የልማት እንቅስቃሴዎች

ልማት በቤተክርስቲያን እንደ ተጀመረ ሥነ ፍጥረት በሰፊው ያስረዳል በመሆኑም ሥራ/ልማት የተጀመረውና የተገኘው ከፈጣሪያችን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ከዚያም በቅደም ተከተል 22ቱን ፍጥረታት ከእሁድ እስከ ዓርብ በ6 ቀናት ፈጥሯል /ዘፍ 1፡1/ በአጠቃላይ ሥራ /ልማት ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ትዕዛዝ ሠርታ ሕብረተሰቡን የማሠራትና የማስተማር ተቀዳሚ ዓላማዋ ነው፡፡ ሥራን የማይወድ ሰው ሃይማኖት አለኝ እግዚአብሔርን አምናለሁ ብሎ መናገር ፈፅሞ አይቻለውም ይኸውም እንደ ቅዱሳት መፃህፍት አስተምሮ ሃይማኖት የሚገለፀው በሥራ ነው ሥራም የሚታወቀው በሃይማኖት ነው፡፡ በአጭሩ በሥራ ያልተገለጸ ሃይማኖት ዋጋ የለውም ማለት ነው፡፡ ከዚህም በመነሳነት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በገጠርና በከተማ ባሉ ገዳማትና አድባራት ከጥንት     ጀምሮ

 • በመስኖ ልማት ፤
 • በእርሻ ልማት ሥራ ፤
 • በከብት እርባታ ልማት ፤
 • በንብ እርባታ ልማት ፤
 • በሕንፃ ግንባታ ልማት ፤
 • በእደ ጥበብ ልማት ስራ፤
 • በትምህርትና በመሳሰሉ መሰረታዊ ልማቶች ተሰማርታ ስታለማ ቆይታለች አሁንም ዘመኑ በሚፈቅደው መልኩ የተለያዩ ልማቶችን በማልማት ላይ ትገኛለች ፡፡ለዚሁም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የልማት ሥራ በየገዳማቱና አድባራቱ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ አቅም በፈቀደው መልኩ የተለያዩ ልማቶችን በማልማት ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህም ልማቶችም ዋና ዓላማ፡-
 1. ቤተክርስቲያኒቷ በገቢ ራሷን እንድትችልና መንፈሳዊ አገልግሎቱ በአግባቡ እንዲገለገል ለማድረግ ፤
 2. ለሕብረተሰቡ የተሟላ ማህበራዊ አገልግሎትን ለመስጠት
 3. የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሆኑ የካህናትና ልዩ ሠራተኞች ኑሮ ደረጃ የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ

ስለሆነም ሀገረ ስብከቱ፡-

 1. በትምህርት ዘርፍ
 2. በጤና የሥራ ዘርፍ
 3. በሕንፃ ግንታ ሥራ ዘርፍ
 4. በእደ ጥበብ ሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ ህብረተሰቡን ሊጠቅም የሚችል ሥራ እሠራ ይገኛል  

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከእቅድና ከልማት ክፍሉ ጋር በመሆን ልማት ነክና ከሕንፃ ግንባታ ጋር ተያዥነት ያላቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

 • የአብያተ ክርስቲናት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙና በልማት ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል
 • በየገዳማቱና አድባራቱ መሰረተ ልማት እንዲስፋፋ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በመነጋገርና በመመካከር ምዕመናኑን በማስተባበር፤ ልማት ኮሚቴዎችን በማስመረጥና በማጠናከር ዘርፈ ብዙ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን እያስፋፋና እየሠራ  ይገኛል፡፡
 • በቀጣይም የሀገረ ስብከቱ ገቢ ማስገኛ የሚሆን ባለ 20 ፎቅ ሕንፃ ለመሥራት በዝግጅት ላይ ይገኛል::

ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት – ታሪክ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ቀጥሎ በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር መሰረት የመንበረ ጳጳስና ሀገረ ስብከት መስርቶ በአገሪቱ ዋና መዲና ሆኖ ሥራውን ሲሠራ የነበረና አሁንም አሰራሩን አጠናክሮ በመስራት ላይ የሚገኝ ግዙፍ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀደም ሲል እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የሸዋ ሀገረ ስብከት ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ 12 አውራጃዎችም ነበሩት::

ለምሳሌ ያህል፡-

  1. መናገሻ አውራጃ
  2. ፍቼ ሰላሴ አውራጃ
  3. ጂባትና ሜጫ አውራጃ
  4. ጮቦ ጉራጌ አውራጃ
  5. ከንባታ አውራጃ
  6. የረርኮረዩ አውራጃ
  7. ዝዋይ አዳሚቱሉ አውራጃ
  8. መንዝና ግሼ አውራጃ
  9. መርሃቤቴ አውራጃ
  10. ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ
  11. ይፋትና ጥሙጋ አውራጃወዘተናቸው፡፡

