በጉራጌ ሀገረ ስብከት በምሁርና አክሊል ወረዳ ሥር የሚገኘው የሴባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ መልከጸዴቅ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጉራጌ ሀገረ ስብከት በምሁርና አክሊል ወረዳ ሥር የሚገኘው የሴባ አቡነ ተክለሃይማኖት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ እና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል።

የሴባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 5 ቀን 2005 ዓ.ም መሠረተ ድንጋይ በወቅቱ የጉራጌና የሀድያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ቀለሜንጦስ ተቀምጦ ከ9 ዓመታት የግንባታ ቆይታ በኋላ እንደተጠናቀቀ ተገልጿል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩንቨርስቲ ምክትል ዲን ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ካሣ፣የሀገረ ስብከቱና የወረዳ ቤተክህነቱ የሥራ ኃላፊዎች: የገዳማት እና የአድባራት፣የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና ምእመናን ተገኝተዋል ሲል የኢኦተቤ ቲቪ በፌስቡክ ገጹ አሳውቋል።

ዝርዝር መረጃውን ይዘን እንመለሳለን።

በመ/ር ሽፈራው እንደሻው

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-

 1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
 2. ፌስ ቡክ ገጽ:- አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት/Addis Ababa Diocese
 3. ቴሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

4.ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese

በዓለ ሆሣዕና

ከላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ)
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላለቅ በዓላት አንዱ የሆሣዕና በዓል ነው፡፡ ስለዚህ በዓል አስቀድሞ ትንቢት ተነግሯል፤ ከትንቢቶቹም አንዱ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያና በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ትን. ዘካ. 9÷9)፡፡

በዚህም መሠረትነት ስለበዓሉ አራቱም ወንጌላውያን ጽፈዋል፡፡ ይህም፡- ማቴ. 21÷1-11፣ ማር. 11÷1-10፣ ሉቃ. 19÷28-40፣ ዮሐ. 12÷12-15 አራቱም ወንጌላውያን የጻፉት የበዓሉ ታሪክ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ቀርቦ ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፡፡ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ገና ማንም ያልተቀመጠባት አህያ ከውርንጫይቱ ጋር ታስረው ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ አላቸው፡፡ የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፡፡ እነርሱም አህያዋንና ውርንጫዋን ሲፈቱ የአህያው ባለቤት አህዮቹን ስለምን ትፈቷቸዋላችሁ? አላቸው እነርሱም ለጌታ ያስፈልጉታል አሉ ወዲያው አመጡለት፡፡ የታሠሩትን ፈትታችሁ አምጡልኝ ማለቱ ሰው ሁሉ ከኃጢአት ማሠሪያ የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ለማጠየቅ ነው፤ ደቀ መዛሙርቱም ልብሳቸውን በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ጎዘጎዙ የዚህም ምስጢር ኮርቻ ይቆረቊራል ልብስ አይቆረቊርም የማትቆረቊር ሕግ ሠራህልን ሲሉ፤ አንድም ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ (በደልን የምትሸፍን) ነህ ሲሉ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያዋና በውርንጭዋ ላይ በጥበብ በአንድ ጊዜ ተቀምጦባቸዋል ለእርሱ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ በአህያ የተቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብዕ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉና ዘመነ ሰላም ደረሰ ሲል ትንቢቱን ባወቀ አናግሯል ምስጢሩም በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጉኝ አልገኝም ከፈለጉኝ አልታጣም ሲል ነው፡፡ ሲሄድም ሕዝቡ ልብሳቸውን በመንገድ አነጠፉ፡፡ እንኳንስ አንተ የተቀመጥክባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነው፡፡ እንዲሁም ሕዝቡ ሕፃናቱ ሳይቀሩ ዘንባባ ይዘው የሚቀድሙትም የሚከተሉትም ሕዝብ “ሆሣዕና ለወልደዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር” (ለዳዊት ልጅ መድኃኒትን መባል ይገባዋል፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው) ሆሣዕና በአርያም እያሉ ያመሰግኑ ነበር፡፡ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡ የዘንባባው ምስጢርም፡- አብርሃም ይስሐቅን ይስሐቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፣ እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋልና በዚህ መሠረት ሕዝቡ፡- የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲሄድ ዘንባባ ይዘው አመስግነውታል፡፡ እንዲሁም ዘንባባ እሾኻም ነው ትምህርተ ኃይል፣ ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል ባሕርይህ አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሲያመሰግኑ ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ መምህር ሆይ፡- ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ መልሶም እላችኋለሁ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግናሉ አላቸው፤ ድንጋዮች ሳይቀሩ ያመሰገኑበት ዕለት ነው፡፡

በዚህ መሠረት ይህ በዓል የምስጋና በዓል ነው፡፡ እኛም ፈጣሪያችንን ሁልጊዜ ማመስገን አለብን የተፈጠርነውም ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ ነው፡፡ ስሙን ለመቀደስ ማለት ስሙን ለማመስገን ማለት ነው ክብሩን ለመውረስ ማለት ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ማለት ነው፡፡ የተፈጠርነው ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል፡፡ ምስጋናውም በፍጹም እምነት፣ በቅንነትና በንጹሕ ልብ መሆን አለበት፡፡ “እባርኮ ለእግዚአብሔር በኵሉ ጊዜ ወዘልፈ ስብሐቲሁ ውስተ አፋየ” (እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ነው) (መዝ. 33÷1)አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን ሁልጊዜ አመስግነን መንግሥቱን ለመውረስ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም ቅዱሳን በአማላጅነታቸው ይርዱን፡፡

ለበዓለ ሆሣዕና ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ትንሣኤውም በሰላም ያድርሰን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ምሥጢር ማለት ቃሉ የግሪክ ቋንቋ ሆኖ ቃሉ ከግዕዝና ከአማርኛ በቀጥታ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ድብቅ ፣ ስውር፣ ሽሽግ፣ ረቂቅ ፣ ለቅርብ ዘመድ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን ይኸውም የፍጡር ሚሥጢርና የፈጣሪ ሚስጥር በመባል ይታወቃል፡፡ የፍጡር ምስጢር ሁለት ይዘት አለው፡፡ የሰውና የመላዕክት ምስጢር ይባላል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው የፈጣሪ የእግዚአብሔር ሚስጥር ይህ የከበረ የተወደደ የሚናፈቅ የበረከት ስጦታ ነው፡፡ ብርሃነ አለም ሀዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል በከበረ ቃሉ ገልፆታል፡፡ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ /በክርስቶስ/  አምናችሁ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱን የነብሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ በማይናገርና ክብር በሞላበት ሀሴት ደስ ይበላችሁ”፡፡ በማለት ስውር ረቂቅ ከሆነው ጸጋ እግዚአብሔር የምንሰጠው ሀብት መሆኑን በማብራራት ገልፆታል፡፡ በዚህ መሰረት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ከሚፈጸሙት ሚስጥራት በቁጥር 7 ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ውሳኔነታቸው ለሰባቱ ሰማያት ስብዐተ እግዚአብሔር ለማይከፈልባቸው ከተሞች ገላጭ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰባት ሚስጥራት ቤተክርስቲያን የሚስጥርነታቸው ምክንያት በአይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚህ ሚስጥራት አማካኝነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡ አበው ሲናገሩ በንባብ የተሰወረ ብሂል ምስጢር ይባላል ብለው ስውርነቱን ረቂቅነቱን ይናገራሉ፡፡ ሰባቱ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን የሚባሉት እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ፡፡

 1. ጥምቀት
 2. ሜሮን
 3. ቁርባን
 4. ክህነት
 5. ንስሀ
 6. ቀንዲል
 7. ተክሊል ናቸው፡፡

1. ሚስጢረ ጥምቀት

ይህ ምሥጢረ ጥምቀት ከኃጢያት ነፃ የምንሆንበት ከዲያቢሎስ አገዛዝ አርነት የምንወጣበት ከእግዚአብሔር በጸጋ የምንወለድበት የምስጢር አይነት ነው፡፡ በቅሰዱሳት መጻህፍት እንደተገለጸው በነብየ እግዚአብሔር በቅዱስ ሕዝቅሌል  ት.ሕዝ 36፡25 “ጥሩ ውሀንም ጥምቀትን እረጫችኋለሁ፡ እናንትም ትጠራላችሁ ከርኩስነታችሁም ሁሉ ከጣኦቶቻችሁ ሁሉ አጠራችኋለሁ አዲስ ልብ እሰጣችኋለው” በማለት የዚህን ምስጢር ክብርነት በረከትነት አምልቶ አስፍቶ ተናገሯል፡፡ በዚህ ሀሳብ ሌሎች ንፁሐን አበው ሀዋርያት ተባብረውታል፡፡ በምልአት ሰብከውታል፡፡ የሐዋ.2፡38 ፣ 1ቆሮ 6፡11 ፣ ዮሐ. 3፡5  ፣ ኤፌ 5፡26 ፣ ገላ 3፡27 ፣ ቲቶ 3፡5  ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምንገባበት ምስጢር ነው፡፡ ከመጸሕፍ ቅዱስ ውስጥ ጥምቀት ብዙ ምሳሌዎች ይኖሩታል፡፡ እነሆ ከማየአይኅ የዳነበትን መርከብ ቅዱስ ጴጥሮስ የጥምቀት ምሳሌ እንደሆነ ገልጾታል፡፡ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ምዕመናን ከሐጢያት ከጥፋት የሚድኑት በጥምቀት ነውና
 ቅዱስ ጳውሎስም እስራኤል ከግብጽ የባርነት ቀንበር ተላቀው የኤርትራን ባህር ተሻግረው ወደምድረ ርስት ያደረጉትን ጉዞ የጥምቀትን ምሳሌ አድርጎ አመስጥሮታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 10፡1-2 ምዕመናን ባህረ ኃጢያትን ተሻግረው ምድረ ርስተ መንግስተ ሰማያትን  የሚወርሱት በጥምቀት ነውና፡፡ ዳግመኛም ይህ ብርሃናዊ ሐዋርያ ጥምቀትን በሞትና በመቃብር ይመስለዋል፡፡ ሮሜ 6፡3-4 ቆላ 2፡12 በሞት ጊዜ ነፍስና ስጋ እንደሚለያዩ በጥምቀትም አሮጌው ሰውነት ይሞታል ይቀበራል አዲስ ሰውነት አዲስ ሕልውናን ይጀምራልና፡፡

2. ምስጢረ ሜሮን

ይህ ቃል የጽርዕ ቋንቋ ነው ትርጉሙም መአዛ ያለው የሚያውድ ፣ የሚጣፍጥ፣ ልብ የሚመስጥ ፣ ጣዕም ያለው መልኩ ጽርየቱ ዘይት ነው፡፡ በግዕዝ ቅብዕ፣ ቅብዐ ሜሮን ይባላል፡፡ ከብዙ እጽዋት ተቀምሞ የሚሰራ ነው፡፡ ሕዝበ እስራኤልን የሚያስተዳድሩ የእግዚያብሔር እንደራሴዎች ነገስታትን መሲሀን የሚባሉት ለዚህ ቅብ ተቀብተው ስለሚነግሱ ነው፡፡ ዘፍ 20፡23 1ኛ ሳሙ 10፡1 ዘዳ 28፡41 1ኛ ሳሙ 9፡6 1ኛ ነገስት 1፡34 ይህ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር የሚገለገልባቸው የቤተመቅደስ ነዋያተ ቅድሳትን አስቀድሞ በዚህ መታተም አለባቸው፡፡ ከተቀቡ በኋላ ለቤተ መቅደስ እንጂ ለተራ አገልግሎት አይውሉም ስለ ቅብዐ ሜሮን ቅዱስ መጽሐፍን የፃፉ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ቅብዐት ይሉታል፡፡ 2ኛ ቆሮ 1፡21 ዮሐ 2፡20 ቅብዕን በመንፈስ ቅዱስ ማህተምን ይሉታል፡፡ ኤፊ 1፡13  ፣4፡30 ይህ ቅብዓ ማህተመ ሕይወት በመሆኑ ለአገልግሎት ይውላል፡፡

