መኮፈስ ይልቅ የአገልጋይነትና የመሪነት ስሜት መላበስ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹የምንመራትና የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት እንደመኾኗ መጠን የተቀበልነው አደራ እጅግ ታላቅና በልዑል እግዚአብሔር ፊት ቀርበን ዋናውን ከትርፍ ጋራ የምንጠየቅበት ነው፤›› ያሉት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ የምንመራቸው ሰዎችና የምናስተዳድረው ሀብት የእግዚአብሔር ሀብት ነውና ሓላፊነታችን እጅግ ከባድ እንደኾነና አገልግሎታችንም በዚሁ አቅዋምና መንፈስ ሊቃኝ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ሐምሌ 9/2005 በተጀመረውና በ11/2005 የሚጠናቀቀው የመጀመሪያው ዙር የሥልጠና መርሃ ግብር፡-

 1.  መልካም አስተዳደር እና ጠቀሜታው
 2.  የግዥ ሥርዐት፣ ተያያዥ ችግሮቹና የመፍትሔ አቅጣጫ
 3.  ዘመናዊ የፋይናንስ አሠራር፣ አያያዝና ተጠያቂነት
 4.  የዕቅድ፣ ቁጥጥር፣ ክትትል እና ግምገማ ሥርዐት
 5.  ውጤታማ መሪነት ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት
 6. ሙስናና ተያያዥ ችግሮች
 7.  የግጭት መንሥኤ እና አፈታት የሚሉ ርእሰ ጉዳዮች የተካተቱ ሲኾን የዘርፉ ባለሞያዎችና ምሁራን ከቤተ ክርስቲያናችን ተጨባጭ ችግሮች ጋራ በማዛመድ በሚያቀርቧቸው መነሻዎች ተሳታፊዎቹ ውይይት ሰፊ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የአሁኑን ጨምሮ በሁለት ዙሮች ከሚካሄደው የሥልጠናና ምክክር ጉባኤ ጋራ በተያያዘ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት እና በአዲስ መልክ በተሠራው መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረት በሚቋቋሙት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሓላፊዎችና ሠራተኞች ምደባ የካሄዳል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ቃል በገባው መሠረት ከሐምሌ 17/2005 በአዲሱ መዋቅር መሠረት ሙሉ ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ሀ/ስብከቱ ለመልካም አስተዳደር በሚያመቹ ሰባት የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የተዋቀረ ሲኾን በቋሚ ሲኖዶሱ ተሻሽሎ በጸደቀለት ልዩ መተዳደርያ ደንብ መሠረት በአግባቡና በሥርዓቱ ሥራውን መሥራት ያስችላል ይህ ልዩ ጊዚያዊ መተዳደርያ ደንብ እስከ ጥቅምት ወር ፳፻፮ ዓ.ም ብቻ በጊዜያዊነት የሚያገለግል ሲሆን የሥራ ምደባውም በትምህርት ዝግጅትና በአገልግሎት ዘመን እንደ ሆነ ለማውቅ ተችሏል፡፡

ይህን በተመለከተ ሀገረ ስብከቱ ሥራንና ሠራተኛን ለማገናኘት ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ በማስቀመጥ ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሂደት በቁርጠኝነት እንደሚከተል የፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የሥልጠናው መርሐ ግብር ዓላማ ባብራሩበት ወቅት አስረድተዋል፡፡

የብፁዕነታቸውን ሙሉ ንግግር ከዚህ ቀጥሉ እንደሚከተለው ይቀርባል

መልካም አስተዳደር ለዘላቂና ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት

“መኑ እንጋ ገብር ምዕመን ወጢቢብ ዘይሰይም እግዚኡ ውስተ ኩሉ ንዋዩ ከመ የሀቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ . . . ብፁዕ ውእቱ ገብር ዘመጺኦ እግዚኡ ይረክቦ እንዘ ዘንተ ይገብር” “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ልባምና ታማኝ ባሪያ ማነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚገኘው ያ! ባሪያ ብፁዕ ነው፡፡” ማቴ.24፡45፡፡

ብፁፁዕ ወቅዱስ አባታችን

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

ክቡራን እንግዶችና የዚህ አውደ ጥናት ተሳታፊዎች!

በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንደተነገረው፡- የምንመራትና የምናገለግላት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃት መስቀል የተሸከመላትና የተገረፈላት ብዙ መከራ የተቀበለላትና የሞተላት እንደመሆኗ መጠን የተቀበልነው አደራ እጅግ ታላቅና በልዑል እግዚአብሔር ፊት ቀርበን ዋናውን ከትርፍ ጋር የምንጠየቅበት ነው፡፡

0341

የምንመራቸውም ሰዎችና የምናስተዳድረው ሀብት የእግዚአብሔር ሀብት ነውና ኃላፊነታችን እጅግ ከባድ ነው፡፡ በመሆኑም አገልግሎታችን በዚሁ አቅዋምና መንፈስ የተቃኘ መሆን ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊት ታሪካዊት እና ብሔራዊት እንደመሆኗ መጠን ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ እድገት አያሌ አስተዋጽኦ ከማበርከቷም በላይ ሕዝቦቿም በማህበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎቶች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ውጤታማ ሥራዎች ሠርታለች እየሠራችም ትገኛለች፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ ተልዕኮ ለሰው ልጆች መንፈሳዊና ማሕበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት ነው፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያለምንም የሃይማኖት፣ የዘር፣ የጾታ ልዩነት ሳታደርግ ከሕዝቦች ሁሉ ጋር ተቀራርባ በመሥራት ሰብአዊ ተግባራትን ስትፈጽም ኖራለች፡፡ በዚሁም ማሕበራዊና የኢኮኖሚ ልማት ማስፋፋት ረገድ የራሷን ልዩ አስተዋጽኦ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት በጽኑ የምትደግፍ ብሔራዊት እና ጥንታዊነት ቤተክርስቲያን ናት፡፡

ከማህበራዊ አገልግሎት ባሻገር የትምህርት፣የሥነ ምግባር፣የኪነ ጥበብ፣የሥነ ልሳን ፣የሥነ-ጽሑፍ፣የቅርስና ሌሎችንም አያሌ እሴቶችን ስታስተላልፍ ቆይታለች፣ወደፊትም ትቀጥላለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህን መልካም ሥራ ለሀገራችን ስታበረክት ያለምንም ፈተና አልነበረም፡፡ በርካታ ፈተናዎች ተገዳድረዋታል፡፡ ሆኖም የሚደርሱባትን ፈተናዎች ሁሉ በብርቱ ታግላ በእግዚአብሔር አጋዥነት ድል አድርጋና ተቋቁማ እነሆ ክብርና ልእልናዋ ተጠብቆ ከዚህ ዘመን ደርሳለች፡፡

የብሔራዊነትና ዓለም አቀፋዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድ አካል የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሀገሪቱ ርዕሰ መዲና እንደመገኘቱና የቤተክርስቲያኗ ዋና የፋይናንስ ምንጭ እንደመሆኑ መጠነ ሰፊ የልማት ሥራ ቢከናወንም አንዳንድ ችግሮች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም ሀገራት ዲፕሎማቶች መናኸሪያ፣ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ፣ የተለያየ ባሕል ልምድና ፍላጎት መድበል በሆነችው በአዲስ አበባ የሚገኝ እንደመሆኑ፣ እንዲሁም ከሥራው ግዝፈትና ካለው ሰፊ የፋይናንስ ፍሰት አንጻር ሲመዘን ችግሩ የተጋነነና የገዘፈ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ ነገር ግን ያለውን ችግር ስንፈትሽ የተለያዩ ጉድለቶች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ይኸውም ፡ –

 1.  የመልካም አስተዳደር ግድፈትና ማሽቆልቆል
 2. ዘመኑን የዋጀ የምጣኔ ሀብት አስተዳደርና ዘመናዊ የሂሳብ አሠራር ክፍተት
 3.  የእርስ በእርስ አለመናበብና የጎጠኝነት ስሜት
 4. ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት አለመዘርጋት
 5.  የተአምኖ ግብርና የሥነ ምግባር ደረጃ ዝቅ ብሎ መገኘትና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

0319

ሐዋርያው “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔር መንጋ ጠብቁ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጎብኙት ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ፡፡” 1ጴጥ.5፡2 በማለት እንዳስተማረን መልካም አስተዳደር ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት ባለን አቅም የምዕመናንን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት በሁሉም መስክ በጎ አርአያነት ያለው መልካም እረኛ መሆኑን ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ በሀገረ ስብከቱ እና በሥሩ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት ይህ ትርጉም በአብዛኛው የተዛባ ይመስላል፡፡ በመልካም አስተዳደር መርህ መሠረት “ኃላፊ ነኝ፣ አዛዥ ነኝ” ከሚል ስሜት ይልቅ የአገልጋይነትና የመሪነት ስሜት መላበስ ተገቢ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሀገረ ስብከቱ በአስተዳደር፣ በፍትህ መንፈሳዊ በማኅበራዊ አገልግሎትና በምጣኔ ሀብት በኩል በሕግና ሥርዓት በመመላለስና በመደራጀት ውጤታማ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

