4

የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት

በስመአብ ወወልድ ወመነፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

4
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ
የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት

ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋለበት እየዋሉ ከአደረበት እያደሩ ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊ ምሥጢር ተአምራትንና መንክራትን እያዩ ቃሉን ኢየሰሙ ዓለምን ሁሉ አስተማሩ፤ ዓለምን በደሙ አድኖ ተነሥቶ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስን ገንዘብ አድርገው በእኔ ያመነ እኔ የምሠራውን ይሠራል ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት እሱ ይሠራው የነበረውን እየሠሩ ኑረዋል፡፡ ለቀጣዩ ትውልድም አስተላልፈዋል፡፡ ቀጥለው የነበሩና ያሉ ሊቃውንትም ተመርምሮ በማያልቅ መንፈሳዊ ጥበብ ሲራቀቁ ቆይቷል፡፡ እየተመራመሩም ይገኛሉ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለነፍስ መቆም አትችልም እንዳለው መንፈሳዊን በመንፈሳዊ ጥበብ ሥጋዊውን ለሥጋ በሚያመቸው መሠረት በምድራዊ ጥበብ ማለትም በግዙፉ እግዚአብሄር ከፈጠረው ከመሬት በተገኘው ቁሳቁስ ሲመራመሩ ቆይቷል፡፡ አሁንም የዘመኑ ትውልድ ጥበብን የሚገልጽ መንፈስ ቅዱስ ገልጾላቸው አባቶቻችን በረቂቅ መንፈስ ሲጓዙት የነበረውን ሕዋ በረቂቅ አየር ሲጓዙት ይገኛሉ፡፡ በዚሁ መነሻነት ቤ/ክርስቲያናችንም የመሪዋ የኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያትን ረቂቅ መንፈሳዊ ጥበብን ሳትለቅ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ እየተጠቀመች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ የታሪክ የኢኮኖሚያዊ፤የማህበራዊ፤ሥልጣኔና ዕድገት በረዥም ዘመን ጉዞዋ ያበረከተችው እሴት ለአፍሪካዊያን መኩሪያና ለመላው ዓለም በታሪክ መዝገብ ከፍተኛሥፍራየሚሰጣት ቤተክርስቲያን መሆንኗ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡

ለሀገራችን የታሪክና የመልካም ገፅታ መንፀባረቂያ የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገራችን ዕድገትና ህዳሴ ትልቅ ድርሻ አበርክታለች አቅም በፈቀደ ሁሉ አሁንም ድርሻዋን በማበርከት ላይ ትገኛለች፡፡ በሀገሪቱ ዋና መዲናችን በአዲስ አበባ ከተማና በኢትዮጵያ የሚገኙት ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር ለሀገሪቱ ማንነት የስኬት ውጤት ዋና መሠረቶች ናቸው፡፡በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ጥንታውያን አድባራትና ገዳማት /ካቴድራሎች/ ለምዕመናን በየቀኑ ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኝዎች በቱሪስት መስህብነት የሚሰጡት አገልግሎት በእጅጉ የላቀ ነው ፡፡ይህም የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ ከመግለፅ ባሻገር በቱሪዝሙ ረገድ ለሀገሪቱ እድገትና ምጣኔ ሀብት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር የሚሰጡት አገልግሎት/አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

በመሆኑም በአዲስ አበባ የሚገኙ ታሪካዊያንና ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናትን የበለጠ ለማወቅ የተዘጋጀው ይህ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ ለአብያተ ክርስቲያናት ጠቃሚ መረጃን ከመስጠት በተጨማሪ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ሀገር ጎብኚዎች የማንነት መገለጫ የሆኑትን ታሪካዊ መረጃዎችን በመስጠት የሚሰጡት አገልግሎት ጠቀሜታው እጅግ በጣም የላቀነው ብዩ አምናለሁ፡፡

በመሆኑም ቤተክርስቲያችን ብዙ ዘመናትን ተሻግራ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ የደረሰች ሲሆን ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሃይማኖት ለትውልዱ ዘመኑ በሚፈቅደው መሳሪያ በመገልገል ሐዋሪያዊ መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊነው ፡፡ ወጣቱ ትውልዱ ቴክኖሎጂውን ሲጠቀም መንፈሳዊ ትምህርትም በያሉበት እንዲያገኙና በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲጠነክሩ/እንዲበረቱ ማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑም በተጨማሪ አጠቃላይ የአህጉረ ስብከቶችም ይሁን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ መልዕክት ለማስታላለፍ ጥሩ አማራጭ መንገድ ነው።በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያናችን በተለይም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከቶች በቴክኖሎጂው መስክ እየተሠራ ያለው ሥራ ጅምሩ የሚበረታታ ቢሆንም ከሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አኳያ ሲታይ ግን ገና ብዙ የሚጠበቅብን በመሆኑ የተጀመሩትን መልካም የሥራ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪዩን አቀርባለሁ ፡፡

           መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ መልዕክት

2

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረው ዓመታዊው የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በድምቀት ተከበረ

 

በዲ/ ዘሩ ብርሃኔ

ታኅሣሥ 19 ቀን 2005 ..

እኛ የምናመልከው አምላክ ኪሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፡፡ .ዳን.317

 

በመጀመሪያ እንኳን ለኃያሉ መልአክ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን፡፡

 

 

 

በየዓመቱ ታህሳስ 19 ቀን የሚከበረው ዓመታዊው  ኃያሉ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዓለ ንግሥ በዚህ ዓመትም እጅግ በጣም ደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ውልዋል፡፡በዓሉ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባለበት ሁሉ ተከብሮ የሚውል ሲሆን ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናትና መዘምራን እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ሥነ ስርዓት በየአመቱ ሁል ጊዚ ተከብሮ ይውላል፡፡በዘንደሮ ዓመትም እንደተለመደው በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡በተለይም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ባሉ የቅዱስ ገብርኤል አጢቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዓሉ በድምቀት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ምእመናንም ተኝተዋል፡፡በተለይም በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እጅግ በደመቀ ሁኔታ በአሉ ተከብሮ ውሏል፡፡በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል
የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ፤ካህናት፤መዘምራንና ብዛት ያለቸው ምዕመናን በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ታህሳስ 19 ቀን ጀምሮ ሲሆን የገዳሙ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምረው 32 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡

ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ//// ልዩ በመሆኑ ለእምነቱ ተከታዮች ምእመናን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እጀግ በጣም የሚያስደንቅ በዓል ነው፡፡

 

 

 

 

 

ዛሬ የምናከብረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከባቢሎን እሳት ያዳነበት ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው በብሉይ ኪዳን ዘመን 605-562 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በነገሠው በናቡከደነጾር ዘመን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከጣዖት አምላኪና አስመላኪ ኀያላን ነገሥታት መካከል አንዱ ናቡከደነጾር ነበር፡፡ ምስሉ የቆመው 587 // እንደሆነ መተርጎማን ያስረዳሉ፡፡ ዳን.31 ናቡከደነጾር እስራኤላውያንን በማረከበት ዘመን ዳንኤልንና ሦስቱን ሕፃናት በልዩ ሁኔታ አክብሯቸው ነበር፡፡

 •          ዳንኤልን ብርጣሶር አለው አሰበ በል አምኃ ቤል ሲል ነው
 •          አናንያንም ሲድራቅ አለው ወልደ ሰቃየ አትክልት /አትክልተኛ/ ማለት ነው
 •          ሚሳኤልንም ሚሳቅ አለው ፀሐቂ ተጋሂ ፍንው ለግብር መልእክት  /ትጉህ ፈጣን መልእክተኛ/ ማለት ነው፡፡
 •        ü  አዛርያንም አብደናጎም አለው ገብረ ዳጎን /የጣዖት አገልጋይ/ ማለት ነው፡፡
 • የቀድሞ ስማቸው ትርጉም ግን
 •       ዳንኤል ማለት ፍትሕ እግዚአብሔር ዳኛ እግዚአብሔር
 • አናንያ ማለት ደመና
 • ሚሳኤል ማለት ሰምዓኒ እግዚአብሔር /እግዚአብሔር ስማኝ/
 • አዛርያ ማለት ረድኤት ማለት ነበር፡፡ .ዳን.17

ንጉሡ እነዚህን ሕፃናት ለሦስት ዓመት በቤተ መንግሠት ጥሩ ምግብ እየተመገቡ የከለዳውያንን ትምህርትና ቋንቋ ያጠኑ ዘንድ አዝዞ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ትምህርቱን እየተማሩ በንጉሡ ቤት የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ሳይመገቡ ጥራጥሬና ውኃ እየተመገቡ በፈተና ያለፉ ነበሩ፡፡ ዳን.18-21

ጠቢባንና አስተዋዮች በመሆናቸው በባቢሎን አውራጃዎች ላይ ተሾሙ፡፡ ዳን.246-49 የሠለስቱ ደቂቅ በንጉሡ ዘንድ መወደድና መሾም ያስቀናቸው ባቢሎናውያን ለናቡከደነጾርበባቢሎን ሀገሮች ለሚሠራ ሥራ የሸምካቸው ከአይሁድ ወገን የሚሆኑ ትእዛዝህን እምቢ ያሉ አምላክህን ያላመለኩ ለሠራኸውም ለወርቁ ምስል ያልሰገዱ ሚሳቅና ሲድራቅ አብደናጎም የሚባሉ ሦስት ሰዎች አሉብለው ከሰሷቸው ያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጣና እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ እነርሱም አንሰግድም አሉ፡፡ ዳን.313-19”

ናቡከደነጾር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ለምስሉ ለማሰገድ ጥረት አድርጓል

 1. በመጀመሪያ ዐዋጅ በማወጅ ነው ይህ ዐወጅ ከተራው እስከ ባለሥልጣናቱ ያሉትን የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም ባለሥልጣናቱ ቀድመው በመስገድ አርአያ እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡
 2. ሁለተኛው የሕዝቡን ልብ በሙዚቃ እንዲደሰቱ በደስታው ተውጠው ሳያስቡት እንዲሰግዱ ማድረግ
 3. የመጨረሻው በማስፈራራት /ወደ እሳት ትጣላላችሁ እያለ/ እንዲሰግዱ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢያባብልና ቢጥር ሠለስቱን ደቂቅ ለማሰገድ ያደረገው ሙከራ  አልተሳካለትም፡፡

ከሠለስቱ ደቂቅ ሦስት ነገሮችን እንማራለን

ማመን፣ መቁረጥ እና ማድረግን፡፡ ሃይማኖት እነዚህን 3 ነገሮች ይፈልጋል፡፡ ሦስቱ ሕፃናት በእግዚአብሔር ፍጹም አመኑ፣ ይህንንም እምነታቸውን ሲገልጡየምናመልከው አምላካችን ከሚነደው እቶን ያድነን ዘንድ ይችላልበማለት ተናግረዋል፡፡ የመጣባቸውን ሁሉ ለመቀበል ወሰኑ ቆረጡአምላካችን እኛን ማዳን ይችላል ነገር ግን ፈቃዱ ከዚህ እሳት ገብተን ሠማዕትነትን እንድንቀበል ቢሆን ከእሳት እንገባለንበማለት አንድ ልብ፣ አንድ ቃል ሆነው አቋማቸውን ገለጡ፡፡ የቆረጡትን ነገር አደረጉት፤ ወደ እሳት ውስጥ ተወረወሩ ሦስቱም ነገሮች ስለተፈጸሙ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ እሳቱን አብርዶ አዳናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩየእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማልበማለት የተናገረው ቃልም ተፈጽሞላቸዋል፡፡ /መዝ.337/ ጠባቂ መልአካቸው ቅዱስ ገብርኤል በእሳት ውስጥ ገብቶ ከመከራ ሥጋ አድኖአቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራና መልአኩል ልኮ የፈጸመውን ትድግና ያየው ናቡከደነጾርናቡከደነፆርም መልሶ፡መልአኩን የላከ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብድናጎም አምላክ ይባረክ፡፡ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብድናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቆረጣሉ ቤቶቻቸውም የጉድፍ መጣያ ያደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ፡፡ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብድናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፡፡ዳን.328-30

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና የኃያሉ መልአክ የሊቀ መላእክት   የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃው፤ ተራዳኢነትና በረከቱ አይለየን አሜን ፡፡

 