3. ምሥጢረ ቁረባን

ይህ ቃል የሱርስት ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም አምኃ ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሥጋውና ደሙ የተሰጠን በነፃ ያለ ዋጋ ሳይገባን በችሮታ ነውና፡፡ በቤተክርስቲያን ምሥጢራት ሁሉ መደምደሚ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ መስዋዕት ማቅረብ የተጀመረው በአዳም ጊዜ ሲሆን ከአዳም እስከ ሙሴ የተነሱ አበው ሁሉ በህገ ልቦና ለእግዚአብሔር መስዋት ይሰው ቁርባን ያቀርቡ ነበር፡፡ መስዋዕታቸው ከእንሰሳ ቁርባናቸው ከእህልና ከአትክልት ማለት ከስንዴ እህል፣ ከወይን ፍሬ የሚቀርብ ነው፡፡ ዘመነ ኦሪት በብሉይ ኪዳን በሙክራብ የተሰዋ እንሰሳት ሁሉ በአዲስ ኪዳን በቤተክርስቲያን ለሚሰዋው ሁሉ የክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር፡፡ መልከ ጼዴቅ ያበረከተው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከት ለአምላክ የሥጋውና የደሙ ምሳ ሆነው አልፈዋል፡፡ ከምሥጢራት አንዱ መሆኑ ሕብስቱ ተለውጦ የክርስቶስ ሥጋ ጽዋው ተለውጦ የክርስቶስ ደም ሲሆን አይታይም፡፡ ነገር ግን እምነት ያለው ሁሉ በእምነት መነጽር ይመለከተዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሳይታይ የሚወደድን ሕይወት ለማግኘት ከቁርባን በፊት ንስሐ መግባት ለአስራ ስምንት ሰዓት መጾም አለበት፡፡ ንጽሕናውን በጠበቅ አለበት፡፡ መምክረ ካህን ጸንቶ መገኘት ያስፈልጋል፡፡

4. ምሥጢረ ክህነት

ይህ ቋንቋ የግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡ ተክህነ አገልገለ ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ ክህነት የተጀመረው በአባታች አዳም ነው፡፡ ክህነት የአገልግሎት ስም ሆኖ የቤተክርስቲያን ከፍተኛ መንፈሳዊ ማዕረግ ነው፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ በልጅነት አክብሮ ነብይና ካህን አድርጎ ሾሞ በኦሪት በወንጌል ሥርዓት እስኪወሰን ድረስ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ የነበሩ አበው በበረከት አበው ከእግዚአብሔር እየተሾሙ ትንቢትን ክህነት ከቅዱሱ መንፈስ እየተቀበሉ (እየተሾሙ) በነብይነታቸው ያለውን የሚመጣውን ሲገልጽ ሲያስተምሩ በሀብተ ክህነታቸው መስዋዕት ሲቀርቡ ነበር፡፡ ክህነት በዘመነ ኦሪት ለሌዊ ነገድ ከተሰጠ በኋላ ሲወርድ ሲወራረድ እስከ ክርስቶስ ደርሷል፡፡ ታላቁ ሊቀ ካህናት እየሱስ ክርስቶስ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋዕት እንሰሳ ሳሆን እራሱን መስዋዕት፣ እርሱ ሰዋዒ ሆኖ ወደ መቅደስ ገብቷል፡፡ ዮሐ 20፡22 ማሬ 18፡18  1ኘና ቆሮ 4፡1 ማሬ 28፡20

5. ምሥጢረ ንስሐ

ይህ ቃል የግዕዝ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም በሰሩት ኃጢያት መጸጸት ምነው ባልሰራሁት ባላደረኩት ብሎ ማልቀስ ወደ ኃጢያት ላለመመለስ መወሰን፣ በሕጉ ጸንቶ ለመኖር ቃል መግባት፡፡ ክርስቲያን በጥምቀት ከአለም ክፉ ስራዎች ሁሉ የተለየ ነው፡፡ ህይወቱ ለክርስቶስ የተሰጠ ነው፡፡ ሮሜ 12፡1 የመጨረሻው ግቡና ዓላማው ሥርየተ ኃጢያትን ማግኘት እና የዘላለም ሕይወት መወረስ ነው፡፡ አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ 1ቆሮ 6-19

6. ምሥጢረ ቀንዲል

ይህ ቃል የላቲን ቋንቋ ነው ትርጉሙም ፍፁም መብራት ማለት ነው፡፡ ከሰባቱ ሚስራት አንዱ ቀንዲል ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘይት የፈውስ ምልክት ነው፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው የሚሰቃዩ ህሙማን ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ቁስለኞች እየተቀቡ ይፈወሱ ነበር፡፡ ኢሳ 1፡6 ሉቃ 10፡34 ራዕ 3፡18 ማር 6፡13  ይህ ቅብዓተ በሐዲስ ኪዳን ለሚጠመቁ ከሚደረግ ቅብዐ ሜሮን ጋር ግንኙነት የለውም ራሱን የቻለ ሕሙማነ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ሕሙማነ ነፍስ ኃጥአን የሚቀቡት ፈውስ የሚያገኙበት ነው፡፡ ማር 6፡13 ያዕ 5፡13-15 ራዕ 1፡17፡፡

7. ምሥጢረ ተክሊል

ይህ ማለት “ተከለለ” ተቀናጀ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ በሥርዓተ ጋብቻ ቅደም ተከተል መሰረት በመተጫጨት እና በቃል ኪዳን የተመሰረተ ጋብቻ በተክሊል ይፈጸማል፡፡ ቤተክርስቲያን ምስክርነት የሚፈጸመው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የሚያሰጥ ስለሆነ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ትክክለኛነቱም የሚታወቀው በተክሊል ሥጋወ ደሙ ሲፈጸም ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ትክክለኛነቱም የሚታወቀው በትክሊል ሥጋወ ደሙ ሲፈጸም ነው፡፡ ዘፍ 1፡27-28 ፣ 2-18 ማቴ 19-4 እነዚህን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አውቀን ተረድተን የእምነታችን ፍጻሜ የሆነውን አምላካችንን ለተፈጠርንለት ዓላማ በመገዛት የነፍሳችንን መዳን ልናረጋግጥ ይገባል፡፡

ለዚህም ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር እንዲረዳን የወላዲተ አማላክ አማላጅነት እንዳይለየን የጻድቃን ፀሎት የቅዱሳን በረከት እንዳይለየን ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!!!

መንፈሳዊ ፎቶዎችን ይመልከቱ

{gallery}pic-spiritual{/gallery}

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የትምህርቱ አስፈላጊነት( የጥናቱ አስፈላጊነት)

 • የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የእምነቱ መሠረትና መነሻ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን በሚገባ ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም ለሌላውም ለማሳወቅና  ለማስረዳት ስለሚያስችል፤
 • መጽሐፍ ቅዱስን በግልም ሆነ በማህበር ስናነብና ስናጠና ዋና ሀሳቡንና ትርጉሙን በቀላሉና በቶሎ እንዲገባን ሊያደርግ የሚያስችል በመሆኑ፣
 • በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ በቂ መረዳትና ችሎታ እንዲኖር፣ የአጠናን ዘዴዎችን ከአወቁ በኋላ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን እንድንሆን፣
 • የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ስብከትና ትምህርት ሲሰጡ በምንማርበትና በምንሰማበት ጊዜ እየተረዳንና እየገባን በፍጥነት መከታተል እንችላለን፡፡
 • በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነሱ ማንኛውንም ጥያቄ ለመመለስ ከማስቻሉም በላይ ለሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለመመስከር እና ለማስተማር እንድንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚገባ ያስተዋውቀናል፡፡ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲኖረን ያለማምደናል፡፡

የትምሕርቱ ዓላማ( የጥናቱ ዓላማ)

 • መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው የፍቅር ምልክት እንደመሆኑ መጠን ዓላማው ሰዎችን የመጥቀምና ሕይወትን የሚሰጥ የፍቅር ዓላማ ነው፡፡
 • በዓለም ላይ ያለውን የአለፈውን የአሁኑንና የወደፊቱን ሁኔታ የሚታየውንና የማይታየውን ድርጊት እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ማስረዳት፣
 • የእግዚብሔር ሐሳብ እና የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ እቅዱን፣ ፈቃዱን ለሰው ማሳወቅ
 • ሰዎችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዲያምኑና አምነውም በደሙ ሕይወት እንዲሆንላቸው መግለጽ፡፡ ዮሐ.2ዐ-30
 • የመዳንን መንገድ ማሳወቅ ፣  ዮሐ.6፡4ዐ ፣አቆሮ 1፡21    ዮሐ.2ዐ፡31
 • ለሐጢአተኞችና ለጻድቃን የሚከፈለው ዋጋ ማሳወቅ
 • የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ማስተማር  ዮሐ.2ዐ፡31
 • አጠቃላይ መግቢያ መስጠት እንዴት፣ በእነማን፣ የት አካባቢ እንደተጻፈ ማሳየት
 • 81 መጽሐፍት አጠቃላይ ሁኔታ ስም፣ ይዘት፣ ወዘተ… ማስጠናት
 • በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ አውቆ ለመመለስ ማስቻል
 • በቅዱስ መጽሐፍ መመሪያ እና ሥርዓት ለመኖር ማሳየት
 • መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር ምልክት ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ተፋቅረው እግዚአብሔርን በመውደድ ለቃሉም በመታዘዝ የክብር ትንሳኤና ዘለዓለማዊነት፣ በተስፋ እንዲጠብቁ ይገልጻል፣ ያነቃቃል፡፡

መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ እስከዛሬ በዓለም ካሉት መጻሕፍት ይልቅ እጅግ ታላቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህም ረጅም ዘመናት በመቆየት በዓለም ላይ ተወዳጅ ከመሆኑም በላይ ብዙ አንባቢዎችን በማግኘት ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ሌሎችን መጻሕፍት ብናነባቸው እውቀትን ከመስጠት የሚያልፉ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለሰዎች ሕይወት ብርሃንና መንገድ ነው፡፡‹ እኔ የነገርኳችሁ ቃል መንፈስ ነው፡፡ ሕይወትም ነው፡፡› እንዳለ ዮሐ. 6፡63 ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ለጊዜው አንብበን የምንተወው መጽሐፍ አይደለም፡፡

ምክንያቱም፡- መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትና ሃይማኖት መመሪያ እንደመሆኑ መጠን የቤተ ክርስቲያን ልጆች አማንያን ሁሉ ይልቁንም አገልጋዮች በሚገባ ሊያውቁት ያስፈልጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሥራቹ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም እንኳን ፍጹም አምላክ ቢሆንም ደግሞም ፍጹም ሰው ነውና በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሊማር ት/ቤት ገብቶ እንደነበረ ‹ ተአምረ እየሱስ‹ የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ይናገራል፡፡ በሉቃ.2፡48 ላይ እንደተገለጸው ገና በአሥራ ሁለት ዓመቱ ከመምሕራን ጋር በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ጥያቄ ሲጠይቅ ለሚጠይቁት መልስ ሲሰጥ መጻሐፍትንም ሲጠቅስ የሚሰሙት በማስተዋሉና በእውቀት መመለሱ ሁሉንም አስገርሞአል፡፡ ጌታ በጥበብና በቁመት በሞገስም ያድግ እንደነበረ ተጽፏል፡፡ ሉቃ.2፡52፡፡