 

ሀገረ ስብከቱ ወደፊት በርካታ እቅዶች ስላሉት ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሥሩ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በጉዳ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የላቀ ክህሎትና እውቀት ባላቸው የየዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት በማስፈለጉ ይህንኑ ቅድሚያ ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን፡፡

በቀጣይም ልዩ ልዩ የአጭርና የረዥም ጊዜ ሥልጠናዎችን እያዘጋጀን የየአድባራቱን መሪዎችና አገልጋዮች የመሪነትና የሥራ ብቁነት ደረጃ ከፍ እናደርጋለን ብለን እናምናለን፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሀገረ ስብከቱ ሥራንና ሠራተኛን በማገናኘት ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛ ቦታ በመስቀመጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው የአሠራር ሂደት በቁርጠኝነት ይከተላል፡፡ ለዚህም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን፣ ቅዱስ ሲኖዶስና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከናችን እንደሚቆሙ እምነታችን ጽኑዕ ነው፡፡

ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚደረገው ሥልጠና እና የምክክር ጉባኤ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች በተለያዩ ምሁራን ይዳሰሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም የጉባኤው ተሳታፊዎች ይህ መርሃ ግብር የተሳካ እንዲሆን ሁላችሁም የድርሻችሁን እንድትወጡ አደራ እያልኩ ንግግሬን እቋጫለሁ፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በረከት ይደረሰን፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

የኮርሱን ጽሑፍ ዳውንሎድ ያድርጉ (ውጤታማ መሪነት) የኮርሱን ጽሑፍ ዳውንሎድ ያድርጉ (ሙስና)

 

{flike}{plusone}

የሰልጣኞቹ የአቋም መግለጫ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል

 1. የቤተ ክርስቲያናችንን ሀብትና ንብረት በአግባቡ ማስተዳደር እንችል ዘንድ በስልጠና የታገዘ ዘመናዊ የሂሳብ አሰራርን እንጠ ቀማለን፡፡
 2. እኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች ኃላፊ ማለት አገልጋይ መሆኑን ተገንዝበን ካህና ትናንና ምዕመናንን በአገልጋይነት መንፈስ ለመምራት ቃል እንገባለን፡፡
 3. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ወደፊት በሚያዘ ጋጃቸው አቅምን የማጠናከሩ ስልጠናዎች በተሳታፊነት ለስልጠናው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ቃል እንገባለን፡፡
 4. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስራና ሰራተኛን በማገናኘት ተጠያቂነት ያለው አሰራር በሙሉ ለመዘርጋት በሚያደርገው ጥረት በሙሉ ልብና ፍላጎት እንሳተፋለን፣ ለተግባራዊነቱም የድርሻችንን እንወጣለን፡፡
 5. ከጥንት ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱ መገለ ጫዎች የሆኑትን የመልካም አስተዳደርና የምግባረ ሰናይ ገጽታዎች ጎልተው ይወጡ ዘንድ ተግተን እንሰራለን፡፡
 6. ቤተ ክርስቲያናችን ድህነትን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መብታቸው የተጓደለባቸውን ወገኖች በመደገፍ ድምጻቸው ሆና እንዳ ይገፉ ለመሟገት ያስችላት ዘንድ መልም አስተዳደር በቤተ ክርስቲያናችን እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡
 7. የቤተክስቲያናችን ተከታዮች ካህናትና ምዕ መናን ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲነግስባቸውና ሙስናን አድልዎንና ምግባረ ብልሹነትን የመሳሰሉ እኩይ ተግባራት እኛም ተጸ ይፈን ሌሎችም እንዲጸየፉት ለማድረግ እናስተምራለን፡፡
 8. መንግሠትና ሃይማኖት መለያየታቸው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ቢሆንም ከመንግሥት ጋር አንድ በሚያደርጉን በሰላም፣ በልማት፣ ጠንካራ ዜጋ በማፍራትና የሀገርን ገጽታ የሚያበላሹ ዕኩይ ተግባራትን አክራ ሪነትን ለመታገል ከመንግሥትና ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በህብረት እንሰራለን፡፡
 9. ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር ልዩነቶ ቻቸን እንዳሉ ሆነው ተቻችሎና ተከባብሮ ለመስራት ቃል እንገባለን፡፡
 10. ሃይማኖታችንን ለማስፋፋት በምናደርገው ሐዋርያዊ አገልግሎት ሕገ መንግሥቱን አክብረን እንቀሳቀሳለን፡፡
 11. በሐዋርያዊ አገልግሎትን ወቅት ግጭትን የሚፈጥሩ ነገሮች እንዳይከሰቱ ተግተን እንሰራለን፡፡
 12. ከእግዚአብሔር የተቀበልነው አደራ ዋና ውን ከነትርፉ ለማግኘት እንሰራለን፡፡
 13. ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊ፣ በማህ በራዊና በኢኮነሚያዊ ልማቶች የነበራት የፊት አውራሪነት ሚና ተጠናክሮ እንዲ ከናወን ኃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡
 14. በውስጣችን የሚታዩትን የመልካም አስተ ዳደር፣ ዘመኑን የዋጀ የምጣኔ ሀብት አስተ ዳደርና ዘመናዊ የሂሳብ አሰራር፣ የእርስ በእርስ አለመናበብና ጎጠኝነት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት አለመዘርጋት፣ ተአምኖ ግብርና የሥነ ምግባር ደረጃ ዝቅ ማለት ጉድለቶች እንዲስተካከሉ ብሎም እንዲወገዱ ጠንክረን እንሰራለን፡፡
 15. በተሰጠን ኃላፊነት ውጤታማ መሪዎች ለመሆን ቃል እንገባለን፡፡
 16. ተሰጥኦ ያላቸውን ተተኪ ሥራዎችን ለማ ፍራት ተግተን እንሠራለን፡፡
 17. ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን በጋራና በአን ድነት እንሠራለን ፡፡
 18. ራሳችንን በማብቃት ውጤታማ መሪዎች ለመሆን ጥረት እናደርጋለን፡፡
 19. ለቆምንለት ዓላማ የማያወላውል አቋም በመያዝ ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን የጣለችብንን አደራ እንወጣለን፡፡
 20. ግዥን በዕቅድና በስርዓት እንዲከናወን እና ደርጋለን፡፡
 21. የግዥ ስርዓቶቻችን ለብክነት እንዳይደረጉ በተሻለ ጥናትና በአንድ ላይ የሚፈጸምበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡
 22. ገንዘብ ሊያስገኝ የሚቻል ትክክለኛ ጥራት፣ መጠን፣ ዋጋ፣ ጊዜ፣ መሠረት ያደረገ የግዥ ስርዓትን እንከተላለን፡፡
 23. ለዚህም ተጨማሪ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ቢደረግ፣
md1