ታሪካዊ ቦታዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ማዕከል ብቻ ሳትሆን የምጣኔ ሀብታዊ፤ማህበራዊ፤ሥነ ጥበባዊ፤የሥልጣኔ እና የነገሥታት ገድሎች ዜና መዋዕሎች መረጃ መዕክል ናት፡፡ለምሳሌ ያህል ፡-የኩሱም፤ላሊበላ፤ደብረ ብርሃን ሥላሴ ፤ጣና ሀይቅ እና  የመሳሉትን ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአዲስ አበባም ታሪካዊና አስደናቁ የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎች በብዛት የገኛሉ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉም ታሪካዊ ቤተመዛክርት ቢሆኑም ቤተመዘክር ሠርተው በቤተመዘክርነት ደረጃ ከሚያስጎበኙ ገዳማትና አድባራት መካከል፡-

 1. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተመዘክር፤
 2. የገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ ቤተመዘክር፤
 3. የርዕስ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ማርያም ቤ/ክ ቤተመዘክር፤
 4. የታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ቤ/ክ ቤተመዘክር ወዘተ መጥቀስ ይቻላል

በእነዚህ ቤተመዛክርት ወስጥ ደረጃቸውን በጠበቀ በዘመናዊ  አደረጃጀትና ጥበቃ ተይዘው በመጎብኘት ላይ ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ውድና ማራኪ የሆኑ ቅርሶች በዋጋ ሊተመኑና በምንም ሁኔታ ሊተኩ የማይችሉ ናቸው የተሰጡትም ከቀድሞ ነገሥታት፣ ከእቴጌዎቹ፣ ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ መንግሥት ልዑላንና ልዕልቶች፣ ከቀድሞ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖችና ከ5ቱ አኅት አቢያተ ክርስቲያናትም ጭምር ሲሆን ደኅንነታቸውም ለረጅም ዘመናት በሚባ ተጠብቆላቸው ከዚህ ትውልድ ደርሰዋል፡፡

የተሠሩትም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከመሳሰሉት ማዕድናት ሲሆን የወርቅና የብር ቅቦችንም ያጠቃልላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ የተዘጋጁ የቤተ መቅደስ አልባሳት፣ ድባብ ጥላዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ይልቁንም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ጸሐፍትና አርእስት በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ በርካታ ሃይማኖታዊ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍትም በእነዚህ ቤተመዛክርት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል በ6ኛው መ/ክፍለ ዘመን በቅ/ያሬድ በ8 የዜማ ምልክቶችና በ3 የዜማ ቅኝቶች ከተደረሱት አምስቱ የዜማ መጻሕፍት ውስጥ አንዱና ከ5ዐዐ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆረጠው ድጓ ተብሎ የሚታወቀው መጽሐፍ በይዘቱም ሆነ በጣዕመ ዜማው በእጅጉ ከሚመስጡትና ከሚያስደንቁት ዋነኛው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ከእነዚህ ከ3ቱ ቅኝቶች ውጭ የሆኑ የዜማ ስልቶች የሏትም አትጠቀምም፡፡ ቅኝቶቹም ዘመን የማይሽራቸው ጊዜ የማይገድባቸውና የማይሰለቹ ሰማያዊ ስጦታዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመንፈሳዊው ምንጭ የተቀዳ የራሷ የሆነ ፊደል፣ አኃዝ (ቁጥር)፣ ቀናትና አዝማናት መቁጠሪያ (ካላንደር) ያላት በመሆኗ ከሌላው የዓለም ክፍል ይልቅ በዚህ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበቧ የተለየች ያደርጋታል፡፡

የቤተመዘክሮቹ ዋና ዓላማ

 • ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የሆኑትን የቤተክርስቲያን ቅርሶች በሙዚየም ውስጥ በማደራጀት በልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ይዞ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጐብኝዎች በማስጐብኘት የቤተክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ገጽታ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ፣
 • እነዚሁ አስደናቂ ታሪኮችንና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን በጥንቃቄ ጠብቆ በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል በየክፍላቸው መድበን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

 1. 1ኛ. ከታሪካዊ ቅርሶች
  • የነገሠታቱ የቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክብር ዙፋኖች፣
  • የነገሥታቱ የአርበኝነት አልባሳት፣
  • በሞዛይክ ቅርፅ የተዘጋጀ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ምስል (ፖርትሬት) እና ሌሎችም፣
 2. 2ኛ. ከሃይማኖታዊ ቅርሶች
  • በተለያየ ዲዛይን የተሠሩ መስቀሎች፣
  • ልዩ ልዩ ጽዋዎችና ጻሕሎች ከነእርፈ መስቀሎታቸው፣
  • የተለያዩ ወርቀ ዘቦና የብር ጥልፍ (ሙካሽ) ሥራ ካባዎችና ድባብ ጥላዎች፣
  • የተለያዩ የብራና ቅዱሳት መጻሕፍት ገበታቸው በወርቅና በብር የተለበጡ ጭምር፣
  • ከዕንቀ፣ ከብርና ከሞዛይክ የተሠሩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ ሥነ-ስቅለትና የመሳሰሉት ይገኛሉ፣
   ሰጭዎቹም ዘርዝር
  • ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ከሌሎችም አባቶች፣
  • ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፣
  • ከቀ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣
  • ከንግሥት ዘውዲቱ፣
  • ከእቴጌ ጣይቱ፣
  • ከእቴጌ መነን፣
  • ከልዑላትና ከልዕልቶቹ፣
  • ከቀድሞ ቤተ መነግሥት ባለሥልጣናት፣
  • ከበጎ አድራጊ ክርስቲያኖች፣
  • ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌላም

እነዚህ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይልቁንም ባለሀብቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ጠብቆና ተንከባክቦ ለቱሪዝም ሴክተሩ እንቅስቃሴ ቢጠቀምባቸው በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል እንላለን፡፡ሙሉውን መረጃ ለማግኘት መጥታችሁ ትጐበኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በአክብሮት ትጋብዛችኋለች፡፡

መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች

የቤተ ክርስቲያኒቷ መሰረታዊ ተልእኮ  ለሰው ልጆች መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን መስጠት ነው ለዚህም ነው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ለዘመናት ያለምንም የሃይማኖት፣ የዘር፣ የፆታ ልዮነት ከህዝቦች ሁሉ ጋር ተቀራርባ በመሥራት ሰብዓዊ ተግባራትን የሞትፈፅመው የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ለማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ልማት መስፋፋት የራሷን ልዩ አስተዋፅኦ በማድረግ የሀገሪቱን ልማት የምታለማና የምትደግፍ ብሔራዊት ቤ/ክ ናት፡፡

የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የትምህርት ታሪክ እንደሚያስረዳን ቤተ ክርስቲኒቷ የትምህርታዊ ሥነጽሑፍ ሥርዓት ምንጭ እንደሆነች ያስረዳል ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርታዊ አገልግሎት በኢትዮጵያ የግዕዝ ፊደላትን ፣ የቀን መቁጠሪዎችና ቋንቋዎችን ከመቅረፃና ከማሳደግ ጀምራል፤ የታረክ ቅርሶች፣ የጥናትና ምርመር ሊቃውንት እንዲያሚረጋግጡት በኢትዮጵያ የጽሕፈት ሥራ የተጀመረው
ከክርስቶስ ልደት ከ1000 ዓመት በፊት ጀምሮ ነው፡፡ በመሆኑም የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የፅህፈት ሥራ ላይ ያዋለችው እምነቷን ማስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ስለሆነም የግዕዝ ቋንቋና ፊደላት በአክሱም ዘመነ መንግስት የበላይነትን እያገኙ በሀውልቶችና በሌሎች ነገሮች የሚጻፉ ጽሑፎች በግዕዝ ቋንቋና ፊደላት በመጠቀም የትምህርት ሥርዓቷን ማሳደግ ችላለች፡፡

የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቦቿ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ትምህርታዊ ህይወት ውስጥ ታላቅ ድርሻ አበርክታለች እያበረከተችም ትገናለች፡፡ የጥንቱ ትምህርት መለያ ባህሪ ያገኘው ልዩ ከሆነው ከሀገሪቱ ክርስቲያናዊ ውርስ ነው ክርስትና በተሰፋፋባቸው የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ቤተ ክርስቲያኒቷ ዋናውን የኢትዮጵያን ጥንታዊ ባህል መሥርታለች ከዚህም የተነሳ ለብዙ መቶ ዓመታት ጥንታውያን ትምህርት ቤቶችን ማቋቋምና ማስፋፋት ችላለች የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ትምህርት ጠብቆ ለማቆየት አገልግሏል ለትውልድም ሊተላለፍ የቻለው በዚህ ሥርዓት አማካንነት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ሥርዓት የሚከተሉት ዋና ክፍሎች አሏት እነርሱም፡-

 1. ንባብ ቤት
 2. ቅዳሴ ቤት
 3. ዜማ ቤት
 4. ቅኔ ቤት
 5. መጽሐፍ ቤት ናቸው

መንፈሳዊ ዜማ ቤት

የቤ/ክ መዝሙር በሰፊው የሚሰጥበት ት/ቤት ዜማ ቤት በመባል ታወቃል፡፡ ዜማ ማለት በግዕዝ፤በዕዝልና በዓራራይ የሚገር ከሰማየ ሰማያት የተገኘ መንፈሳዊ የመላእክት መስጋና ማለት  ነው፡፡ይህም ግዕዝ በአብ፤ዕዝል በወልድ እና ዓራራይ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሰል ነው፡፡ በታወቀው የዜማ ደራሲ በቅዱስ ያሬድ እንደተደረሱ የሚነገርላቸው የተለያዩ የዜማ ዓይነቶች አሉ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋናው ድጓ ነው፡፡

ቅዳሴ ቤት

ይህ ት/ቤት ዲያቆናትና ቀሳውስት የቅዳሴን ዜማ በጥልቀት የሚማሩበት ት/ቤት ነው የቅዳሴ ትምህርት ሰደድኩላና ደብረ ዓባይ በሚል በ2 የዜማ ዓይነቶች ተከፍሎ የሚሰጥ ነው፡፡

ቅኔ ቤት

በዚህ ት/ቤት ተማሪዎች በግዕዝ ቋንቋ  ግጥምችን እንዲገጥሙ ት/ት ይሰጣቸዋል፡፡ ቅኔ ፣ የዜማና የግጥም ምጣኔ ያለው በእንግሊዝኛ ናፖይትሪን ከተሰኘው ቃል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው በቅኔ ቤት ተማሪዎች የሚማሩት የቅኔ ግጥም መግጠም ብቻ ሳይሆን የግዕዝ ቋንቋን ከሰዋሰዋዊ ህግጋቱ ጋር ነው በመሆኑም ቅኔ ማጥናት /መማር የግዕዝን ሥነ ጽሑፍ ለመረዳት ዋና ቁልፍ ነው፡፡

መጽሐፍ ቤት

ይህ ትምህርት ቤት የብሉይና የሐዲስ የመፃሕፍተ ሊቃውንትና የመፃህፍተ መነኮሳት ትርጓሜ የሚሰጥበት ትምህርት ቤት ነው፡፡በዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቤተክርስቲያንን ትውፊት፣ ዶግማ፣ታሪክና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በእያንዳንዱ ትርጓሜ አማካኝነት ይማራሉ፡፡

የቤተክርስቲያን ት/ቤቶች ጠቀሜታና አስፈላጊነት እስከ 19ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ ውስጥ ለማበራዊም ሆነ ለመንፈሳዊ ትምህርት ብቸኞች የትምህርት ተቋማት ሆነው አገልግለዋል ቀሳውስቱና የሀገሪቱ ሚኒስትሮች  የእነዚህ ት/ቤት ተቋማት ውጤቶች ነበሩ፡፡ የሕግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች፣ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ጸሐፊዎች ወዘተ ሥልጠና የሚያገኙት ከእነዚህ ት/ቤቶች ወይማ ገዳማት ነበር በአጠቃላይ ከዚህ መረዳት የምንችለው የቤት ክርስቲኒቱ ት/ቤቶች ለሃይማኖታዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን  ለማህበራዊ፣ ህጋዊ ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ አገልግሎቶች እጅግ በጣም አስፈላጊዎች እንደነበሩና እንደ ሆኑም ነው፡፡ በመሆኑም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት የታወቁ የቅዳሴ፣ ቅኔ፣ የአቋቋም፣ የድጓና የመጽሐፍ መምህራን መድቦ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ትምህርትን በመስጠት ላይ ገኛል፡፡

