2

በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. በየዓመቱ የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በድምቀት ተከበረ


ታኅሣሥ 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

                    በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

በመጀመሪያ እንኳን ለኃያሉ መልአክ ለሊቀ መላእክት ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን፡፡

እኛ የምናመልከው አምላክ ኪሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፡፡ ት.ዳን.3፥17

በየዓመቱ ታህሳስ 19 ቀን የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በዚህ ዓመትም እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ውልዋል፡፡በዓሉ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባለበት ሁሉ ተከብሮ የሚውል ሲሆን ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናትና መዘምራን እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ሥነ ስርዓት በየአመቱ ሁል ጊዚ ተከብሮ ይውላል፡፡በዘንደሮ ዓመትም እንደተለመደው በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡

በተለይም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ባሉ የቅዱስ ገብርኤል አጢቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉ በድምቀት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ምእመናንም ተኝተዋል፡፡በተለይም በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እጅግ በደመቀ ሁኔታ በአሉ ተከብሮ ውሏል፡፡በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ፤ካህናት፤መዘምራንና ብዛት ያለቸው ምዕመናን በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

 

2

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከታህሳስ 19 ቀን ጀምሮ ሲሆን የገዳሙ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምረው ለ32 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ ለእምነቱ ተከታዮች ምእመናን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እጀግ በጣም የሚያስደንቅ በዓል ነው፡፡

ዛሬ የምናከብረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከባቢሎን እሳት ያዳነበት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው በብሉይ ኪዳን ዘመን ከ605-562 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነገሠው በናቡከደነጾር ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከጣዖት አምላኪና አስመላኪ ኀያላን ነገሥታት መካከል አንዱ ናቡከደነጾር ነበር፡፡ ምስሉ የቆመው በ587 ቅ/ል/ክ እንደሆነ መተርጎማን ያስረዳሉ፡፡ ዳን.3፥1 ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን በማረከበት ዘመን ዳንኤልንና ሦስቱን ሕፃናት በልዩ ሁኔታ አክብሯቸው ነበር፡፡ 

 • ዳንኤልን ብርጣሶር አለው አሰበ በል አምኃ ቤል ሲል ነው
 • አናንያንም ሲድራቅ አለው ወልደ ሰቃየ አትክልት /አትክልተኛ/ ማለት ነው
 • ሚሳኤልንም ሚሳቅ አለው ፀሐቂ ተጋሂ ፍንው ለግብር መልእክት /ትጉህ ፈጣን መልእክተኛ/ ማለት ነው፡፡ 
 • አዛርያንም አብደናጎም አለው ገብረ ዳጎን /የጣዖት አገልጋይ/ ማለት ነው

1

የቀድሞ ስማቸው ትርጉም ግን 1)ዳንኤል ማለት ፍትሕ እግዚአብሔር ዳኛ እግዚአብሔር

2)አናንያ ማለት ደመና 3)ሚሳኤል ማለት ሰምዓኒ እግዚአብሔር /እግዚአብሔር ስማኝ/ 4)አዛርያ ማለት ረድኤት ማለት ነበር፡፡ ት.ዳን.1፥7 ንጉሡ እነዚህን ሕፃናት ለሦስት ዓመት በቤተ መንግሠት ጥሩ ምግብ እየተመገቡ የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያጠኑ ዘንድ አዝዞ ነበር፡፡

እነርሱ ግን ትምህርቱን እየተማሩ በንጉሡ ቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ሳይመገቡ ጥራጥሬና ውኃ እየተመገቡ በፈተና ያለፉ ነበሩ፡፡ ዳን.1፥8-21 ጠቢባንና አስተዋዮች በመሆናቸው በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ተሾሙ፡፡ ዳን.2፥46-49 የሠለስቱ ደቂቅ በንጉሡ ዘንድ መወደድና መሾም ያስቀናቸው ባቢሎናውያን ለናቡከደነጾር “በባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሸምካቸው ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ አምላክህን ያላመለኩ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉ” ብለው ከሰሷቸው ያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጣና እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ እነርሱም አንሰግድም አሉ፡፡ ዳን.3፥13-19”

ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ለምስሉ ለማሰገድ ጥረት አድርጓል 1. በመጀመሪያ ዐዋጅ በማወጅ ነው ይህ ዐወጅ ከተራው እስከ ባለሥልጣናቱ ያሉትን የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም ባለሥልጣናቱ ቀድመው በመስገድ አርአያ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡ 2. ሁለተኛው የሕዝቡን ልብ በሙዚቃ እንዲደሰቱ በደስታው ተውጠው ሳያስቡት እንዲሰግዱ ማድረግ 3. የመጨረሻው በማስፈራራት /ወደ እሳት ትጣላላችሁ እያለ/ እንዲሰግዱ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢያባብልና ቢጥር ሠለስቱን ደቂቅ ለማሰገድ ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም፡፡

ከሠለስቱ ደቂቅ ሦስት ነገሮችን እንማራለን ማመን፣ መቁረጥ እና ማድረግን፡፡ ሃይማኖት እነዚህን 3 ነገሮች ይፈልጋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት በእግዚአብሔር ፍጹም አመኑ፣ ይህንንም እምነታቸውን ሲገልጡ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል” በማለት ተናግረዋል፡፡ የመጣባቸውን ሁሉ ለመቀበል ወሰኑ ቆረጡ “አምላካችን እኛን ማዳን ይችላል ነገር ግን ፈቃዱ ከዚህ እሳት ገብተን ሠማዕትነትን እንድንቀበል ቢሆን ከእሳት እንገባለን” በማለት አንድ ልብ፣ አንድ ቃል ሆነው አቋማቸውን ገለጡ፡፡ የቆረጡትን ነገር አደረጉት፤ ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ሦስቱም ነገሮች ስለተፈጸሙ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እሳቱን አብርዶ አዳናቸው፡፡

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” በማለት የተናገረው ቃልም ተፈጽሞላቸዋል፡፡ /መዝ.33፥7/ ጠባቂ መልአካቸው ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ውስጥ ገብቶ ከመከራ ሥጋ አድኖአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና መልአኩል ልኮ የፈጸመውን ትድግና ያየው ናቡከደነጾር “ናቡከደነፆርም መልሶ፡- መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡” ዳን.3፥28-30

  የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል  ተራዳኢነትና አማላጂነት አይለየን አሜን ፡፡

 

 

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጋራ ልምድ ልውውጥ ጉባኤ ተካሄደ

                         በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በግብፅ ኮብፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጋራ ትብብር በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሰፊ የልምድ ልውውጥ መርሀ ግብር በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተካሂዷል፡፡ይህ ጉባኤ ከታኅሣሥ 11-15 ቀን 2005 ዓ.ም. ለአምስት ተከታታይ ቀናት ልምድ ልውውጡ የተከናወነ ሲሆን በአምስቱ ዕለታት በየቀኑ እስከ አንድ ሺሕ የሚሆኑ የተለያዩ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ሰባኪያነ ወንጌልና እንዲሁም ከሁሉም የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የተውጣቱ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች የዚሁ ትልቅ ጉባኤ ተሳታፊ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል ፡፡

በዚሁ የጉባኤው መክፈቻ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ እና የኢሊባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ጸሐፊና የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሊቀ ጳጳስ ፤ብፁዕ አቡነ ቢመን የላዕላይ ግብፅ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ቄስ ዳውድ ለሜይ የግብፅ መንበረ ማርቆስ ካቴድራል ካህን፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአድባራት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና የቅዱስ ጳውሎስ ሰዋሰወ ብርሃን ከፈተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ተገኝተዋል፡፡