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማትና አድባራት ኃላፊዎች ከብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ/ሀ/ስ/የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስና ከአ/አ/ሀ/ስ/ዋና ስራ አስከያጅ ጋራ የትውውቅ መርሃ ግብር ተካሄደ

                                   በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

md1

ሰኔ 14/2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 2.30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ የትውውቅ መርሃ ግብሩ የተካሄደ ሲሆን በዚሁ ዕለት አዲሱ አስከያጅ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ/ሀ/ስ/የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስ አማካኝነት /ጋባዥነት ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ በተፈቀደላቸው መሠረት በአጭሩ ከጀመሪያ ጀምሮ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አሰከያጅነት እሰከ ተሶሙበት የነበረውን ሁኔታ ለተሰብሳቢዎች ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ዕለቱን የገልፅልያል ብለው ያሰቡትን ከመጽሐፍ ቅዱስ 2 ጥቅሶችን አንብበዋል፡፡ ክቡር ዋና ስራ አስከያጁ መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት እንደተናገሩት ለዚሁ ትልቅ ሐዋሪያዊ አገልገሎት በተሻለ መልኩ እንዳገለግል ለመረጡኝ መንፈሳዊያን አበቶቼ በተለይም ታላቁ የልማትና የሰላም አባት የሆኑትን ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን እንዳላሳፍር ድንግል ማርያም በሽልም ታውጣህ ብላችሁ ፀልዩልኝ ብለዋል፡፡አቅማቸው በፈቀደው መልኩ /መጠን የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ለማስፈፀም ሌት ተቀን ሊሠሩ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ኃላፊዎችና ሠራተኞችም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስረሰ አሰከያጅ ሆነው በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀውላቸዋል ፡፡ በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና የገዳማትና አድባራት ሠራተኞች በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ እና በዋና ስራ አስከያጁ በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መመደብ እጅግ በጣም ከመደሰታቸውም በላይ ሙስና እና ብልሹ አሠራርን በማስወገድና በማጥፋት ከፍተኛ የሆነ ሥራ ሊሠሩ ሁሉም ሠራተኞች ከፍተኛ የሆነ ተስፋ እንደጣሉባቸው ገልፀውላቸዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአ/አ/ሀ/ስ/የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀጳጳስ በበኩላቸው እንደተናገሩት ወደ ባህሩ ገብተን እ በንዋኛልን ወይም ደግሞ እንሰጥማለን ምክያቱም ከኋላ ሆነው የሚታዘቡን ብዙ ናቸው ብለዋል፡፡በመሆኑም የተጣለብንን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመወጣት በባለሞያዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አወቃቀርና አደረጃጀት፡-