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡
በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው»

በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡  በመሆኑም ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡
ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና ሕዝብ በጎ ፈቃድ እና አርቆ አስተዋይነት ወደ እስክንድርያ ተልእኮ ለጵጵስና የበቃው የመጀመርያው ጳጳስ ፍሬምናጦስ ሀገረ ስብከት «ጳጳስ ዘአኩስም ወዘኩላ ኢትዮጵያ» የሚል ነበር፡፡ ከእርሱ በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ ቆይታለች፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በተለያዩ ጊዜያት ከአንድ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት ተሾመው መጥተው ስለነበር ከአንድ በላይ አህጉረ ስብከት እንደነበራት ይጠቁማል፡፡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1438 ዓም ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ከግብጹ ፓትርያርክ ዮሐንስ 14ኛ ተሾመው መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ለአምሐራ፣ አቡነ ገብርኤልም ለሸዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተመደቡ፡፡ ይህም በወቅቱ የነበረውን የሀገረ ስብከት አደረጃጀት ያመለክታል፡፡

በዐፄ ዮሐንስ ጊዜም በ1874 ዓ.ም አራት ጳጳሳት ከግብጽ መጥተው አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ማቴዎስ የሸዋ ጳጳስ፣ አቡነ ሉቃስ የጎጃም፣ አቡነ ማርቆስ የበጌምድር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ተሾመዋል፡፡ እነዚህ አበው በውል የተለየ ቦታ ተከልሎ ተሰጥቷቸው እንደነበር ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በጻፉት «ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ» በተባለው መጽሐፋቸው የአቡነ ማቴዎስን ሀገረ ስብከት ሲዘረዝሩ «ሸዋን ከበሽሎ ወዲህ መደብ አድርገው የጁን፣ ዋድላን፣ ደላንታን፣ ዳውንትን፣ ግራ መቄትን፣ ከበጌምድር መጃን፣ ስዲን፣ ፎገራን፣ ጭህራን፣ደምቢያን፣ አርማጭሆን፣ መረባን፣ ጃን ፈቀራን፣ ጃንዋራን፣ ቆላ ወገራን፣ ጠገዴን፣ ወልቃይትን» እያለ ይዘረዝራል፡፡

በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመርያዎቹን ጳጳሳት ስታገኝ የታወጀው ዐዋጅ ዐንቀጽ አንድ «የኢትዮጵያ የመላው ሊቀ ጳጳሳት በአቡነ ቄርሎስ ሆኖ ደቡቡ ለአቡነ ሳዊሮስ፣ ምዕራቡ ለአቡነ አብርሃም፣ ምሥራቁ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ አዜቡ ለአቡነ ሚካኤል፣ ሰሜኑ ለአቡነ ይስሐቅ ይሁን» ይላል፡፡ ይኼው ዐዋጅ የየአንዳንዱን ጳጳስ የሀገረ ስብከት ክልል ዝርዝር እና የመንበረ ጵጵስናውን ማረፊያ ከተማ ይተነትናል፡፡

በጣልያን ዘመን ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እና ጳጳሳት ተሰባስበው ብጹዕ አቡነ አብርሃምን ሊቀ ጳጳስ አድርገው አምስት ጳጳሳትን ሲሾሙ አዳዲስ አህጉረ ስብከት ተመሠረቱ፡፡ አቡነ ዮሐንስ የሸዋ፣ አቡነ ማርቆስ የኤርትራ፣ አቡነ ማቴዎስ የወሎ፣ አቡነ ገብርኤል የጎንደር እንዲሁም አቡነ ሉቃስ የወለጋ አህጉረ ስብከት ጳጳሳት ሆነው ተሾመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራስዋን አህጉረ ስብከት መመሥረት የጀመረችው ከራስዋ ልጆች መካከል ፓትርያርክ ባገኘች ጊዜ ነበር፡፡ በ1943 ዓም የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አቡነ ታዴዎስን ለጎሬ፣ አቡነ ገብርኤልን ለወሎ፣ አቡነ ማርቆስን ለኤርትራ፣ አቡነ ፊልጶስን ለኢየሩሳሌም፣ አቡነ ጎርጎርዮስን ለከፋ ጳጳሳት አድርገው ሾመው ነበር፡፡ ይህም አዳዲስ አህጉረ ስብከት መመሥረታቸውን ያመለክታል፡፡ በ1948 ዓ.ም ትግራይ በሀገረ ስብከትነት ተቋቁሞ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ተሾመውበታል፡፡  በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአህጉረ ስብከት ቁጥር በየጊዜው እያደገ መጥቶ፣ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ» በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጡት፣ በ1974 ዓ.ም የአህጉረ ስብከቱ ዕድገት ወደ አሥራ ዘጠኋ ያህል ደርሶ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም» የተሰኘው  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጽሐፍ እንደሚገልጠው አርባ በሀገር ውስጥ፣ ስምንት ከሀገር ውጭ፤ በድምሩ አርባ ስምንት አህጉረ ስብከት ይገኛሉ፡፡

የሀገረስብከቱ ራእይ፤ ተለዕኮ፤ አላማና ግብ

ራእይ

በአዲስ አበባ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን  በተገቢው መምራት፤ ምእመናንን በማስተማር በእምነታቸው ጸንተውና በምግባር ታንፀው በእናት ቤተክርስቲያናቸው መዋቅር ሥር ተጠልለው በተሟሏ መልኩ መንፈሳዊ አገልግሎትን ሲያገኙማየት፤ አድባራቱና ገዳማቱን በማስተባበር ልማትና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ሁለንተናዊ የቤተክርስቲኒቱ ዕድገት ዕውን እንዲሆንና ጠንካራ የምጣኔ ሀብትን በመፍጠር በመንፈሳዊም ሆነ በማህበራዊ መስክ ሁሉ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛ ማየት፡፡

ተልዕኮ

 • ምእመናን ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓታቸውን፣ ትውፊታቸውንና ባሕላቸውን እንዲያውቁ እና በምግባር እንዲጸኑማድረግ ፤
 • ስብከተ ወንወጌልና ሓወርያዊ አገልግሎት እንዲስፋፋ ማድረግ፤
 • የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ህግና ደንብን ተከትሎ እንዲሠራበት በማድረግ ሀብቷንና ንብረቷን መጠበቅና ማስጠበቅ፤
 • በአዲስ አበባ የሚገኙ ኢ-አማንያን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት አውቀው እንዲያምኑ እና የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እንዲሆኑ ማድረግ ፤
 • ቤተክርስቲያን ከታሪኳ እና ከታላቅነቷ ጋር የሚመጣጠን በሀገሪቱ ማኅበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ታሪካዊ ሚና እንዲኖራት ማስቻል፤
 • የካህናት መብት እና ግዴታ እንዲጠበቅ ማድረግ  ፤
 • ምእመናን እናት ቤተክርስቲያናቸውን በዕውቀታቸው ፣በገንዘባቸው እና በጉልበታቸው የሚያገለግሉበትን መንገድ ማመቻቸት፤
 • የካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞ የኑሮ ሁኔታ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ፤
 • ወጣቶችን በስነ ምግባር ማነጽና ለልማት ማዘጋጀት፤
 • ሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንዲጠናከሩ ማድረግ፤

ዓላማ

 • በሀገረ ስብከቱ ግልጽነት፤ተጠያቂነትና ተአማኒነት ያለው መልካም አስተዳደርና እንዲሁም የፋይናንስ አያያዝ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ፤
 • የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግንና በመጠበቅ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲኒቱ ሠራተኞች የኑሮ ደረጃ አቅምን ማሳደግና መፍጠር

ግብ

ብልሹ አሠራርና ኋላ ቀር አመለካከትን አስወግዶ አሁን ያለውን የቤተ ክርስቲያኗ ዓመታዊ ገቢ በእጥፍ አሳድጎ የገዳማቱና አድባራቱ ሠራተኞች የኑሮ ሁኔታ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት ነው፡፡

 

ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት ፣ ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊት፣ ብሔራዊት እንደመሆኗ መጠን በነበራትና ባላት ሃላፊነት የነበረውን ከማጠናከር  ጎን ለጎን ዘመናውያን ት/ቤቶችን በየቦታው በማቋቋም ትውልድን በዘመናዊ ትምህርትና ሥነ ጥበብ ስታስተምር ቆታለች፣ አሁንም በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡

ከእነዚህ ዘመናውያን ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች መካከል፡-

1.    የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም ጤና ሳይንስ ኮሌጅ

ይህ ኮሌጅ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በደብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደርና ምዕማናን አማካኝነት በ1997 ዓ.ም የተቋቋመ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ተማሪዎችን በከፍተኛ ውጤት በማስመረቅ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጀመሪያው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለህብረሰቡ ከሚሰጠው የጤና ሳይንስ ሥልጠና በተጨማሪ ለሠልጣኞች የተግባር ልምምድ የሚሆን እና ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ የተደራጀ ሆስፒታል የመገንባት፤እንዲሁም በትምህርት ጥራት፤በጥናትና ምርምር፤በሀገሪቱ ግንባር ቀደም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመሆን ራዕይ ያለው ከፍተኛ የተምህርት ተቋም ነው፡፡

ኮሌጁ በቀኑ ክፍለ ጊዜ በዲግሪና በዲፕሎማ መርሐ ግብር የሚያስለጥን ሲሆን የሚሰጠው የስልጠና ዓይነትም፡-
የሥልጠና መስኮች

 • በዲግሪ ፕሮግራም
  • በክሊኒካል ነርሲኒነግ
  • በፐብሊክ ሄልዝ(በጤና መኮንንነት)
 • በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ዘርፍ(በደረጃ ፕሮግራሞች)
  • በነርሲነግ ዘርፍ
   • በደረጃ 2 Health Care Giving
   • በደረጃ 3 Nursing Assistance
   • በደረጃ 4  Comprehensive Nursing
   • በደረጃ 4 Midwifery Nursing
  • በሕክምና ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ዘርፍ
   • በደረጃ 2 Medical Laboratory Assistance
   • በደረጃ 3 Medical Laboratory Service
   • በደረጃ 4 Medical Laboratory service
  • በፋርማሲ ቴክኖሎጂ ዘርፍ
   • በደረጃ 2 Retail Pharmacy Assisting
   • በደረጃ 3 Hospital/Community Pharmacy Assistance
   • በደረጃ 4 Pharmacy Technology Service

የመሳሰሉትን ሲሆኑ የትምህርት አሰጣጥት ሂደቱም በትምህርት ሚኒስተር ህግና ደንብ መሰረት ሆኖ ጥረቱን ጠብቆ ትምህርቱን / ስልጠናውን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

2.    የደብረ ሃይል ቅድስ ራጉኤል ኮሌጅ

ይህ ኮሌጅ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ካሉ ኮሌጆች መካከል ቀጥሎ የሚገኝ ዘመናዊ ኮሌጅ ሲሆን በመደበኛ ትምህርት የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችም፡-

 1. የአስተዳደር ሥልጠና
 2. የኮምፒያተር/አይቲ እና
 3. የአካውንቲግ ሥልጠናዎች ሲሆኑ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ የሚገኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ይህ ኮሌጅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ውጤት በማስገንዘብ ከመሰናዶ ት/ቤት ወደ ኮሌጅነት ደረጃ ያደገ ውጤታማ ት/ቤት ወይም ኮሌጅ ነው ፡፡ይህ ት/ቤት ልዩ የሚደርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአንደኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ማደጉ እና የመማር ማስተማሩን ሂደት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በመካሄድ ላይ እንዳለ ሆኖ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ባለው ቁርጠኝነት በኮሌጅ ደረጃ ት/ቤቱን አስፋፍቱ ትምህርት በጥራት መስጠት በመቻሉ ነው፡፡

በዚህም ረገድ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ፣የደብሩ አስተዳደርና ቦርድ ከበላይ አካል በመመካከር ያሳዩትን የሥራ ተነሻሽነት ለሌሎችም አድባራት አርአያ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው፡፡