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቤ/ክ፣ ነገስታትና ሕዝብ መልካም ፈቃድ ወደ እስክንድርያ ተልኮ ለጵጵስና የበቃው የመጀመሪው ጳጳስ አባ ፍሬምናጦስ ሲሆን መጠሪያውም “ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወዘኩላ ኢትዮጵያ” የሚል ነበር፡፡ ከእርሱ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በእስንድሪያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር አንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ለአንድ ሺህ ዓመት ያህል መቆየቷ ይታወሳል በመሆኑም በአፄ ዘርዐያዕቆብ ዘመነ መንግስት በ1438 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከግብፅ ፓትርያርክ ዮሐንስ 14ኛው አማካኝነት የሸዋ ሀገር ሰብከት ሊቀጳጳስ ሆነው ተመድበው የነበረ ሲሆን በመቀጠልም በአፄዮሐንስ ጊዜም በ1874 ዓ.ም አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በመሆን ሀገረ ስብከቱን አገልግለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የራስዋን አህጉረ ስብከት መመስረት የጀመረችው ከራስዋ ልጆች መካከል ፓትርያርክ ባገኘች ጊዜ ሲሆን በ1943 ዓ.ም. የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው የተሸሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ጎርጎርዮስ ቀዳማዊን የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አድርገው ሹመውነበር፡፡ በመቀጠልም የሸዋ ሀገረ ስብከት በአያሌ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳትና ሥራ አስኪያጆች ሲመራ ቆይቶ ከተማው እየሰፋ፣ ሕዝቡም እየበዛ በመምጣቱ ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተብሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብቻ ሆኖ የአዲስ አበባን ምዕመናንና ካህናት በመምራትና በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል በቅርብ ጊዜ አዲስ አበባ ሀገረስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ደረጃ ከመሩና እየመሩ ካሉት ሊቃነጳጳሳትና ሥራ አስኪያጆች መካከል፡፡

  • ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስካልዕ
  • ብፁዕ አቡነ በርናባስ
  • ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ
  • ብፁዕ አቡነ ማትያስ
  • ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ
  • ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ
  • ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
  • ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
  • ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ
  • ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልና ብፁዕ አቡነ ዳንኤል(ሀገረ ስብከቱ ለ4 በተከፈለበት ወቅት)
  • ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ
  • ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
  • ብፁዕ አቡነ አረጋዊ
  • ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅ ናቸው::

በሥራአስኪጅነት:

  • ሊቀ ካህናት ሰንቄ ደበላ
  • መልአከ ሰላም ጎሃ ጽባህ ወ/ሐዋርያት
  • ሊቀ ሥልጣናትአባ ገ/ማርያም አፅብሐ
  • ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ማርያምፈለቀ (ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ)
  • ለቀ ካህናት ሃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ
  • ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገ/አማኑኤል
  • መልአከ ሰላምአባ ገ/ሚካኤል በየነ(ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ)
  • ሊቀ ስዮማን ራደ አስረስ
  • መልአከ ገነት አባ ሃይለ ማርያም መውደድ
  • አለቃ መኮንን ገ/መድህን
  • መምህር አባ ተከስተ ወ/ሳሙኤል (ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል)
  • መልአከ ፀሃይ አባ ተክለ ህይወት ማህፀንቱ
  • ሊቀመዕምራንመኩሪያደሳለኝ
  • ሊቀማዕምራንፈንታሁንሙጬ
  • ንቡረዕድአባ ገ/ማርያም ገ/ሥላሴ
  • ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ
  • ሊቀ ህሩያን ሠርፀ አበበ፣መልአከ ፅዮን አባ ህሩይ ፣ንቡረ ዕድ አባ ዮሐንስና መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ(ሀገረ ስብከቱ ለ4 በተከፈለበት ወቅት)
  • መጋቤ ሐዳስ ይልማ ቸርነት
  • ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን
  • ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ
  • መምህር ጎይትኦም ያይኑ
  • መ/ር ይቅርባይ እንዳለ
  • ቆሞስ አባ ሞገስ ኃ/ማርያም
  • ቆሞስ መልአክ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ
  • መ/ር አካለወልድ ተሰማ (በአሁኑ ሰዓት ሀገረ ስብከቱን በመምራት ላይ የሚገኙ)ናቸው::

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ጊዜ ከ230 በላይ የሚሆኑ ገዳማትና አድባራት እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንና በብዙ ሺ የሞቆጠሩ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች እየመራና እያስተዳደረ የሚገኝ ሲሆን ሀገረ  ስብከቱ ከመንፈሳዊ አስተዳደር ጎን ለጎን ማህበራዊ/ህዝባዊ አስተዳደርና መሠረተ ልማትም በከፍተኛ ደረጃ እያከናወነ ይገኛል፡፡