1ኛው ከሐምሌ 1/2005 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት ያህል የሚገለግል ጊዚያዊ የሥራ አደረጃት እስከ መስከረም 30/2006 ዓ.ምሥራ ላይ የሚውል ሲሆን

2ኛው ሙሉ መዋቅርና አደረጃጀት ደግሞ ሥራውን ሙሉ ቡሙሉ ተጠናቅቆ ከጥቅምት 1/2006 ዓ.ም ጀምሮ በባለሞያዎች ተጠንቶና ተሠርቶ የቀረበውን በሚመለከታቸው አካላት ተገምግሞና ተስተካክሎ ሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡

md2

በመሆኑም ሥልጠኑን ወደ ታች በማውረድና የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎችን በቦታው ላይ በመስቀመጥ ሥራው ሊሰራ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በዚሁም መሠረት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ7 ክፍለ ከተሞች ተደራጅተው ከሐምሌ 1/2005ዓ.ም መደበኛ ሥራቸውን መሥራት እንደሚጀምሩ ገልፀው ገዳማቱና አድባራቱ ራሳቸው የሚገለገሉባቸው በመሆኑ አቅማቸው በፈቀደው መልኩ በፍላጎትና በውዴታ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መርዳት ብትችሉ መልካም ነው ባሉት አባታዊ ማሳሰቢያ መሠረት ፡-

1. 113 የሚሆኑ ገዳማትና አድባራት 1,158,900.00

2. 9 የሚሆኑ ገዳማትና አድባራት ሙሉ የሥራ አስኪያጆች (የሥራ ኃላፊዎች) ወምበርና ጠረጴዛ

3. 11 ገዳማትና አድባራት ዘመናዊ ኮምፒውተር ከነ ፕሪንተሩ

4. 11 ገዳማትና አድባራት ለክፍል ሠራተኞች ወምበርና ጠረጴዛ

5. 2 ገዳማትና አድባራት 2 ትላልቅ የአበባ ምንጣፎች

6. 1 ደብር 10 ወምበሮች እስከ ሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ ሁሉም ነገር አጠቃልለው ለሀገረ ስብከቱ ገቢ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን አሠራሩን ግልጽ ለማድረግ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ተወካዮች ቁሳቁሶቹን ለመግዛት በጉባዔው ተመርጠዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአዲስ መልክ የሚደራጁ የክፍለ ከተሞቹ ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

1. አራዳ ክፍለ ከተማ

2. አቃቂ ክፍለ ከተማ

3. ቦሌ ክፍለ ከተማ

4. ጉለሌ ክፍለ ከተማ

5. ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ

6. ነፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ እና

7. የካ ክፍለ ከተማ ናቸው፡፡

{flike}{plusone}

0001

የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ተጠናቀቀ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

0001

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ ከበዐለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የቅዱስ ሲኖዳስ ጉባኤ እንዲካሔድ በተደነገገው ቀኖና ክርስቲያን መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 21-30 ቀን 2005 ዓ.ም ተካሒዷል፡፡

ይህ ጉባኤ የርክብ ካህናት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ከላይ በተጠቀሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደተገለው ብፁዓን ሊቃነ ጰጳሳት በቤተ ክርሲቲያን ያለውን አጠቃላይ መንፈሳዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጉዳዮችን በማየት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ታላላቅ ውሳኔዎችን የሚወስኑበት ዓቢይ ጉባኤ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያናቸን ውስጥ ያሉትን ወቅታዊና ነባራዊ ጉዳችን ለመመርመርና ለመገምገም ባለው ሐዋርያዊ ኃላፊነት ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተልዕኮ አፈጻጸም እንቅፋት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በአጀንዳ ቀርጾ፣በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ማዕከል፣በባሕርይዋም ንጽሕትና ቅድስት ብትሆንም ኃጢአትና ስሕተት በነገሠበት ዓለም ያለች በመሆንዋ ከእርስዎ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ ተግባራት እንዳይጋቡባት የመጀመሪያው ጥበቃ በብፁዓን ሊቀነ ጰጳሳት ላይ ያረፈ ነው፡፡ በተለይም የአሁኑ ዓላማችን ጥበብ ባፈራው የአሠራር ዕውቀት በየቀኑ በለውጥ ጎዳና በሚራመድበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለሙ በተሻለና በበለጠ በመንፈሳዊ በአእምሮአዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት፣ማስተማርና ማገልገል ይጠበቅባታል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህ የተቀደሱ ተግባራት በሥራ ለመተርጎም ወቅታዊ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተመልክቶአል፡፡