1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በየገዳማቱና አድባራቱ ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያለውን ት/ቤት አቋቁሞ ተማሪዎች መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ እንዲማሩ በማደረግ ላይ ነው ሥጋዊ ጥበብ የሚባለውም በቀደሙት አባቶቻችን አባባል ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ፍቆ፣ ብዕርን ቀርፆ፣ መፃህፍትን መፃፍ፣ መጠረዝና መደጎስ እንዲሁም እርሻ ማረስ፣ ንግድ መነገድና የመሳሰለ ሲሆን እንደ ዘመኑ አባባል ደግሞ የቀለም ት/ቤቶችን አቋቁሞ /ከፍቶ በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እስከ ዮኒቨርሲቲ ያለውን ትምህርት መስጠት ማለት ነው በመሆኑም የኦ.አ.ሀ.ስ. ከሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት መካከል የሚከተሉት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡

 1. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት
 2. የደብረ ኃይል ቅድስ ራጉኤለ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት
 3. የምስካየ ሕዙናን መድሃኒዓለም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት
 4. የማህደረ ብርሃት ቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ዮኒቨርሲቲ ኮሌጅ
 5. የመንበረ መንግስ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ት/ቤት
 6. የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ት/ቤቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

1.    የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት

በ1955 ዓ.ም. መስከረም 14 ቀን የማስተማር ሥራውን የጀመረው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የተቀበላቸው የተማሪዎች 8 ብቻ ሲሆኑ እነዚህም መነኮሳትና ዲያቆናት ነበሩ፡፡ በ1956 ዓ.ም. ከ1ኛ እስከ 4ኛ ባሉ ቁጥራቸው 39 የሚደርሱ ተማሪዎችን ይዞ የመደበኛ ትምህርት ማስተማር ጀመረ፡፡ በዚያን ጊዜ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት “የኢትዮትያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት” በመባል ይታወቅም ነበር፡፡

ት/ቤቱን ለመክፈት ያስፈለገበት ዓላማም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ ሲሆን  ዓላማውም ካህናትን ዘመናዊ ትምህርት ለማስተማር ነው በመሆኑም በወቅቱ ለነበሩ መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ ማድረግ በቀላሉ የተከናወነ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የካቴድራሉ የበላይ አስተዳዳሪዎች ጥብቅ ቁጥጥር  እያደረጉ የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ት/ቤት ገብተው እንዲማሩ ይደረግ ነበር፡፡

ቀደም ሲል ለቀሳውስት ፣መነኮሳትና ዲያቆናት ዘመናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ታስቦ የተቋቋመው የካቴድራሉ ት/ቤት አገልግሎቱን ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የቤተክርስቲያኗ አንዱ ዓላማ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሲሆን ልጆቻቸው እንዲማሩላቸው ይጠይቁ የነበሩ ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለክፍያ እንዲማሩ ሲደረግ በአካባቢ የነበሩ ጫማ ጠራጊዎች፣ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጮች የትምህርት ዕድሉን እንዲያገኙ ተደርጓል።

ከዘመናዊ ሥርዓተ ትምህርት ጋር መንፈሳዊ ትምህርትም ይሰጥ ስለነበረ ት/ቤቱ ታዋቂነትና ዝና ያገኘው በጣም በፈጠነ ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ሲጠቀስ የሚችለው ተማሪዎች በትምህርት ችሎታቸው፣ በትህትናቸውና በሥርዓት አክባሪነታቸው ተለይተው ስለሚታወቁ በቀላሉ የህብረተሰቡን ትኩረት እንደሳበ ይነገርለታል፡፡

የተማሪዎች ቁጥር ሲጨምርና ት/ቤቱም እያደገ ሲሄድ ተማሪዎች መጠነኛ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያ-አምስት ብር-እንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትምህርት በክፍያ ሆነ፡፡የት/ቤቱ ፈላጊ ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይነት ነበረ፡፡

ት/ቤቱ መጀመሪያ ሲቆረቆር ይዞት የነበረው ቦታ አሁን ከካቴድራሉ ጽ/ቤት ጀርባ በነበሩ ክፍሎች ነበር፡፡ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ደግሞ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ 12ኛ ክፍል  በዚሁ ት/ቤት  የብሔራዊ ፈተና አስፈትኖ በወቅቱ በተደረገበት ተጽዕኖ ደረጃው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ደረጃ በቻ እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡
በ1966 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ የመጣው ሥርዓት በት/ቤቱ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም በእርሾነት እንዲቆይና ለዛሬው ደረጃ እንዲደርስ የካቴድራሉ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ ጥረትና መስዋዕትነት መክፈላቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይኸም በመሆኑ ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡-

 1. አፀደ ህፃናት
 2. የ1ኛ ደጃ ት/ቤት
 3. የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡

በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን እንደገና ማስተናገድ የጀመረው በ1ኛ ደረጃ ት/ቤት በ1996 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በመክፈት ነበር በመቀጠልም በ1997 ዓ.ም. አዲስ ባሠራው ህንፃ የ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ት/ቤቱ ትምህርት ሚኒስተር ያወጣውን ሥርዓተ ትምህርት በመከተልና ባለ 3 ፎቅ የራሱ ህንፃ ገንብቶ ት/ቤቱን ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,500 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡

ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡

2.    የምስካየ ህዙናን መድሃኒዓለም ገዳም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት

የምስካየ ህዙናን መድሃኒዓለም ገዳም 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤትከቀድሞው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት ቀጥሎ በ1974 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ት/ቤቱ ትምህርት ሚኒስተር ያወጣውን ሥርዓተ ትምህርት በመከተልና ባለ 4 ፎቅ የራሱን ህንፃ ገንብቶ ት/ቤቱን ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል የገዳሙ ት/ቤት በአሁኑ ሰዓት ከመዋዕለ ህፃናት እስከ መስናዶ ድረስ ከ2,000 ለሚያንሱ ተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ት/ት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ ት/ቤቱ በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲስ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች እንደ አንዱ ለመሆንና ለመቆጠር በቅቷል በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ገዳሙን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት ሆኗል፡፡