በማስተማር ዘመኑም ቢሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ለሚሰሙት በቂ ትምህርት ለሚጠይቁትም አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ የጽሑፍን ጥበብ ለሰው ልጆች የገለጸው አምላካችን እግዚአብሔር በሄኖክ ዘመን የፊደላትን መልክ በሰማይ ሰሌዳ ላይ አሳየ፡፡ ዘፍ.4፡26፡፡ ከዚያም በኋላ የሰው ልጆች የፊደላትን መልክ ለይተው ማወቅና ማጥናት በሕሊና የሚመላለስ ሀሳብ በአፍም የሚነገር ቃል እንዳይረሳ በመጽሐፍ ተጽፎ የታወቀ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ባገኘው ትውልድ በሄኖክ ዘመን ለሰው ልጆች ጽሕፈትን አስተማረ፡፡ ኩፋ.5፡22-24፡፡ ሁሉን በጊዜው ገልጦ ያሳየ አምላክ በስጋ ተገልጦ ሰው ሆኖ በሚመላለስበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡     ‹መጻሕፍትን ካላመናችሁ ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?› ዮሐ. 5-47፡፡ ላይ በማለት እምነት በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በኋላ እንኳን በኤማሁስ መንገድ ለተገለጠላቸው ሁለቱ ቀደመዛሙርት ባለማስተዋላቸው ከገሰጻቸው በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ያለውንና የተነገረውን ተርጐሞላቸዋል፡፡ ለሐዋርያትም ቢሆን መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከተፈላቸው፡፡ ሉቃ.24-27፡፡
ከዚህ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ  እየተመሩ ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት ስለሆነ ስሕተት የሌለበት መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች፡፡ ይህንንም ታስተምራለች፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳን ሰዎች ላይ አድሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲጽፉ ምስጢርንና እውቀትን ከሚገልጽባቸው መንገዶችና ዘዴዎች መካከል፣

1ኛ. ቃል በቃል፡- ባርያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ እርሱ በቤቱ ሁሉ የታመነ ነው፡፡ እኔ አፍ ለአፍ በግልጽ እናገረዋለሁ፡፡ በምሳሌም አይደለም፡፡ ዘኁ.13፡7-8

ልበ አምላክ ዳዊትም፡-የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበረ፡፡ 2 ሳሙ.23፡2፡፡

2ኛ.  በሕልም፡- ዮሴፍም ሕልምን አለመ ለወንድሞቹም ነገራቸው፡፡ ዘፍ.37፡5፡፡

3ኛ.  በራዕይ፡- በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ በራዕይ እገለጽለታለሁ፡፡ ዘኁ.12፡6

ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡ 2.ጴ.ጥ.1.21

4ኛ. በመጽሐፍ እንዲጽፉ፡-በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፡፡ በኋላየም የመለከትን ድምጽ የሚመስል ትልቅ ድምጽ ሰማሁ፡፡ የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ለአብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ፡፡ ራዕ.1፡1ዐ፡፡ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ቅዱስ መጽሐፍ በቅዱሳን ሰዎች እንደተጻፈ ቢነገርም በራሳቸው ሀሳብ ወጥተው ወርደው አመንጭተው ሳይሆን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርተው ጽፈዋቸዋል፡፡ ብዙ ሊቃውንትም የሚስማሙበት አንድ የሚሆኑበት ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ሥራ መለኮታዊ ነው ይላሉ፡፡

ይህም ማለት የሰዎች ቃልና የሀሳባቸው ፍሬ ሳይሆን እግዚብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ከናፍር ያናገራቸው በሰዎች ብዕር ያጻፋቸው ናቸው ማለት ነው፡፡ ኢሳ.34፡16፣ ኤር.36 በሌላ አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ዓይነት ደራሲ(አዘጋጅ)አለው፡፡ ሰው ሁለተኛው ደራሲ ሲሆን መጀመሪያውና ዋናው ደግሞ በእያንዳንዱ ደራሲ ላይ አድሮ ያሳሰበ፣ የመራ ያመለከተ እንዲሁም በእውቀትና በጥበብ ተሞልቶ የገለጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ ልዑል እግዚአብሔር የፈለገውን እንዲጽፍ፣ እንዲናገር ሰዎችን የሚያነሳሳ መሆኑ ከታወቀ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት የራሱ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እና ቃል ናቸው፡፡ ይህም ኦሪት፣ ነቢያት፣ ጽሕፋት እንዲሁም ሐዋርያት በወንጌላቸውና በመልእክታቸው በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ነገ.2፡8-16፡፡ ነህ.8፡ኤር.25፡1-23  2ጢሞ 3፡17፡፡

ከላይ እንደተመለከትነው የሰዎች ድርሻ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን በጽሑፍም ሆነ በቃል ማስተላለፍ ሲሆን በሁለተኛ ደራሲነታቸው በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በቅርፀት፣ በጽሕፈት የመጣላቸውንና የተገለጠላቸውን ቃል አስተውሎና ጠንቅቆ በመያዝ እንዲሁም በተሰጣቸው እውቀት በጽሑፍ በማስተላለፍ አስተዋጾ አላቸው፡፡ ከዚህ በቀር ለመናገርም ሆነ ለመጻፍ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን እንጂ ከራሳቸው አመንጭተው እግዚአብሔር እንዲህ አለ በማለት አይናገርም፡፡ ኤር.1፡7፡፡ ሕዝ.2፡7፣ አሞ.3፡7፣ 1ነገ 22፡7፡፡

ምክንያቱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተውና ተነድተው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ሰዎች ከተለያዩ የሥራ መስክ የተጠሩ ናቸው፡፡ ከዚህም  ሌላ በተለያዩ ዘመንና በተለያዩ አህጉር የኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹም አይተዋወቁም ነበር፡፡ ሆኖም የጻፉአቸውን መጻሐፍት የጻፋቸው አንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ቃሉም ሆነ መልእክቱ ፈጽሞ አይጋጭም፡፡(አይጣላም፡፡)

ጸሐፊዎች በችሎታቸውና በእውቀታቸው የተለያዩ ሆነው ሳለ በእግዚአብሔር መንፈስ የጻፉአቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ዋና ሀሳብና መልእክታቸው አልተለያየም፡፡ በዚህም ምክንያት እኛ ለሕይወታችን መመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን የበላይ አድርገን ተቀብለነዋል፡፡ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ስልጣን ይባላል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን በውስጡ የያዘ የእግዚአብሔር የቃሉ መዝገብ ነው፡፡ በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት በኋላ ዘመን በአንድነት ተሰባስበው የሚገኙበት መጽሐፍ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም በአንድነት እርስ በእርሳቸው ሳይፋለሱ የሚናገሩት ለሰው ልጆች የተላለፈውን የእግዚአብሔርን መልእክት ነው፡፡

ስለዚህ ከልጅነታችን ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን መማር፣ ማወቅ፣ ማጥናትና ማስተዋል እንደሚገባ እንረዳለን፡፡ ሐዋርያት ያስተምሩ የነበረውም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጥቀስ ነበር፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና፡፡ ሮሜ.15፡4

ስለሆነም ለማንኛውም ትምህርት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ከሕጻንነታችን ጀምሮ ማወቅና ማጥናት አለብን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በተማረውና በተረዳው ነገር ጸንቶ እንዲኖር ከመከረው በኋላ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ የሚችሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሚያውቅ መስክሮለታል፡፡ 2ኛ ጢሞ.3፡114-15 ራሱም ቅዱስ ጳውሎስ የሚያነባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ነበሩት፡፡ 2ኛ.ጢሞ.4፡13፡፡

ነገር ግን ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንማርም ሆነ ስናጠና በመንፈስ እንጂ በሥጋ መሆን የለበትም፡፡ በሥጋዊ ስሜት መጻሕፍትን መመርመር ሕይወት አይገኝበትም ‹እናንተ መጻሕፍት የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ ጌታ የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ.5፡39›

ስለዚህ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመንፈስ ሆነን እግዚአብሔር በሚሰጠው ማስተዋል መርምረን በሕይወታችን እየተረጐምን እንደ መጻሕፍት ሁሉ እኛም ስለጌታችን ልንመሰክር ይገባናል፡፡ በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ሁሉን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳንን ጽሑፍና እውቀት አምላካችን ይስጠን አሜን፡፡

ነገረ መለኮት (Theology)

<<Theology >> የሚለው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት ማለትም ‹‹Theo›› እና ‹‹logy›› የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ Theo›› ማለት ‹‹God›› ማለት ሲሆን ‹‹logy›› ደግሞ study or knowledge የሚል ቀጥተኛ ትርጉም አለው፡፡ በመሆኑም ‹‹Theology›› (የነገረ መለኮት) ማለት ስለ እግዚአብሔር የማይጨበጠውን፣የማይላጠውን፣ የማይገመተውን እንዲሁም ከሰዎች አእምሮ በላይ የሆነውን ጌትነቱንና አምላክነቱን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው መጠን ሰዎች የሚረዱበት ጥበብ ነው፡፡

እግዚአብሔር ተብሎ ወደ ግዕዝ የተተረጉመው በዕብራይስጡ ቋንቋ ኤል ወይም በብዙ ቁጥር ኤሎሄም የሚለው ቃል ነው፡፡ ኤል ማለት  ኃይል ማለት ነው፡፡ በታላቁ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሌሎች የእግዚአብሐር ስሞችም ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህዌ ማለት የነበረ ያለና የሚኖር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል ወደ አማርኛው ሲተረጎም የሀገር  ወይም የዓለም ጌታ ማለት ነው፡፡ በምድራችን ላይ በርካታ ሃይማኖቶች፤ እምነቶችና አመለካከቶች የመኖራቸውን ያህል ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረና (ያስገኘ) እና የየዕለት ሁኔታዎችን  የሚመራ እና  የሚቆጣጠር አንድ ከሰዎች በላይ የሆነ የማይታይ ትልቅ ኃይል ያለ መሆኑን አብዛኛው ወገኖች ይስማማሉ፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሃይማኖት የራሱ የሆነ መመሪያና ትምህርት አለው፡፡

በዚህ መሰረት የክርስትና ነገረ መለኮት  ስንል ስለ እግዚአብሔር ህልውና ስለጠባዮቹ ስለመለኮታዊ አንድነቱ ሶስትነቱ ለፍጥረቱ ስለሚያደርገው ጥበቃ (መግበቱ) ከሶስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ ዓለምን ማዳኑንና በአጠቃላይም ለዚህ ሁሉ ትምህርት ምንጭ በሆነው አምላካዊ መጽሀፍ የተገለጸው ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚመረምር ትምህርት (ዕውቀት) ማለታችን ነው፡፡

መሆኑም በዚህች አጭር ፅሁፍ ውስጥ ይህንን ሀሳብ በስፋት ለማየት አባይን በጭልፋ ያህል ከባድ ስለሆነ በነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርዶቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን አስተምሮ በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

 

ሀልወተ እግዚአብሔር

ለእግዚአብሔር ህላዌ ማስረጃነት ከሚቀርቡት በርካታ ጉዳዮች መካከል በተለይ የፍጥረታት ሥነ ሥርዓትና አሠራሩ፣ የህሊና ምስክርነት ፣የሠው ልጆች የተፈጥሮ ዝንባሌ፣ የቃለ እግዚአብሄር፣ የታሪክ ምስክርነት ወዘተ….. ይገኙበታል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍ ወፎችንና እንስሳትን ብትጠይቋቸው ብዙ ሊያስተምሯችሁ በቻሉ ነበር፡፡ በምድር ላይ እና በባህር ውስጥ የሚኖሩትን ፍጥረቶች ጥበብ እንዲያስተምሯችሁ ብትጠይቋቸው ሁሉም እግዚአብሔር አንደሰራቸው ያስረዱአችኋል፡፡ የፍጥረቶቹን ሕይወት የሚመራ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ነፍስ በእግዚአብሔር ሥልጣን ስር ነው፡፡›› (መ.ኢዮ 12÷7-10) በማለት ዓለምን ያስገኘ እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስተምራል፡፡ መዝሙረኛው ቅ/ዳዊትም ይህንን ሀሳብ ሲያጠናክረው ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔር ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይ ጠፈሮችም የእግዚአብሔር ሥራ ያውጃሉ፡፡›› (መዝ19፡1) በማት ከእግዚአብሔር ውጭ ይህች ዓለም ሌላ አዛዥና ባለቤት እንደሌላት ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡

በአንድ ወቅት በአቴና ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ስለ እግዚአብሄር ሀልወት ለማመንና ለመቀበል ተቸግረው መስዋዕት እያቀረቡ መስዋዕት የሚያቀርቡለትን አምላክ ባለማወቃቸው ‹‹ ለማይታወቅ አምላክ›› ብለው ጽፈው ሲያመልኩ ግን የሚያመልኩትን አምላክ ሳያውቁ እንደነበረ ሀዋርያው ቅ/ጳውሎስ አርዮስፋጐስ በተባለው ሥፍራ ቆሞ የክርስትናን ሃይማኖት እንዴት እንደሰበካቸውና የማይታወቀውን አምላክ ሲገልጽ ‹‹ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሠማይና የምድር ጌታ ነውና….›› (የሐዋ 17፡24) በማለት ስለእግዚአብሔር ሀልወት ለአቴና ሰዎች ገልጧል፡፡

 

የእግዚአብሔር ጠባዮች

የእግዚአብሔር ጠባዮች በሁለት  አጠቃለን ለማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በማናቸውም መልኩ ለእግዚአብሄር እንጂ ለፍጡር የማይነገር የእርሱ የብቻው የባሕርይው መገልጫዎች ናቸው፡፡ እነርሱም በማንኛውም ሁኔታ ውሱንነት የሌለው መሆኑ፣ በራሱ የሚኖር መሆኑ፣ የማንም እርዳት የማያስፈልገው መሆኑ፣ ዘለዓለማዊነቱ አለመለወጡ፣ በሁሉም ቦታ የሚገኝ መሆኑ አለመታየቱ፣ አልፋና ኦሜጋ መሆኑ ወዘተ የመሰሉት ጠባዮች ይገኙበታል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው ይህም ሁሉን ዐዋቂነቱ፣ ጥበበኛነቱ፣ ሁሉን ቻይነቱ፣ ቅዱስነቱ፣ ትክክለኛ ዳኝነቱ፣ ፍቅሩና ደግነቱ፣ እውነተኛነቱና ታማኝነቱ…. ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ሰዎች በጸጋ በተለያየ መጠን ያግኙ  እንጂ የእግዚአብሔር ግን የባሕርይው ናቸው፡፡

 

ምስጢረ ሥላሴ

የክርስቲያን ሃይማኖት ከሌሎች ሃይማኖቶች ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ዋንኞቹ ርዕሶች መካከል ምሥጢረ ሥላሴ ወይም የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት እምነት አንዱ ነው፡፡ በክርስትና እምነት መሰረት እግዚአብሄር አንድ ነው አንዱ አምላክ ሦስት አካል አለው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር አንድ ሲሆን ሦስት አካል አለው ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል አንድ መለኮት ሦስት አካል፣ ወይም ሦስት አካል ያለው አንድ መለኮት ማለት ነው፡፡ የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት ምስጢር ግልጽ ሆኖ በመጽሀፍ ቅዱስ ተቀምጧል፡፡ ሊቀነቢያት ሙሴ በጻፈው በመጀመሪያ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል ‹‹እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ›› ( ዘፍ 1፡1) በማለት አንድነቱን ገልጾ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን በአምሳያችን እንፍጠር ( ዘፍ 1፡26) በማለት በአንድ ምዕራፍ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ (ዘፍ 3፡22 ፣ ዘፍ 11፡7፣ ኢሳ 6፡3፣ ዘኑ 6፡24)

ከመጀመሪያው ጀምሮ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ስለአንድነት እና ስለሦስትነት ትምህርት ግልጥ ሆኖ በስም ቀርቧል፡፡ ወንጌላዊው ቅ/ማቴዎስም እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፡፡ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኃቸው የኔ ደቀመዛሙርት አድርጓቸው›› (ማቴ 28፤19) በማለት አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ተጽፎ የሚገኘውን የሦስትነቱን ምስጢር በግልጽ በስም ጠቅሶ ይገኛል፡፡(ማቴ 3፡13-17 ፣ ማር1፡19-11፣ ሉቃ 3፡21-22፣ ማቴ17፡5፣ሉቃ 1፡35፣ዮሐ1፡33)

በተለያየ ዘመናት በነገረ መለኮት ላይ ለሚነሱ ክህደት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የትምህርቱ ስርወ እምነት እንዳይበረዝ በተለይ በኒቂያና በቁስጥንጥንያ ጉባዔያት የሐይማኖት ቀኖናዎች የአንድነቱን፣ የሦስትነትን እምነት አረጋግጠዋል፡፡ ይህም ፀሎተ ሃይማኖት በሚባለው የሃይማኖት ጸሎት ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡

‹‹ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡›› ይህን ስለ እግዚአብሄር አብ፤ ‹‹ከዘመናት ሁሉ በፊት ከአብ የተወለደ በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ በአንዱ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡›› ይህን ስለ እግዚአብሔር ወልድ ‹‹ሕይወትን በሚሠጥ ጌታ፣ ከአብ ከሰረፀ፣ ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን›› ይህንን ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቀኖናቸው ደንግገዋል፡፡

 

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ክብር

በንጉስ ቁስጢንጢኖስ ዘመነ መንግስት በ325 ዓ.ም በኒቅያ ከተማ በተሰበሰቡት 318 የዓለም ኤጲስ ቆጶሳት ውሳኔ መሰረት ከተወገዘው ከአርዮስ ጀምሮ የጌታችን የባሕርይ አምላክነትና ከአብ ጋር ያለው እኩልነት የሚክዱ የአርዮስ ወገኖች ነበሩ አሁንም አሉ፡፡ ለዚህም ምላሽ ወንጌላዊው ቅ/ዮሐንስ ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችስ ስንኳ ያለእርሱ የሆነ የለም›› (ዮሐ1፡3) በማለት ስለክርስቶስ ክብር ተናግሯል፡፡ ይህም ማለት (ዘፍ1፡1) ሰማይንና ምድርን እንዲሁም በእነርሱ የሚገኙትን ፍጥረቶች ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር እርሱ ነበር ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ እውራንን ያበራ፣ አንካሳን ቀጥ ያደረገ፣ ዱኩማንን ከድካማቸው ያሳረፋቸው፣ ሙታንን ያስነሳ፣ ህሙማንን የፈወሰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ መሆኑን ነቢያት እንደተናገሩት፣ ሃዋሪያት እንደሰበኩት መምህራን እንዳስተማሩት ይልቁንም ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እንዳረጋገጠልን ይህንን የሐይማኖት መሰረት አድርገን እናምናለን፡፡ ‹‹የሥጋን ህማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ እግዚአብሔር በባህርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም ሕማም በሚስማማው ባህርዩ ኃይልን እንጂ ሞትም ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በሆነ ጊዜ ሞትን አጠፋ ከሞተም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ›› (ሃይ አበ.ገጽ 175) ቅዱስ ቴዎድጦስ የዕንቁራ ኤጲስ ቆጶስ፡፡

 

የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ክብር

መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል መሆኑን ቤተክርስቲያን ታምናለች (ታስተምራለች) ይህም ማለት በባህርይ በጠባይና የመለኮት ግብር በሆኑ ነገሮች ሁሉ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል ማለት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንዱ ከሌላው የሚበልጥ ወይም የሚያንስ ሳይሆን ሦስቱም አካላት በከሃሊነት፣ በክብር በሥልጣን፣ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እኩል ናቸው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ክብር ከአብና ከወልድ ጋር በባህርይ እኩል መሆኑን ቅዱሳት መጻህፍት በበቂ ማስረጃዎች አረጋግጠዋለሁ፡፡ በቅዱሳት መጻህፍትም በግልጥ የቀረበ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አካልነት ማለት ከሶስቱ አካላት አንዱ መሆኑን ታምናለች፡፡ ይሁን እንጂ የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ክብር የሚክዱ መናፍቃን በተለያዩ ዘመናት ተነስተዋል፡፡ እንደ አርዮስ፣ ሰባልዮስ እና መቅዶንዮስ ያሉ ናቸው፡፡

ለእነዚህም መናፍቃን ሊቃውንት ‹‹ወንአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማህየዊ ዘሠረፀ እመ አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሆ ምስለ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ……›› በማለት በሃይማኖት ፀሎት ደንግገዋል፡፡ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል፡፡ (1ቆሮ 12፡11) በማለት የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊ ክብር ገልጧል፡፡ ከላይ ለማየት እንደተሞከረው በነገረ መለኮት ትምህርት ውስጥ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያለመጠራጠር ለልጆቿ የሥላሴን አንድነትና ሶስትነት ያለመቀላቀል ያለመለያየት ስታስተምር ኖራለች ወደፊትም ታስተምራለች፡፡

የሥላሴ ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን  አሜን!!!

ክርስቲያናዊ ህይወት

ክርስትና የሚለው ቃል “XPIETIAVOS” ኽርስቲያኖስ ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም የክርስቶስ መሆን ማለት ነው፡፡ ክርስትና ሰዎች በፍቅረ እግዚአብሔር ተስበው፤ ፈጣሪያቸውን አውቀው፤ እረፍትን ሽተው፤ በህጉና በትእዛዙ ፀንተው፤ ለመኖር ሲሉ ከዓለም ፈቃድ ተለይተው የሚኖሩበት ህይወት ነው፡፡ ይህንንም ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር ዮሐንስ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የስጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ÷ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም፡፡

ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚያብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዐለም ይኖራል” (1ዮሐ 2፡16) በማለት ክርስቲያን ለመሆን በመጀመሪያ ዓለምን መካድ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ በክርስትና ወድቆ (ተረግሞ) የነበረው የሰው ዘር እንደ ተነሳ (እንደ ተፈታ)፤ የታመመው እንደ ተፈወሰ፤ የረከሰው እንደ ተቀደሰ፤ የሞተው እንደተነሳ፤የተሰበረው እንደተጠገነ፤ የሳተው እንደ ተመለሰ ይታመናል፡፡

የክርስትና መስራቹ ራሱ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ “በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሰራለሁ፡፡ የገሀነም ደጆችም አይችሏት” (ማቴ 16፡18) በማለት ቤተክርስቲያን ሳይሆን ቤተክርስቲያኔን የራሱ እንደሆነች በህያው ቃሉ አረጋግጦልናል፡፡

ክርስቲያኖች ክርስቲያን ከመባላቸው አስቀድሞ ምዕመናን (መዝ 100፡7) ፤ ደቀመዛሙርት (ኢሳ 8፡16) ፤ ወንድሞች (ማቴ 8፡10) የመሳሰሉት በመባል ይጠሩ ነበር፤ ነገር ግን ደቀመዛሙርቱ ክርስቲያን ተብለው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰየሙት በአንጾኪያ በማርቆስ እናት በማርያም ቤት እንደነበር ቅዱስ መጽሀፍ ይነግረናል፡፡ (የሐዋ 11፡26)