በዚህ መሠረት ጉባኤው ብዙ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ዓበይት ውሳኔዎች አሳልፎል፡፡

1. በየሥራ ዘርፉ እየተከሠተ ያለው የመልካም አስተዳደርን ችግር በተለይም ብልሹ አስተዳደርና አሠራር፣ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናስ አያያዝ፣እንዲሁም ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮች ሁሉ ወሳኝ በሆነ መልኩ ለመቅረፍና ለማድረቅ፣ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያናችን በመሪ እቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር ለመቀየስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፡- ብፁዓን ሊቃናት ጳጰሳት፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዓቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን ለማጣርትና ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቶ በአንድ ድምጽ ወስኖል፡፡

2. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርና በፋይናስ አያያዝ፣እንዲሁም በስብከተ ወንጌልና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች አሁጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስ ሀገረ ስብከት መሆን ስለሚገባው በአንድ ሀገረ ስብከት፣ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጰስ እንዲመራ፣ እንደዚሁም በመልካም አስተዳደር ፣በፋይናንስ፣ አያያዝና በሰው ኃይል አመዳደብ የሕግ የበላይትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈፈላጊውን ክትትል ሁሉ በቋሚ ሲኖዶስ በመንበረ ፓትርያርኩ ጥልቅ ክትትል እንዲደረግ ፣ 3. የቤተ ክርስቲያናችን የሕይወት ምንጭ የሆነውን ስብከተ ወንጌል ትምህርት በሰው ኃይል ፣በሚዲያም ጭምር እየታገዘ በመላው ዓለም ላሉ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ትምህርቱን በጥራትና በጥልቀት ይሰጥ ዘንድ አስፈጻሚው አካል ጠንከር ያለ ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶሱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ምርጫ በየ3 ዓመቱ እንዲካሄድ ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ፤የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪጅ ፤ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አድርጎ ሲኖዶሱ መርጦአቸዋል፡፡

4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ፣እንደዚሁም የምስራቅና ሰሜን አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጰስ ሆነው እንዲሰሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

5. በመካከለኛው ምስራቅና በሎሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም መንግሰት እያደረገ ያለው ጥረት ቤተ ክርስቲያናችን በሙሉ ልብ እንደምትደግፈውና ለስኬቱም የበኩሏን እንደምትወጣ፣ለዚህም በየደረጃው ያሉ መምህራን ፣ካህናትና ሰባኪያን ሁሉ የዚህን ጎጂነት ደጋግመው በማስረዳትና በማስተማር ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ጠንክረው እንዲስተምሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

6. የሀገራችን ሕዝቦች ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቀው መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገሮች እኩል ለማስለፍ በሚደረገው ሁለንተናዊ የልማት ተግባር ቤተ ክርስቲያናችን ከሕዝቡና ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅባትን ሁሉ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ አረጋግጧል፡፡

7. ኢትዮጵያ ሀገራችን በሀገር ውስጥ፣ በምስራቅ አፍሪካ፣ በመላ አፍሪካ ከዚያም በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን፣ የሰው ልጅ እኩልነትና መብት እንዲከበር ፣ፍትሐዊ የሆነ የሀብት አጠቃም እንዲኖር ፣የአየር መዛባትን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ሀብት እንዲስፋፋ የምታደርገው ያላሳለሰ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያደነቀ የሀገሪቱን መልካም ዝናና በጎ ገጽታ ለመጠበቅ የበኩሉን ጠንክሮ እንዲሰራ አረጋግጦአል፡፡

8. በሀገራችን የዕድገት ሒደት ክፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ በመገንባት የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራው ተጠናቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደማታቋርጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያረጋግጣል፡፡

9. ሀገራችን ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የኅብረተ ሰቡን ጤንት ለመጠበቅ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለእናቶችና ለህፃናት እየተደረገ ያለው ልዩ የጤና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ኀብረተሰቡን ከማስተማርና የጉዳዩን ጠቃሚነት ከማስረዳት ባሻገር ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ይገላፃል፡፡

10. ከሀገር ውጪ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሚፈለገውን የአንድነት ውጤት ባያስገኝም የቤተ ክርስቲያኛችን አንድነትና ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን እንዲሁም ለሕዝባችን ያለው ትርጉም የላቀ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሚገነዘብ ሁኔታዎች ተመቻችተው የሰላም ውይይት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