3.    የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ት/ቤት

የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ት/ቤት በድብሩ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደርና ልማት ኮሚቴ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ትብብር ሐምሌ 6 ቀን 1991 ዓ.ም ባለ 3 ፎቅ ህንጻ ተገንብቶ የመጀመሪ ደረጃ ት/ቤት የተከፈተ ሲሆን በ1997 ዓ.ም አሁን ወዳለው 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በማሳደግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ት/ቤቱ ወደ 2ኛ ደረጃ ተሸጋግሮ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ማትሪክ ሲያስፈትን በመሰናዶ ደረጃ ደግሞ ከ11 እስከ 12 ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በማስተማር ብዙዎቹ ጥሩ ነጥብ እያመጡ ዩኒቨርስቲ በመግባት ላይ ይገኛሉ በአሁኑ ጊዜ 1ኛ ደረጃውም ሆነ 2ኛ ደረጃው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙና ታዋቂ ከሆኑት ጥቂት ት/ቤቶች መካከል የሚጠቀስ ሆኗል፡፡

4.    የመንበረ መንግስ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ት/ቤት

የመንበረ መንግስ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ት/ቤት በ1998 ዓ.ም ተመስርቶ ከመዋዕለ ሕፃናት አስከ 10 ክፍል ድረስ የመደበኛ ትምህርት ለህብረተሰቡ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

5.    የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ት/ቤት

የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ት/ቤት በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ከ1ኛ እሰከ 8ኛ ክፍል ድረስ በማስተማር ላይ የሚገኝ ት/ቤት ነው

6.    ሌሎችም ለጊዜው ያልተጠቀሱ ነገር ግን በቀጣይ የሚጠቀሱ አሉ::

diocese

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት መልዕክት

diocese

ለሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንታዊት ታሪካዊትና ብሔራዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በረዥም ዘመንጉዞዋ ያበረከተችው እሴት ለአፍሪካዊያን መኩሪያና ለመላው ዓለም በታሪክ መዝገብ ከፍተኛሥፍራየሚሰጣት ቤተክርስቲያን ናት፡፡
በሀገራችን  የሚገኙት ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር ለሀገሪቱ ማንነት የስኬት ውጤትዋና መሠረቶች ናቸው፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን!
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እንደ አንድ ትልቅ ሃይማኖታዊ ተቋምነቷ ለሀገሪቱ ሰፊ ሥራን አበርክታለች፣ እያበረከተችም ነው፡፡በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ጥንታውያን አድባራትና ገዳማት /ካቴድራሎች/ ለምዕመናን በየቀኑ ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዳኝ በውስጣቸው ታሪካዊ ሙዚየሞች፣ ኮሌጆችና ዮኒቨርሲቲዎች፣ 1ኛና 2ኛ ደረጃት/ቤቶች፣ ክሊኒኮች፤ የሙያ ማሰልጠኛዎችና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ለሀገሪቱ እድገትና ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙ ናቸው፡፡
በመሆኑም ታሪካዊዋንና ጥንታዊትዋን ቤተክርስቲያን የበለጠ ለማወቅ የተዘጋጀው ይህ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ ለአብያተ ክርስቲያናት ጠቃሚ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ለሀገር ውስጥና ለውጪ ሀገር ጎብኚዎች መረጃን በመስጠት ጠቀሜታው እጅግ በጣም የላቀነው ብለን እናምናለን፡፡

በመሆኑም ቤተክርስቲያችን ብዙ ዘመናትን ተሻግራ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ የደረሰች ሲሆን በዚህ በተጓዘችባቸው ጉዞዎች አባቶቻችን ሃለፊያትንና መፃዕያትን በመገንዘብ አስቀድመው ከትውልድ ሃሳብ ቀድመውና ከትውልድ እኩል እየተጓዙ ክርስትናን አቆይተው ለእኛ አስረክበውልናል፡፡

እኛም ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሃይማኖት ለትውልዱ ዘመኑ በሚፈቅደው መሳሪያ በመገልገል ሐዋሪያዊ መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊነው ፡፡ የሰው ልጅ ሲፈጠር በቦታ የሚወሰንና የሚገደብ ሆኖ በመፈጠሩ በአንድ ሥፍራ ሆኖ በሌላ ስፍራ ያለውን ነገር በራሱ ለማወቅ አይችልም፡፡
ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንደ ቅዱሳኑ በሕይወቱ ሳለ በቅቶ ሲገኝ ብቻ ነው አለ በለዚያ በሀገር ርቀት ምክንያት ሰዎች ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ሌሎች መንገዶችን መጠቀም ስለነበረበት ከእግዚአብሔር በተሰጠው አዕምሮ በመጠቀም የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን ሰርቷል፡፡

ከእነዚህም መካከል አሁን በዚህ ዘመን የተጀመረው የመረጃ መረብ ቴክኖሎጅ አንዱነው፡፡ይህም ቴክኖሎጂ ትውልዱ ሲጠቀምበት በዓለማዊ ትምህርት ብቻ እንዳይዋጥ መንፈሳዊ ትምህርትንም ለማስታላለፍ ጥሩ አማራጭ መንገድ ነው። ቤተክርስቲያንም በዘመኑ ያሉትን በዕውቀቱ የተካኑትን ልጆቿን በመጠቀም ዘመኑ ባስገኘው መሳሪያ ትምህርት እንዲስተላለፍ መደረጉ አግባብ ነው፡፡

አባቶቻችን ሐዋሪያት በቁጥር ጥቂቶች ሲሆኑ የተሰጣቸውን የወንጌል ቃል እስከ ምድር ዳርቻ ምስክሮች በመሆን በልዩ ልዩ ቋንቋ ፣ የወንጌሉን ቃል ለዓለም ሁሉ አዳርሰዋል፡፡
በዚህ ዘመን ደግሞ ይህንን ዓለም አቀፍ ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ለመፈጸም ቴክኖሎጂውን መጠቀም ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ሰዎችን በቀላሉ ስለ ሀገረ ስብከታችን ሁለንተናዊ የሥራ እንቅስቀሴም ይሁን ትምህርታዊ የሆኑ ጽሁፎችን በማዘጋጀት በዌብሳይቱ ብዙ ሰዎችን በቀላሉ ማስተማር ይቻላል፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሀገረስብከቱ የሚጠበቅበት ድርሻውን ለማበርከት ለሚያደርገውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከጎኑ ሆናችሁ የሚጠበቅባችሁን ማንኛውንም የቤተክርስቲያን አገልግሎት ተሳታፊ እንድትሆኑ ሀገረ ስብከቱ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

 

 

ሊቀ ኅሩያን ሰርፀ

የምስራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