በምድራችን በሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ይገኛሉ፡፡ የሃይማኖታቸውን መስራች ስናጠና ግን ሰዎች ሆነው እናገኛለን፡፡ ትምህርታቸው ዛሬም በተከታዮቻቸው ይኑር እንጂ እነርሱ ግን በህይወት የሉም፤ የክርስትና ዋና መስራች ግን ትናንት የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዐልፋና ዖሜጋ ዘዓአለማዊ በመሆኑ ዛሬም ስራውን አላቆመም ማለት ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ህይወት ለመኖር ክርስቲያኖች የሚከተለውን መተግበር እንዳለብን የህይወት ምንጭ የሆነው መጽሀፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡

1.    እግዚያብሔርን ማወቅ

መቼም ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት ዘመን ስለ እግዚያብሔር ያልሰማ አለ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ይሁን እንጂ ከዕውቀት ብዛት እግዚአብሄርን የካዱ (እግዚአብሔር የለም) ያሉ በርካታ ሰዎች በምድራችን መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህም ስንፍና እንጂ እውቀት እንዳልሆነ ልበ አምላከ ቅዱስ ዳዊት ይነግረናል፡፡ “ይበል አብድ በልቡ አልቦ እግዚአብሔር” ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል (መዝ 13፡1)፡፡ ፍልስፍና ማለት ጥበብን ማፍቀር ማለት እንጂ እግዚአብሄርን አለማወቅ ወይም መካድ ማለት አይደለም፡፡ አንድ ልጅ አባቱን አላውቅህም አባቴ አይደለህም ስላለው አባቱ አልወለደውም ማለት አይደለም እንዳውም ልጁ ሲጠራ አባቱን የካደ ልጅ ተብሎ ይጠራል፡፡

እግዚአብሄርን ማወቅ፡-

ትርጉም ያለው ሕይወት ይሰጣል

በምድራችን ትርጉም ያለው ሕይወት ማለት ምን አልባት የሚመስለን ሀብት፤ ንብረት፤ ስልጣን ፤ ጥሩ መልበስ፤ ጥሩ መመገብ ፤ ጥሩ ቤት መኖር ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ትርጉም ያው ህይወት መኖር የሚቻለው እግዚአብሄርን ሲያውቅ ነው፡፡ በዚህ ዘኪዎስ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ዘኪዎስ ጌታውን ሳያውቅ የኖረበት ዘመን ትርጉም አልባ ህይወት ነበር አምላኩን ሲያውቅ ግን “ጌታ ሆይ ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ ማንንም በሃሰት ከስሼ እንደሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው” (ሉቃ 19 ፤9) በማለት አዲሱ ክርስቲያናዊ ህይወት ምን እንደሚመስል ነግሮናል፡፡

ታሪክን ይቀይራል

ሰዎች እግዚአብሄሔርን ሲያውቁ ዘማዊ የነበረው ድንግል፤ ዘረኛና ወገንተኛ የነበረው ሁሉን በክርስቶስ አንድ አድርጎ የሚያይ ፍትሃዊ፤ አሳዳጅ የነበረው ስለ ክርስቶስ ተሳደጅ፤ ክፉ የነበረው ደግ፤ ዘፋኝ የነበረው ዘማሪ፤ ነፍሰ ገዳይ የነበረው የሰውን ህይወት የሚያድን ወዘተ ይሆናል፡፡ለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ጥሩ አስረጅ ይሆናል፡፡

2.    በዕምነት ማደግ

ብዙዎች ክርስቲያን ተብለው ይጠራሉ ጥቂቶች ብቻ በእምነት ውስጥ በጥበብ ይኖራሉ፡፡ “ዕምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነውና” (ዕብ11፡1) የሰው ልጅ በሃይማኖት ካልኖረ ለምኞቱ ገደብ የለውም፡፡ ያለኝ ይበቃኛል አይልም፡፡ አመንዝራ ሲያይ በፍትወት ስሜት ይቃጠላል፣ የወይን ጠጅ በብርሌ ባማረ መልኩ ባየ ጊዜ መጠጥ ያምረዋል ለዚህ እኮ ጥበበኛው ጠቢቡ ሰለሞን “ከተማን ከመግዛት ራስን መግዛት ይበልጣል ያለው”

3.    በእግዚአብሔር ፍቃድ መኖር

እግዚአብሔር ከእኔ ይልቅ ስለ እኔ ያስባል ብሎ ማመን ነው፡፡የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘለዓለም ይኖራል፡፡(የሐ2፡17) የጌታችንም ፈቃድ ሁሉ የእግዚአብሔር እንደሆነ ሲያስተምር “አባት ሆይ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ ነገር ግን የእኔ ፍቃድ አይሁን የአንተ እንጂ”(ሉቃ22፡42) ምክንያቱም ሀዋርያው እንደተናገረው ”ስለ በጎ ፈቃድ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሰራ እግዚአብሔር ነውና” እንዲል (ፊሊ1፡13)

4.     እግዚአብሔርን መምሰል

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ዓለም ሶስት ዓመት ከሶስት ወራት በአገልግሎት ሲቆይ በርካታ ትምህርቶችን ከማስተማሩም በላይ በሕይወቱ አብነት ለመሆን መልካም ሥራ ካደረገ በኋላ ከመዝ ግበሩ  እናንተም እንዲሁ አድርጉ(ዮሐ13፡14)(ምንም እንኳን መልካምነት የባህርይው ቢሆንም) በማለት ክርስቲያኖች በሕይወት ዘመናቸው ክርስቶስን መምሰል እንዳለባቸው መጽሀፍ ይስተምረናል፡፡ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ቃል ”እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ”(1ኛቆሮ 11፡1) በማለት ያረጋግጥልናል፡፡በመሆኑም የመንፈስን ፍሬ በማድረግ የስጋን ሥራ በመተው አምላካችንን መምሰል ይገባናል ማለት ነው፡፡(ገላ 5፡18)ይህንን በማድረግ ቅዱሳን ቅድስናን ገንዘብ አድርገዋል፡፡“እግዚአብሔር መምሰል ግን ለአሁኑ እና ለሚመጣው ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል”(2ጢሞ 4፡8)

5.    ፍቅር ሊኖረን ይገባል

በክርስትና መጀመሩያውም መጨረሻውም ፍቅር ነው፡፡ ምክንያቱም “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፡፡እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” (1ዮሐ 4፡8) በመሆኑም ያለ ፍቅር ክርስትና የለም፡፡ቢኖር እንኳን ቅ/ጳውሎስ እንደተናገረው ከንቱ ነው “ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ”(1ቆሮ 13፡1)

6.    ከመስቀሉ መካፈል

የጠፋውን በግ ፍልጋ ራሱን ባዶ ያደረገው ክርስቶስ (ፊሊ 2፡8) ድሉ በመስቀል ስለ ተጠናቀቀ ክርስቲያኖች በሕይወት ዘመናቸው ከመስቀሉ ተካፋይ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህም ከመስቀሉ ስር የተሰጠችንን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን መውሰድ፤ የተቆረሰውን ቅዱስ ስጋ መብላት፤ የፈሰሰውን ክቡር ደም መጠጣት ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ (ዮሐ 19፡27፤ ዮሐ 6፤56) ይህ ሁሉ ሲሆን ለዘለዓለም በሕይወት እንኖራለን ማለት ነው፡፡

ስብሃት ለእግዚያብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለ መስቀሉ ክቡር
አሜን

የቅዱሳን ሕይወት(ክብረ ቅዱሳን)

በሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረአማኑኤል

ቅድስና በምንልበት ጊዜ ቅድስናን በሁለት ከፍሎ ማየት ተገቢ ይሆናል፤ ይኸውም፡-

 • ሀ. የባሕርይ ቅድስና ፤
 • ለ. የጸጋ ቅድስና ማለት ሲሆን የባሕርይ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻ የምንገልጸው ልዩ አገላለጽ ነው፡፡ የጸጋ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ደግሞ ሰማያውያን መላዕክትና ምድራውያን ሰዎች ራሳቸውን ለቅድስና አዘጋጅተው ሲገኙ ቅድስናውን የሚያገኙት የቅድስና ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚገኝ ልዩ ስጦታ ነው፡፡ በተለይ ምድራውያን ሰዎች በሃይማኖት ጸንተው፤ በበጎ ሥራ ተቃኝተው በቅን ልቡና አግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ቅዱሳን ይሆናሉ፤ ቅዱሳንም ይባላሉ፡፡ ‹‹እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› ተብሏልና፡፡ (ዘሌ 19፡2)

የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን በምንልበትም ጊዜ ብሔራዉያን ቅዱሳንንና ከዉጪ ወደ ኢትዮጽያ መጥተዉ ያበረከቱትን ከፍተኛ መንፈሳዊ አገልግሎት ከግምት ዉስጥ በማስገባት የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ቅድስናን ሰጥታ፣ በየስማቸዉ ቤተ ክርስቲያን አንፃ፣ ፅላት ቀርጻ፣ ገዳም ገድማ ያከበረቻቸዉና የምታስከብራቸዉ ቅዱሳን በርካታዎች ሲሆኑ በዚህ ፅሁፍ አጠቃሎ መግለጽ ባይቻልም ለግንዛቤ ያህል የአገር ዉስጥና የዉጭ ሀገር ቅዱሳን በማለት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ከፍሎ መግለፅ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለፀዉ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸዉን ፈፅመዉ ዘለዓለማዊ ዕረፍታቸዉን በኢትዮጽያ ምድር በማድረጋቸዉ ብሔረ ሙላዳታቸዉን ለመግለፅ ያህል ታስቦ የተገለፀ ጽሑፍ መሆኑ ከግንዛቤ ዉስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡

የኢትዮጽያን የሁለት ሺህ ዘመን ቅዱሳን ታሪክ በዚህ ጽሑፍ አምልቶና አስፍቶ መግለፅ ባይቻልም ዝርዝር ታሪኩን ለታሪክ ጸሐፊዎች በመተዉ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አለኝታ የሆኑትን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዐበይት መምህራንን፣ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያናችን ስም በየአረፍተ ዘመናቱ መላ ሕይወታቸዉን የሰዉ ዘር የሆነዉን ሁሉ በሥራና በጸሎት በማገልገል፣ እግዚአብሔርን በማመስገን ሕይወታቸዉን መሥዋዕት አድርገዉ ያቀረቡትንና እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነዉን ገድል የፈጸሙትን ሁሉ ቤተክርስቲያናችን የጾታ ልዩነትን ሳታደርግ በገድላቸዉ ጽናትና በትሩፋታቸዉ ብዛት ብፁዕና ብፅዕት፣ ቅዱስና ቅድስት ሊያሰኝ ከሚችል የብፅዕናና ቅድስና ማዕረግ የደረሱ መሆናቸዉን በማረጋገጥና በስማቸዉም ቤተክርስቲያን እንዲታነጽ፣ ገዳም እንዲገደም፣ ደብር እንዲደበር፣ ገድልና ድርሳን እንዲጻፍላቸዉ፣ ወርሃዊና ዐመታዊ በዓላቸዉ እንዲታሰብና እንዲዘከር በማድረግ በቅዱስነት ያወቀቻቸዉንና ያሳወቀቻቸዉን ኢትዮጰያዉያንና ብሔረሙላዳታቸዉ ከኢትዮጰያ ዉጪ የሆኑትን ቅዱሳንና ቅዱሳትን ስም ዝረዝር በከፊልም ቢሆን እንደሚከተለዉ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡

 

ኢትዮጰያዉያን ቅዱሳንና ቅዱሳት

1. ሕጽዋ ለሕንደኬ ንግስተ ኢትዮጰያ

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጰያ የገባዉ ወይም ኢትዮጰያና የክርስትና ሐይማኖት የተዋወቁት ሐዋርያዉ ቅዱስ ሉቃስ በግብረ ሐዋርያት 8፡26-40 ላይ እንደመዘገበው ጃንደረባው እንደ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዞ ሥርዓተ አምልኮትን ፈጽሞ በፍኖተ ጋዛ ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ ነው፡፡ ዘመኑም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ34 ዓ.ም. ነው፡፡