11. ቅዱስ ሲኖዳስ የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ዕውቀት እየቃኘ ለሃይማኖት ፣ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንም ጊዜ በላይ የተዘጋጀ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ ተገንዝቦ እርሱም የበኩሉን ሥራ በቅን መንፈስ እንዲወጣ አበክሮ አሳስቧል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና መመሪያዎች ሁሉ ተፈጻሚነት ኖሮአቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት በሁሉም ደረጃና አካባቢ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት በሙሉ ልባቸው ሲሰለፉ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ነው፡፡ስለሆነም ለእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ለሕልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ተከታዮች በሙሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎችና መመሪያዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ በአጽንዖት በማሳሰብ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲካሄድ የሰነበተውን ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቅቆአል፡፡

እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ፣ይቀድስ ፣አሜን!!!

አባ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

{flike}{plusone}

ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

009

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

009
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 1.   በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤
 2. ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤
 3.   የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ፤
 4.   በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤
 5. እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ያበሠረን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ለ፳፻፭ ዓ.ም በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹እስመ ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ንቅረብ እንከ በልበ ጽድቅ›› ‹‹የሕይወትና የእውነት መንገድን አድሶልናልና ከእንግዲህ በቅን ልቡና ወደ እርሱ እንቅረብ›› (ዕብ. 10÷19) የሰው ልጅ ለማያረጅና ለማያልፍ ሕይወት የታደለ፣ በእግዚአብሔር አምሳልና አርአያ የተፈጠረ፣ እጅግ ክቡርና ታላቅ ፍጥረት እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ በምድር በሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ያለው የበላይነት ሥልጣንም ይህን ያረጋግጣል፡፡

{flike}{plusone}

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህን ያህል ጸጋ ቢኖረውም የተሰጠውን ክብርና ልዕልና በአግባቡ ጠብቆ መዝለቅ አልቻለም፤ በእግዚአብሔር ፊት በፈጸመው ከባድ በደል ምክንያት የተሰጠውን ጸጋና ክብር ከማጣቱም በላይ በሕይወት ፈንታ ሞትን፣ በእውነት ፈንታ ሐሰትን፣ በዘለዓለማዊነት ፈንታ ጊዜያዊነትን፣ በማያረጀው ፈንታ የሚያረጀውን ሕይወት ተላብሶ ወደ ምድረ ፍዳ ተባረረ፤ ከእግዚአብሔር ልጅነት ተራቁቶ ከማኅበረ መላእክት ተለየ፤ ረዳት የለሽና ጎስቋላ ሕይወት ተሸክሞ መኖር ጀመረ፡፡ ለእርሱ ያልተፈጠሩ የሞትና የመቃብር ጎዳናዎች እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በሰፊው ተጓዘባቸው፡፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ዓመታት ለሰው ልጅ የፍዳ፣ የመርገም፣ የኵነኔ ዓመታት ነበሩ፡፡ ሲኦልና ገሃነም የሰው ዘርን በአጠቃላይ ለመዋጥ አፋቸውን የከፈቱበትና ሰውን ሁሉ በመራራ ሥቃይ የማገዱበት፣ ገነትና መንግሥተ ሰማያት አንድ ስንኳ ለእነርሱ የተገባ ፍጡር የሌለ እስኪመስሉ ድረስ ባዶአቸውን የቀሩበትና ተዘግተው የነበሩበት መራራ ጊዜ ነበር፡፡ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ እንደመኾኑ መጠን በሰው በደል ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱን ቢያስተላልፍም ከፈራጅነቱ ጎን ለጎን መሐሪነቱን የማያርቅ ለፍጥረቱ እጅግ ሩኅሩኅ ነውና በሰው ላይ የተላለፈው የሞተ ነፍስ ፍርድ በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት እንዲያከትም አደረገ፤ የተዘጋው የገነት በር እንዲከፈት፣ በሲኦል የተጋዙ ነፍሳት ወደ ገነት እንዲመለሱ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰው ጉዞ ወደ ሲኦል መኾኑ ቀርቶ ወደ ገነት እንዲኾን በማድረግ ሰውን በክርስቶስ ደም ታረቀው፡፡ በዚህ ታላቅ መሥዋዕትነት ያረጀውን የሲኦል መንገድ ዘግቶ አዲስ የገነት መንገድን ስለከፈተልን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ÷ ‹‹አዲስ የእውነትና የሕይወት መንገድ ከፍቶልናልና ከእንግዲህ ወዲህ በቅን ልቡና ወደርሱ እንቅረብ›› እንዳለ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ኀይላችን ወደ እርሱ ልንቀርብ ይገባል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