በመቀጠልም ዐቃቤ ርእሰ መንበሩ ግብፅና ኢትዮጵያ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን አስታውሰው የቆየ ቤተሰባዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የመጡ ግብፃውያንንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አመስግነዋል፡፡በመቀጠል ቄስ ሶምሶን በቀለ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች አይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ መምሪያ ሓላፊ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት አምስት ቀናት የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮረው የልምድ ልውውጡ በከፍተኛ መነቃቃትና ፍላጎት እንደተካሄደ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እነዚህን ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ያላቸው ብቃት እንደተጠበቀ መሆኑን የገለጡት ቄስ ዳውድ ለሜይ በሥርዓት አፈጻጸሙ ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል በተጨማሪም ምእመናን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት፣ የሚታይና የማይታይ ጸጋ ለማግኘት እነዚህ ምሥጢራት ከሕይወታቸው ጋር አስተሳስረው ሁል ጊዜ በማንኛውም ቦታ በየትኛውም ጊዜ የምስጢራት ተካፋይ መሆን እንደሚያስፈልግ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ልዑኩ በአጽንኦት ገልጠዋል፡፡ በመሆኑም ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በዝርዝር ማወቅ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን በማብራራት ይልቁንስ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመጠንከር፣ ከዲያብሎስ ቀስት ለማምለጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ ለመቃኘት፣ ምስጢራቱን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በተግባር መትግበር እንደሚገባም አክለው ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ከደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን በጋር በመሆን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ሦስት ወጣቶችም በገና እየደረደሩ ዝማሬያቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ስንሰማ ንጉሥ ዳዊት በዓይነ ኅሊናዬ ይመጣል በመጽሐፍ ቅዱስ የተዘረዘሩት የዜማ መሣሪያዎች መልካቸቹውን ሳይቀይሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ መዝለቃቸውን አድንቀው ለወደፊት ይህ ትውፊት ሳይቋረጥ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በእነሱ በኩል ከሁለት የዘለለ የዜማ ዕቃ እንደሌላቸው ያስታወሱት ቄስ ዳውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጣዕመ ዜማ እጅግ የሚመስጥና ደስ የሚል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በዝማሬያችን የተመሰጡት ግብፃውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም በፍጹም ተመስጦ ለመዘመር ሲሞክሩ እንደነበር ከቦታው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በአረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተለያዩ መዝሙራትን በማቅረብ የዝማሬውን መልእክት ቄስ ዳውድ አብራርተዋል፡፡ የልምድ ልውውጡ በጎ ገጽታ እንዳለው እና ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዕለቱ ከተገኙ ተሰብሳቢዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡እኛም እንዲህ ዓይነቱ በጎ ጂምር ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው እንላለን፡፡

ለመሆኑ ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያን ሐዋሪያዊና ማኀበራዊ አገልግሎት ለምን ለምን ይጠቅማል?

ቀደምት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በወቅቱ በተሰጣቸው ጥበብ በየአገሩ ቋንቋ እየተገለፀላቸው ዓለምን እየዞሩ እግዚአብሔር በሰጣቸው ፀጋ የዓለምን ሕዝብ ክርስትናን አስተምረዋል፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ጥበብን ሁሉ የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ታዲያ እግዚአብሔር እውቀትንና ጥበብን የሚሰጥ መሆኑን ካመንን እግዚአብሔር እውቀቱንና ጥበቡን ሰጥቷቸው የተሠራውን ቴክኖሎጂ ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት ብንጠቀምበት ጥቅሙ/ ጉዳቱ ያመዝናል? በእኛ አመለካከት ቴክኖሎጂዉን በመጠቀም የዓለምን ሕዝብ ማስተማር ይቻለል፣ የቤተክርስቲያኒቱንም ታሪካዊ ቦታዎች ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡ ወቅታዊ የሆኑ የቤተክርስቲያን ጉዳዮችንም ለዓለም ሕዝብ በተለያየ ቋንቋ ማሠራጨት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ፡-    

 1. በቪዲዮ ኮንፈረንስ
 2. በቻቲንግ
 3. በቴሌ ኮንፈረስ
 4. በኢሜል . . .

በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በቪዲዮና በመሳሰሉት የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮም ይሁን ማሕበራዊ ጉዳዮችን በቀላሉ ማዳረስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በቴክኖሎጂው የማይከናወኑና የግድ በአካል በቤተክርስቲያን በመገኘት የሚከናወኑ ሥርዓቶች አሉ፡፡እነሱም፡-ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ማለትም ሚስጥረ ጥምቀት፣ ሜሮን፣ ቁርባን፣ ክህነት፣ ንስሐ፣ ተክሊል እና ቀንዲል ሲሆኑ ከእነዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ ስብሐተ ነግህ፤ የሰርክ ጸሎት፤ ሰዓታት፤ማኀሌት፤ፍትሐት እና የመሳሰሉት በዚህ ቴክኖሎጂ አይከናወኑም ነገር ግን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮችን ማከናወን ይቻላል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ምእመናን የቤተክርስቲያኒቱ ልሳናት ወይም ሚዲያዎች የሆኑትን ለይተው ማወቅና መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስሙ የቤተክርስቲያን የሆነ ነገር ግን በድረገጹ  የሚለቀቀው ጽሑፍ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነና ቤተክርስቲያኒቱ የማታውቃቸው ልዩ ልዩ የግል ድርጅቶች በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ ብዙ ችግር እየፈጠሩ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ምእመናንንም ሆኑ ልዩ ልዩ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች በቤተክርስቲያኒቱ ፈቃድና እውቅና ተሰጥቶአቸው በሚመለከታቸው አካላት ታምኖባቸው የተለቀቁ ሳይቶችን ብቻ ብትጐበኙ መልካም ነው እንላለን፡፡

በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አዲስ ድረ ገጽ ተሠርቶ በሥራ ላይ ዋለ

                    

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለተገልጋዩ ማህበረሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና አሠራሩም ዘመኑ የሚፈቅደውን ሥራ ለመሥራት ታስቦ ባለ 3 ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ ማሠራቱን ተከትሎ በሀገረ ስብከቱ ሊኖሩ ከሚገባቸው ሥራዎች አንዱ ሀገረ ስብከቱንና በሀገረ ስብከቱ ያሉትን አድባራትና ገዳማት እንዲሁም በየገዳማቱና አድባራቱ ያሉትን ታሪካዊ ቦታዎችን ሊያስተዋውቅ የሚችልበት፤ ምዕመናን ወቅታዊ የሆነ የሀገረ ስብከቱ ሃይማኖታዊም ሆነ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉበት ድረ ገጽና የኢንተርኔት አገልግሎት በወቅቱ በነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ከፍተኛ ጥረት ተደርጐ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሀገረ ስብከቱ ድረ ገጽ አየር ላይ ውሎ እንደነበረ ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም አዲሱ የሀገረ ስብከቱ  ሕንፃ በሚመረቅበት ወቅት ቴክኖሎጂውን ሊያስጠቅሙ የሚችሉ፡-

 1. ከ15 ያላነሱ ዘመናዊ ኮምፑውተሮች፣
 2. የተለያዩ ቪዲዮ ካሜራዎችን፣
 3. ዲጂታል ላይብሬሪ ሊሰጥ የሚችል ዘመናዊ ላይብረሪ፣
 4. የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫና መቆጣጠሪያ ክፍሎች ለአገልግሎት ተዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተስተጓጉሎ ቆይቷል፡፡

ከ2ዐዐ2 ዓ.ም. ጀምሮ እሰከ 2ዐዐ4 ዓ.ም. አጋማሽ ተጀምረው የነበሩትን ጥሩ የሥራ  ጅምሮች ግን ማስቀጠል አልተቻለም፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ ድረ ገጹም ይሁን የኢንተርኔት አገልግሎቱ ሥራ ላይ ባይውልም ከሐምሌ 2ዐዐ4 ዓ.ም. ጀምሮ ከ2 ዓመታት በፊት ተጀምሮ የቀረውን በአዲሱ የሀገረ ስብከቱ አመራር ሰጪነት የድረ ገጹም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ሥራ እንደገና ሊሠራ ችሏል፡፡ በቀጣይም ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች እንዳሉ ሆነዉ ይህን ሥራ እንዲሠራ ያደረጉ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ሠራተኞች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በተለይም በሥራው ወቅት ያሳዩት የሥራ ትብብር በቃላት መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው፡፡ ከባለሞያው በተጨማሪ ለዚሁ ሥራ ሌት ተቀን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ የኮሚቴ አባላትም ከፍተኛ የሆነ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