‹‹የቤተ ክርስቲያን አባት›› እየተባለ የሚጠራው አውሳብዮስ የወንጌላዊው ሉቃስን ግብረ ሐዋርያት መሠረት አድረጎ ‹‹ሕጽው ለወገኖቹ ሆነ የኢትዮጵያ ሐዋርያ እሱ ነው›› በማለት ጽፎአል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ገጽ 18 ላይ ይመለከቱ፡፡

2. ቅዱሳን ነገስታት አብርሃ ወአጽብሓ

አብርሃ ወአጽብሓ የተሰኙ ቅዱሳን ነገስታት(ወንድማማቾች) እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ፍጹም በሆነ ስምምነት ለ15 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን በጋራ ከአስተዳደሩ በኋላ እንደ አበው ሐዋርያት ዕጣ ተጣጥለው አብርሃ በአክሱም፤ አጽብሓ በሸዋ መናገሻ ከተማውን ኤረር በማድረግ መንበረ መንግሥታቸውን ዘርግተው እየተመካከሩ ኢትዮጵያን በማስተዳደራቸው፤ ለሀገሪቱና ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሁለቱ ወንድማማች ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታቸዋለች፡፡ በስማቸውም ቤተ ክርስቲያን አንጻለች፡፡ ወርኀዊና ዓመታዊ በዓላቸውንም በየዓመቱ ጥቅምት 4 ቀን እንዲታሰብና እንዲከበርም አድርጋለች፡፡ (ታሪከ ነገሥት አብርሓ ወአጽብሓ ከመምህር ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ 1989 ዓ.ም አዲስ አበባ)

3. አፄ ካሌብ

ከአብርሃና አጽብሓ ቀጥሎ ከተነሡት ቅዱሳን ነገሥታት ክርስትናን በማስፋፋትና በመንከባከብ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያደረጉት ከ485-515 ዓ.ም. የነበሩት አፄ ካሌብ ናቸው፡፡
አፄ ካሌብ ስለ ክርስትና መስፋፋት፤ ስለ ክርስቲያኖች አንድነት ብዙ ተጋድሎን ከተጋደሉና ከአሳለፉ በኋላ መንግሥታአውን ለልጃቸው ለአፄ ገብረ መስቀል አስረክበው፤ መንነው፤ ልብሰ ምንኩስናን ለብሰው ከአክሱም ወደ ሰሜን ምሠራቅ በሚገኘው በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም በሚገኘው ዋሻ የምናኔ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ መንግሥታቸውን ለቀው በመነኑበት ሰዓት እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነውን ማለትም የነገሡበትን ዘውድ ወደ ጌታ መቃብር ጎልጎታ ልከው በምናኔ 12 ዓመታት ከተጋደሉ በኋላ በ536 ዓ.ም. ግንቦት 20 ቀን አርፈዋል፡፡ አፄ ካሌብ በምንኩስናና በምናኔ ሕይወት የቅዱሳንን አሠረ ጽድቅ ፈጽመው ያለፉ ደገኛ ንጉሥ ስለነበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቁጥራቸው ከቅዱሳን ነው፡፡ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ 1974 ዓ.ም.)

4. አባ ዮሐኒ

አባ ዮሐኒ ብሔረ ሙላዳችው በክልል ትግራይ፤ በተንቤን ልዩ ስሙ ሀገረ ሰላም ከተባለው ቀበሌ ሲሆን የነበሩበትም ዘመን በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በቆላ ተንቤን ደብረ አንሣ(ዓሣ) ከተባለው በረሓ በጾምና በጸሎት ተወስነው ይኖሩ ከነበሩት ከአባ አሞኒ ጋር እንደ ኖሩ፤ ዕድገታቸውም በእናት ጡት ሳይሆን ቶራ እያጠባች እንዳሳደገቻቸው በገድለ አቡነ ዮሐኒ ተመዝግቧል፡፡ ገዳማቸውም ደብረ አንሣ(ዓሣ) ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ወርኀዊና ዓመታዊ በዓላቸውም ህዳር 5 ቀን ይታሰባል፡፡ ( ምንጭ፡- 1. የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ከዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ 2. Journal of Ethiopian Studies. Vol 3 No. 2 July 1975)

5. ቅድስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ505 ዓ.ም. የተነሣ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዓለም በሚታወቅበት ሙያውና ዕውቀቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ የመንፈሳዊ ዜማ ደራሲ የቅኔ ተመራማሪ፤ ኪሩቤልን በሚያስምስለው ጣዕመ ዝማሬ የተወደደና ድምፅ መልካ ማሕሌትዊ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ድጓ፤ ዝማሬ መዋሥእትና ምዕራፍ የተሰኙ የዜማ መጻሕፍት አሉት፤ የብሉያት የሐዲሳትና የሊቃውንት መጻሕፍት ትርጓሜም ሊቅ ነው፡፡ እነዚህ ከብሉያት ከሐዲሳት ከሊቃውንት መጻሐፍት ለጸሎትና ለማሕሌት የሚስማሙትን ቃላት እየመረጠ ምሥጢራትን ከትርጓሜ እያስማማ ዜማዎቹን በዐራቱ ክፍላተ ዘመን በመፀው፤ በሐጋይ፤ በጸደይና በክረምት በመክፈል የየወቅቱን የተፈጥሮ ሥነ ባሕርይ በአንክሮና በምስጋና በሚገልጽ ጣዕም እንዲዘምሩና እንዲጸልዩ ያደረገ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነው፡፡ ዜማውንም ግዕዝ፤ ዕዝል አራራይ በሚል በሦስት የዜማ ስልት ከፍሎ ዘምሮታል፡፡
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቱን ያዘጋጀው ከ540-560 ዓ.ም. ባለው ዘመን ነው፡፡ ማሕሌታዊው ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍሎች ለ11 ዓመታት እየተዛዋወረ ሲያስተምር ቤተ ክርስቲያንን ያገለግልና ሲያስገለግል ቆይቷል፡፡
በመጨረሻም በሰሜን ተራራዎች ሥር ካሉት ገዳማት በአንዱ ዋሻ ውስጥ ገብቶ በጾም፤ በጸሎት፤ በብሕትውና ዘመኑን አሳልፎአል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ እስከ ዛሬ እልፈትና ውላጤ ያላገኘው በጣዕመ ዝማሬው በምልክቱ ልዩ የሆነ የዜማ ድርሰቱን ለኢትዮጰያ ቤተ ከርስቲያን ያበረከተ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝክረ ስሙን በጥንቃቄ ጠብቃ፤ በስሙ ጽላት ቀርፃ፤ ቤተ ክርስቲያንን አንጻ፤ ገድሉን ጽፋ በዓለ ዕረፍቱን በየዓመቱ ግንቦት 11 ቀን ታከብራለች፡፡ (ምንጭ፡- The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Faith, order of worship and Ecumenical relations, July 1996)

6. ሌሎች

 • ቅዱስ ይምርሃነ ክርሰቶስ
 • ቅዱስ ሐርቤ(ገ/ማርያም)
 • ቅዱስ ላሊበላ
 • ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ

እነዚህ ቅዱሳን የነበሩበት ዘመን ከ11ኛው እስከ 12ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን ምስፍንናን ከክህነት፤ ክህነትን ከምንፍስና ጋር አስተባብረው በመያዝ ለክርስትና መስፋፋት፤ ለቤተ ከርስቲያን ዕድገት፤ ለአገር አንድነት የከፈሉት መስዋዕትነት፤ ያቆዩት መንፈሳዊ ቅርስ በዐይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ኢኮኖሚ የደም ሥርና የጀርባ አጥንት ሆነው የሚታዩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ ስማቸው ለተጠቀሱው መንፈሳውያን ነገሥታት የቅድስና ማዕረግ ሰጥታ፤ ገድላቸውን ጽፋ ለትውልደ ትውልድ አቆይታለች፡፡

(ምንጭ፡- 1. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትና ዛሬ መስከረም 1990 ዓ.ም 2. ዜና መዋዕል ዘብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነሐሴ 1978 ዓ.ም. 3. የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ከዶ/ር ሥርግው ሐብል ሥላሴ 1981 ዓ.ም.)

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ነው?

፩. ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን  ምንድን ነው?

ሥርዓት “ሠርዐ” ሠራ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ደንብ፣ አሠራር፣ መርሐ ግብር ማለት ነው። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንልም የቤተ ክርስቲያን ዕቅድ፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር መርሐ ግብር ወይንም ደንብ ማለታችን ነው።

ሥርዓት የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፦

ሥራን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፈጸም

ማንኛውንም ነገር ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ከየት ተጀምሮ በየት በኩል ሄዶ በየት በኩል እንደሚጠናቀቅ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ይዘጋጅለታል። የአንድ ሥራ አሠራር በትክክል ካልተነደፈና አካሄዱ ካልተስተካከለ፤ ሥራው የተዘበራረቀ ይሆናል ፍጻሜውም አያምርም።
ማኅበረ ምዕመናንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ አንድ ዓይነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገናል። ብዙ ስንሆን አንድ ልቡና አንድ ሃሳብ የሚያደርገን ሥርዓት ነውና። /ኤፌ. ፬፥፫፤ የሐዋ. ፬፥፴፪፤ ሮሜ. ፲፭፥፮

የሃይማኖትን ምሥጢራት ለመጠበቅ

ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ ነው። ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደት፣ ወዘተ በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆን የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ /ሥርዓት/ ያስፈልጋቸዋል። የእነዚህ ሁሉ ዝርዝር አፈጻጸም በሥርዓት ውስጥ ይካተታል። ስለዚህ በአንዲት ርትዕትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥር ያሉ ሁሉ ያቺን አንዲት እምነት የሚገልጹት አንድ ዓይነት በሆነ ሥርዓት ነው። ሥርዓት በመሠረተ እምነት /ዶግማ/ የምናምናቸውን በተግባር የምንገልጽበትና ተግባራዊ የምናደርግበት መንገድ ስለሆነ ሥርዓቱ ሲሠራና ሲፈጸም ሃይማኖታዊ አንድምታና ነጸብራቅ ይኖረዋል።

 

፪. ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን ማለት ሕንፃው፣ የክርስቲያኖች አንድነት /ጉባኤ/ እና የምዕመኑ ሰውነት በመሆኑ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የምንለውም በእነዚህ በሦስቱ ላይ የተሠራውን ሥርዓት ነው። አንዳንዶቻችን ቤተ ክርስቲያንን ከራሳችን አርቀን ሌላ አካል አድርገን ስለምንመለከት ሥርዓቱ እኛን የሚመለከት አይመስለንም። ሥርዓቱ ግን የተሠራው ለሦስቱም የቤተ ክርስቲያን ትርጓሜዎች መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጩ ወይንም መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት ውሳኔ /ሲኖዶስ/ እና አባቶቻችን ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜ ያደረጓቸው ጉባኤያት ውሳኔዎች ናቸው።