ያረጀው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ኾኖአል፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ሁሉ አርኣያና መሪ እንደመኾኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝ ሲያደርግ እኛም በሐዲስ መንፈስ በሐዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደገና ወደአረጀውና ወደአፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም፡፡ አዲስ ሕይወት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ መድኃኒት እንዲኾን በላከው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ድኅነትን ማግኘት ነው፤ ምንም ዐይነት አማራጭ የማይገኝለትን ይህን የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ የሰው ዘር ሁሉ ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ ሊቀበለው ይገባል፤ በዚህ በኩል ካልኾነ ሌላ የምንድንበት መንገድ የምናመልጥበት ዐውድ ፈጽሞ የለምና፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደተቀመጠው የክርስትና ሃይማኖት በመልካም ሥነ ምግባር ገዝፎ የሚታይ ሃይማኖት እንጂ በእምነት ብቻ ተደብቆ የሚኖርበት ሃይማኖት አይደለም፤ በርቀት ያለችው ነፍሳችን በግዙፉ ሥጋ ኾና በምትሠራው ሥራ አማካይነት በአካላችን ውስጥ እንዳለች እንደምናውቅ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም መልካም ሥራን አብዝቶ ሲሠራ በሥራ ገላጭነት ሃይማኖቱ ገዝፎ በጉልሕ ይታያል፤ በመኾኑም በክርስትና ሕይወት ሃይማኖትና ሥነ ምግባር እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው በአንድነት ሲኖሩ ሕይወተ ነፍስን እንደሚያጎናጽፉ ልብ ብሎ ማስተዋል ይገባል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ በሚመነጨው መርሕ መሠረት በሥራ በመትጋትና በፍጹም ፍቅር በመኖር ሕይወታችንን ይበልጥ ልናሳድገው ይገባል፤ ከሁሉ በፊት ሰው የተፈጠረው ለሥራና ለክብር እንደኾነ ከቶ ልንዘነጋው አይገባም፤ ይህም ከኾነ ሰው ለአንዲት ደቂቃ ያህል እንኳ እጅ እግርን አጣጥፎ ያለሥራ ሊቀመጥ እግዚአብሔር አልፈቀደም፤ አይፈቅድምም፡፡ በሐፈ ገጽከ ብላዕ ኅብስተከ፤ ወደወጣኽበት መሬት እስክትመለስ ድረስ ጥረኽ ግረኽ ላብኽን አንጠፍጥፈኽ ብላ ነውና የሚለው (ዘፍጥ.3÷19)፡፡ በዙሪያችንም ኾነ በሌላው አካባቢ የተሻለ ኑሮና ክብር ያላቸው ኾነው የሚታዩ ሁሉ የመክበራቸው ምስጢር ጠንክረው መሥራታቸው እንደኾነ በውል ልናጤነው ይገባል፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም በታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እንደሚታየው ኻያ አራት ሰዓት ሙሉ በትጋት ከሠራን በአጭር ጊዜ ሌሎች የበለጸጉ አገሮች ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም፤ ዋናው ቁም ነገር ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ በመተማመን፣ በመቻቻል ለሥራና ለሥራ ብቻ መነሣቱ ላይ ነው፡፡ ይህ ኹኔታ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የምናየው ስለኾነ ለምንጣደፍለት የዕድገት ሽግግር ትልቅ መሣርያችን መኾኑን ዐውቀን እንደ ዐይን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል፤ ይህ የኾነ እንደኾነ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ በአገራችን የተጀመሩትን ታላላቅ ሥራዎች ኹሉ ያለጥርጥር ማሳካት እንችላለን፡፡ ‹‹የእውነትና የሕይወት መንገድ አድሶልናልና፤›› የሚለውን የፋሲካ ትምህርተ ሃይማኖት የሕዳሴውን ልማት በማፋጠንና በማሳካት ልንገልጸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ታላቁን የፋሲካ በዓላችንን ስናከብር ለእኛ ብሎ፣ በእኛ ፈንታ መሥዋዕት ኾኖ የዘለዓለም ሕይወትን ካጎናጸፈን ጌታ ጋራ ማክበር አለብን፤ ፋሲካን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ማክበር የምንችለው የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትንና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ነው፡፡ ስለኾነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖቱ፣ ከተቀደሰ ሥነ ምግባሩና ባህሉ በወረሰው ሥርዐት መሠረት እንደተለመደው በዓሉን በሰላም፣ በፍቅር፣ በስምምነትና በመረዳዳት፣ ድኾችን ይዞ በመመገብ በመንፈሳዊ ደስታ እንዲያከብር መንፈሳዊ መልእክታችንንና ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የተቀደሰና የተባረከ የፋሲካ በዓል ያድርግልን፤ እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

{flike}{plusone}