ሰንበትን ማክበር፣ በጻድቃን ስም አብያተ ክርስቲያናትን ማነጽ፣ የቁርባን ሥርዓት፣ የመሳሰሉት ከመጽሕፍ ቅዱስ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው። /ዘፍ. ፳፰፥፳-፳፪፤ ዘጸ. ፲፮፥፳፱፤ የሐዋ. ፩፥፲፪/።
ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባውንና የተቀደሰውን ንዋየ ቅድሳት እንደገና ወደውጭ አውጥቶ ለሥጋዊ ጥቅም ማዋል እንደማይገባ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩ ረስጣ ፳፰/፣ ጥምቀት በፈሳሽ ውኃ መፈጸም እንዳለበት፣ ወንዶች ሴቶችን ሴቶች ደግሞ ወንዶችን ክርስትና እንዳያነሱ፣ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ፲፰ ሰዓት መጾም እንደሚገባ፣ ሥጋ ወደሙ በምድር ላይ እንዳይወድቅ /እንዳይነጥብ/፣ ያላመኑ ሰዎች ሥጋ ወደሙን መቀበል እንደሌለባቸው፣ ወዘተ ያሉት ደግሞ በሲኖዶስ /የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት/ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።
ከእናቱ፣ ከእህቱ፣ ከአክስቱ ወይንም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ከምትታሰብ ሴት ጋር ካልሆነ በቀር አንድ ኤጲስ ቆጶስ፣ አንድ ቄስ፣ አንድ ዲያቆን፣ ወይንም ሌላ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከማንኛውም ሴት ጋር አብሮ እንዳይኖር፤ ስለ መናፍቃን ጥምቀት፣ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር፣ ስለ ድንግልና ኑሮ፣ ወዘተ ደግሞ በተለያዩ ጉባኤያት አባቶቻችን ያስተላለፏቸው ውሳኔዎችና ቀኖናዎች የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

የቤተ ክርስቲያን አመሰራረትና የቅዳሴ አገልግሎት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር

መቼም በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እየሰፋች ከሀገር ቤት አልፋ በውጭ ሀገርም አብያተ ክርስቲያናት እየታነጹ ስለሆነና ሁላችንም የቻልን ዘወትር ቅዳሴ በሚቀደስባቸው ዕለታት፣ ያልቻልን ደግሞ በዕለተ ሰንበት ለቅዳሴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለምንሄድ ስለ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት፣ አሠራርና ቡራኬ፣ እንዲሁም ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዴት መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን። ለዚህም እንዲረዳን እንደሚከተለው እናያለን።

ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ቃሉ ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል /ቤቴሰ ቤተጸሎት ትሰመይ/ የሚለው /ኢሳ. ፶፮፥፮-፯፤ ኤር. ፯፥፲፩፤ ማቴ. ፳፩፥፲፫፤ ማር.  ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፮፤ ዮሐ. ፪፥፲፮-፲፯/ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የዋዛ የፈዛዛ፣ የሳቅ የስላቅ፣ የጨዋታ፣ የመብል፣ የመጠጥ ቤት ሳትሆን፤ ምዕመናን ኃጢአት ቢሠሩ ሰለ ኃጢአታቸው የሚያዝኑባት የሚያለቅሱባት ንጹሕ የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ካህናት የሚያስተምሩባት፣ ምዕመናን የሚማሩባት የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት የሚጸልዩባት፣ በኅብረት የሚያስቀድሱባት ሥጋ  ወደሙ የሚቀበሉባት፣ የኃጢአት ሥርየት የሚያገኙባት፣ ሕፃናት በአርባ ቀንና በሰማንያ ቀን በጥምቀተ ክርስትና አማካኝነት ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት የሚቀበሉባት፣ ኢአማንያን የነበሩ በመምህራን ትምህርት አምነው ክርስቲያን የሚሆኑባት፣ ለክህነትም ሆነ ለአባልነት የዘር ሐረግ የማይቆጠርባት ዓለም አቀፋዊት የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡
 
አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስትመሠረት ጀምሮ ሥርዓት አላት። የምትመሠረተው ባንድ ግለሰብ ስም ሳይሆን በካህናትና በምዕመናን ጥያቄ በሀገረ ስብከቱ ኤጲስ ቆጶስ ፈቃድና ትእዛዝ ነው፤ ካለኤጲስ ቆጶስ ፈቃድ ከመጽሐፉ ትዕዛዝ ወጥቶ አንዱ ቢያቋቁም ወይም ቢሠራ ቤተ ክርስቲያን ናት ብለው ለዘለዓለሙ በዛች ቤተ ክርስቲያን አይቁረቡባት፤ እንደገበያ፣ እንደእንስሳት በረት ፈት ሆና ትኑር ይላል። /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩-፫/።
 
ቤተክርስቲያን ለመሥራት ፈቃድ ከተገኘ በኋላ ስለ አሠራሯ የሚከተለው ሥርዓት ተሠርቶላታል። ቤተ ክርስቲያኗ ስትሠራ ደጆችና መስኮቶች አውጡላት ዛፍ ቅረጹላት ሐረግ ሳቡላት እንደሚል በተቻለ መጠን ሊያስጌጧት ይገባል የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናትና።  በሰማይ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት እንዲያበሩ፣ ሰባቱ ሰማያት ብሩሃን እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያንም ብርህት ትሁን፤ ይልቁንም ክቡራት መጻሕፍት ሐዲሳት፣ የጳውሎስ መልእክታት፣ የሐዋርያት መልእክታት፣ ግብረ ሐዋርያት በሚነበቡበት ጊዜ የበራች ትሁን፣ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ያለውም ይህንኑ ያመለክታል። /ማቴ. ፭፥፲፬/። ቅዱስ ወንጌል በሚነበብበት ጊዜ ግን ፈጽማ የበራች ትሁን፤ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ያለው ይሻል። /ዮሐ. ፱፥፭/።

ቤተ ክርስቲያን ሲባረክ

ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጽሞ በምትባረክበትና በምትቀደስበት ጊዜ ከኤጲስ ቆጶሱ ጋር ሰባት ቀሳውስት አብረውት ሊኖሩ ይገባል፣ ታቦቱም በሚባረክበት እንደዚሁ ሊሆን ይገባል፣ ኤጲስ ቆጶሱ እግዚአብሔር ሰውን የሚያከብርበት ራሱን የሚያስመስልበት ነውና ደስ በሚያሰኝ በቅብዐ ቅዱስ በሜሮን ያክብራት ያትማት፣ ታቦቱንም በመቅደስ ውስጥ በመንበር ያስቀምጡባት ከታቦቱ ጋራ የዮሐንስን ወንጌል ያኑሩ ከደቀ መዛሙርቱም በጌታ ኢየሱስ አጠገብ የሚቀመጥ ጌታ የሚወደው ቅዱስ ዮሐንስን ነበርና። /ዮሐ. ፲፫፥፳፫/ ።
 
ታቦቱም ሲቀረጽ ከላይ አልፋ፣ ቤጣ፣ የውጣ፣ ወኦ/ወዖ/ ይቀረጻል። ቀጥሎ እመቤታችንን፣ ከእመቤታችን ቀጥሎ ዮሐንስን፣ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያኑ የሚተከለው ታቦት መልአክም ቢሆን፣ ሰማዕትም ቢሆን፣ ጻድቅም ቢሆን ይቀረጻል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ካልተሟሉ ታቦቱን ሊቀድሱበት አይገባም።
 
ከቤተ ክርስቲያን የገባ ዕቃ የወርቅ፣ የብር፣ ፃሕል ጽዋእ እርፈ መስቀል ቢሆን ንዋየ ቅድሳት ነው ተብሎ አቡነ ዘበሰማያት ከተደገመበት በኋላ ከቤታቸው ወስደው በፃሕሉ ፈትፍተው ሊበሉበት በጽዋው ቀድተው ሊጠጡበት አይገባም። ደፍረው ቢያደርጉ ሥርዓት ማፍረስ ነውና ይህን ያደረገ ቢኖር በአንድ ሁለት ተቀጥቶ ንሰሐውን እሰኪፈጽም ከምዕመናን ይለይ። /ዳን. ፭፥፩-፴፩/።
 
በቤተ ክርስቲያንም ኤጲስ ቆጶሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ምዕመናን እንዴት መቆም እንዳለባቸው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ይገልጻል። ኤጲስ ቆጶሳት የቤተ ክርስቲያን አዛዚያን እንደመሆናቸው በታቦቱ ፊት ይቁሙ፣ ቀሳውስትም መምህራን እንደመሆናቸው ከኤጲስ ቆጶሳት ቀጥለው ይቁሙ፣ ሊቀ ዲያቆናትም ከኤጲስ ቆጶስ አጠገብ ይቁሙ፣ ዲያቆናትም አገልጋዮች እንደመሆናቸው ከቀሳውስት ቀጥለው ይቁሙ፣ ከዲያቆናት ቀጥለው ሕዝቡ ሁሉ ባንድ ቦታ ይቁሙ፣ የሚበቃ ቦታ ቢኖር ሕፃናት በአንድ ወገን ለብቻቸው ይቁሙ፣ የሚበቃ ቦታ ከሌለ ግን ከአባቶቻቸው ጋራ ተስገው ይቁሙ፣ እንደዚሁም ሴቶች ባንድ ወገን /ቦታ/ ለብቻቸው ይቁሙ፣ ቦታ ቢገኝ ሕፃናት ሴቶች ባንድ ወገን ለብቻቸው ይቁሙ፣ ቦታ ባይኖር ግን ሕፃናቱ በፊት እናቶች በኋላ ይቁሙ፣ ደናግላን ሴቶችና ባልቴቶች ግን ከሴቶች በላይ ይቀመጡ ። /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፪ ድስቅ ፲፪ ኒቅያ ፷፩/።

ሥርዓተ ቅዳሴ

በቅዳሴ ጊዜ ስለሚደረጉና ሰለማይደረጉ ነገሮች ደግሞ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ያዝዛል፦
 
በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ ይጹም ይስገድ፣ የሳቀው ሕዝባዊ ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ ይላል። ምነው ፍርድ አበላለጠ ካህኑን ተቀብሎ ወጥቶ ይቀጣ አለ፤ ሕዝባዊውን ሳይቀበል ወጥቶ ይሂድ አለ ቢሉ ካህኑ የሚቆመው ከውስጥ ነው ሲስቅ የሚያየው የለም። ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ቄስ እገሌ አባ እገሌ በመሥዋዕቱ ምን አይተውበታል ብለው መሥዋዕቱን ሳይቀር ይጠራጠሩታል፤ ስለዚህ ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤ በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።
 
በቤተ ክርስቲያንና በቅዳሴ ጊዜ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ ነገር የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት የጸሎት ቦታ ናትና ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣ አይፈቀድም፣ በጣም ጭንቅ ምክንያት ወይም በሕመም ምክንያት ከሆን ግን ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ ሊወጣ ይችላል። በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁን ነጭ ልብስ ደስ እንዲያሰኝ በሥጋ ወደሙ የተገኘ ክብርም ደስ ያሰኛልና፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ባህርየ መለኮቱን በገለጸ ጊዜ ልብሱ እንደበረድ ነጭ ሆኗል። መላእክትም ወርኃ ሰላም ወርኃ ፍስሐ ነው ሲሉ የልደት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።
 
አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት ፫-፭/ ።
 
በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዖውን የማያውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና ሆኖ ሕሊናው ወደ ዓለማዊ እንዳይወስደው መቆጣጠር አለበት።
 
ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ካህኑ ለሕዝቡ ተርጉሞ ይንገራቸው ያስተምራቸው እጁንም በሚታጠብበት ጊዜ የተጣላችሁ ሳትታረቁ፣ የሰው ገንዘብ የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ ሥጋ ወደሙን ብትቀበሉ ሥጋው እሳት ሆኖ ይፈጃችኋል ደሙ ባህር ሆኖ ያሰጥማችኋል። ነገር ግን የወሰዳችሁትን የሰው ገንዘብ መልሳችሁ፣ ከተጣላችሁት ታርቃችሁ ኃጢአት ብትሰሩ ንስሐ ገብታችሁ ብትቀበሉት ግን መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ይሆናችኋል። በረከተ ሥጋውን በረከተ ነፍሱን ያድላችኋል ብሎ ይንገራቸው ያስተምራቸው ይላል።
 
በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።
 
በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያትይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።
 
ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው። ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልም “የጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለ” ይበል፣ ተሳላሚው ቄስም “መንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህ” ይበል። ለዲያቆናትም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣ ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህ” እያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንም “ልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህ” እያለ ይባርካቸው። ለሴቶችም “ልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽ” ብሎ በእጁ ይባርክ።

ስብከተ ወንጌል

“ሑሩ ውስተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት” ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንግልንም ለፈጥረት ሁሉ ስበኩ

ወንጌል፡- ወንጌል የሚለው ቃል “ዩአንጌሊዎን” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው በግእዙ ቋንቋ ብሥራት ይባላል፡፡ የግሪኩም ይሁን የግእዙ ትርጉም የምሥራች ማለት ነው፡፡

ወንጌል በሚል ቃል የተጠራው የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዜና ልደቱና ትምህርቱ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት የሠራው የአድኅኖት ሥራ ሁሉ ወንጌል ተብሏል፡፡
ወንጌል ከላይ እንዳየነው የምሥራች ሲሆን የልዑል አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም በግብረ መንፈስ ቅዱስ መወለዱን ስለሚያበሥር ነው፡፡ “እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ሉቃ 2፡10

በዚህም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ቀደመ የልጅነት ክብሩ እንደተመለሰ ሲያስረዳ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች በማለት መልአኩ ለኖሎት አበሰራቸው ከዚህ የበለጠ የምሥራች የሚባል ምን አለ? የተወለደው የሁሉ መድኃኒት ነውና ሰውን ሁሉ አዳነ ይህ ለእኛ ከደስታ ሁሉ በላይ ደስታ ነው በምንም ዋጋ የማይተመን እግዚአብሔር ለእኛ የተሰጠበት የምስራች ቃል ነው፡፡ እንግዲህ ስብከተ ወንጌል ሲባል የወንጌል ትምህርት ሲሆን ይህም የምስራችን ቃል ላለተበሠሩ ማብሠር፣ ላልተሰበኩ መስበክ፣ ላልሰሙ ማሰማት ፣ማስተማር ፣ማስረዳት ፣ማሳማን ፣በቃለ ወንጌል አምነው ጸንተው እንዲኖሩ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ከተሰጣት የአገልግሎት ሥራ ሁሉ ቀዳሚም ደኃሪም የምስራቹን ቃል መስበክ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በማስተዋል እንመልከት፡፡

“እንዲህም አላቸው ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ያመነ የተጠመቀም ይድናል” ማር 16፡15
“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላዓለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው” ማር 16፡8
“የወንጌል ሰበኪነትን ሥራ አድርግ አገልግሎትህን ፈጽሞ” 2ጢሞ4፡5 “በጊዜውም አለጊዜውም ወንጌልን ስበክ”

 

የስብከተ ወንጌል ዓላማ

ወንጌልን የማስተማር ዓላማው ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ ወንጌል በመጀመሪያ የተሰበከው በባለቤቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ማቴ 4፡17 ሉቃ 8፡1/ በመቀጠልም ከላይ እንደተገለጸው የቃሉን ትምህርት እየሰሙ የሚሰራውን የማዳን ሥራ እያዩ ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርቱን ለዚህ ምስክሮች እንደሆኑ በአንደበታቸውም የምስራቹን ቃል እንዲሰብኩ በሕይወታቸው ሁሉ የሚመሰክሩበትን የዕውቀትና ጥንካሬ መንፈስ አጎናጸፋቸው ሉቃ 24፡47 – 53 እነሱም እንዲህ እያሉ መሰከሩ፡፡

“ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን” 1ዮሐ 1፡1 እንዳሉትም፡-

 • ጆሮአቸው የሰማውን ቃለ ወንጌል ሰበኩ፤
 • ዓይናቸው ያየውን የማዳኑን ሥራ መሰከሩ፤
 • በእጆቻቸው የዳሰሱትን ሁሉ አረጋግጠው ተናገሩ፡፡

በዚህ የወንጌል ስብከታቸው ልባቸው የተነካ ሰማዕያን ወንድሞች ሆይ እንድንድን ምን እናድርግ አሉአቸው የሐዋ ሥራ 2፡37፣16፡30
ከጨለማ ወደ ሚደነቀው ብርሃን የሚያወጣውን የምስራቹን ቃል ከሰሙ በኋላ ሐዋርያትን ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ምንስ መሥራት ይገባናል ብለው ሰሚዎቹ መጠየቃቸው የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ከሐዋርያቱ ጋር አብሮአቸው ይሠራ እንደነበር ማስረጃ ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅ/ማርቆስ “እነሱ ወጥተው በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ ጌታም ከእነሱ ጋር አብሮአቸው ይሠራ ነበር በሚከተሉትም ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” በማለት እንደጻፊው /ማር16፡20/ በዚሁ ሁኔታ የቃሉ ባለቤት የተናጋረውን ልበ አእምሮ እያበራ የሰሚውን እዝነ ህሊና እየከፈተ የምስራቹ ቃለ ወንጌል ለሁሉም ደረሰ በዘባነ ኪሩብ የሚመሰገነው ልዑል አምላክ በጎል የተወለደው ሰዎችን ለማዳን በመሆኑ ታላቅ ደስታን አጎናጸፈ“ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና” ቲቶ 2፡11

ስለሆነም ሐዋርያቱም ከነሱ ቀጥለው በወንጌል አገልግሎት ላይ የተሾሙ ሁሉ በቃለ ወንጌል እያሳመኑ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ አገለገሉ፡፡

 

ስብከተ ወንጌል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ወንጌልን በሁለት መንገድ ትሰብካለች እነዚህ የስብከተ ወንጌል ዓይነቶች ሕይወትና ዕውቀት ናቸው፡፡

1.    በዕውቀት

ከአበው ሐዋርያት ጀምሮ የተምሮ ማስተማርን ፈለግ በመከተል የወንጌሉን ሙሉ ዘርዓ ቃል በአእምሮአቸው ሰሌዳ በመጻፍ ትርጓሜውን በርቱዕ አንደበታቸው የሚተነትኑ ምሁራንን በማፍራት የዕውቀት ማኅደር መሆኗ ይታወቃል ፡፡ እነዚህ ምሁራኖቿ የሚናገሩ መጻሕፍት ናቸው ፡፡ ከእነዚህ የሚቀዳው የትርጓሜ ወንጌል ምሥጢር ሌላውን የወንጌል ደቀመዝሙር ይወልዳል ይህ አንዱ ትልቁ የወንጌልን ምሥጢር በከፍተኛ ትርጓሜ ደረጃ የመተንተን የማስረዳት መንገድ ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ቀለል ባለ አገላለጽ ለሰሚዕ አእምሮ በሚመጥን ደረጃ ሆኖ ከሕይወታቸው ጋር እያዛመዱ የምስራቹን ቃል መስበክ ነው ለዚህ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምሁራኖቿ የበለጠ የክህሎት ማበልጸጊያ መንፈሳዊ ከሌጆችን በማቋቋም አሠልጥና የክህሎት ምስክር ሰጥታ የሰለጠኑትን በመላው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በዓለም ዓቀፍ ሁሉ አሰማርታ እየሠራች ትገኛለች፡፡

2.    የሕይወት ስብከት

በሕይወት መስበክ በዕውቀት ከሚሰበከው በላይ ሌላውንም ያሳምናል የሕይወት ስብከት ስንል ጾረ መስቀሉን በሕይወት ትክሻ ተሸክሞ ክርስቶስ ለሁሉም የተቀበለውን መከራ ማሳየት ነው፡፡ ሐዋርያው “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራልን” እንዳለው /2ቆሮ4፡11፣ ቁላ1፡24/ የዓለምን የሞቀ የደመቀ ካባ ከመልበስ የጣመ የላመ ከመጉረስ የሕይወትን መስቀል ተሸክሞ እንደ ወንጌል ቃል በእግዚአብሔር መንግሥት ከፀሐይ ሰባት እጅ በርቶ ለሌላው ማብራት /ማቴ 13፡43/ ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ የሕይወት ሰብከት ወንጌሉን በቃል ሳይሆን በሕይወት የረተጎሙ ብዙ ቅዱሳንና ቅዱሳት በማህጸኗ ተጸንሰው ተወልደው ፍሬአቸውን አበርክተዋል፡፡ ለዚህ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን እና ኢትዮጵያን በደንብ አድርጎ መመልከት በጆሮ ከሚሰሙት በላይ ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ በወርቃማ የሃይማኖታዊ ቀለም የተጻፉ ገዳማቶቿ ሕያዋን ምስክሮቿ ናቸው፡፡ ዓለም ያለውንና የነበረውን በዘመንዮሽ ቁሳዊነት እየለወጠ የራሱን ማንነት እያጣ ባለበት በአሁኑ ዘመን እንኳ የእስዋ ገዳማት የወንጌል ቃል የሕይወት ትርጉም አንባዎቿ ናቸው፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያዊቷ /ብሔራዊቷ/ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን በወንጌል የተመሰረተች ቃለ ወንጌልን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር /በሕይወት/ የምትሰብክ ሕያዊት ቤተክርስቲያን ናት፡፡

 

ስብከተ ወንጌል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚመራቸው ከ160 በላይ የሆኑ ታላላቅ ካቴድራሎች፣ ገዳማትና አድባራት ያሉት ሲሆን ሀገረ ስብከቱ የሀገሪቷ ዋና ርዕሰ ከተማ በሆነችው ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሥራውም እጅግ ሰፌ ነው፡፡
ሀገረ ስብከቱ የቤተክርስቲያኗን መሠረታዊ የወንጌል ስብከት አገልግሎት ለማከናውን እንዲቻል ካሉት ትላልቅ መምሪያዎች አንዱ የስብከት ወንጌል መምሪያ ነው በዚህ መምሪያ አስተባባሪነት ደግሞ በ160 አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ እጅግ ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል በተለይ ባለፉት ዓመታት የስብከተ ወንጌል የኅብረት ጉባኤ በመባል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስራችነት በሀገረ ስብከቱ ሙሉ አስተተባባሪነት በመላዋ አዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት መርሐግብሮች

 1. የየዕለት ጉባኤያት ዘወትር ከ11 – 1፡00 የሚካሄዱ
 2. የወርኃዊያን ልዩ ጉባኤያት በልዩ ዝግጅት የሚካሄዱ
 3. የወርኀዊያን ጉባኤ በዓላት በልዩ ዝግጅት የሚካሄዱ
 4. የዓመታውያን  ጉባኤያት በዓላት በልዩ ዝግጀት የሚካሄዱ  ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችንም የተለያዩ የስብከተ ወንጌል ልዩ ጉባኤያት በማዘጋጀት ሀገረ ስብከቱ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እያስተባበረ፣ እየመራና እያሠራ ይገኛል፡፡

ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምን መደረግ አለበት

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር መሆኑ የታወቀ ነው፤ በተለይ ለአገልግሎት መቃናት በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት አገልግሎቱ በሚጠይቀው የሙያ ብቃት መምህራንን በመመደብ፤ አቅምን ያገናዘበ በቂ በጀት በመበጀት፤ ለሥራው አስፈላጊ ማቴሪያሎችን በማሟላት፤ አገልግሎቱ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ እንዲሰጠው ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
የደረስንበት ዘመንና እየተቀበልነው ያለው ጊዜ በሁሉም ዘርፍ በግሎበላይዜሽን አስተሳሰብ ጥላ ውስጥ እያስባገን ስለሆነ ሰዎች በማዕበሉ አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የወንጌሉን ቃል በምልዓት መስበክ አእምሮአዊ ሚዛናቸው ወዳልሆነ አካሄድ እንዳያጋድል ማድረግ የቤተክርስቲያኒቱ እና የሀገረ ስብከቱ ሃይማኖታዊ ኃላፊነት ነው፡፡